የሹሩባ ትንሳኤ

0
1050

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች እና በርካታ ባሕላዊ አልባሳቶች በተጨማሪ ለየት ያለ የጸጉር አሰራር ባለቤት በመሆን ትታወቃለች። እንደ ጉዱላ፣ ዘራንቺ፣ ጉቴና፣ ናዝራው እና ሹሩባ የመሳሰሉት የጸጉር አሰራሮች በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎችን ሀይማኖት፣ ዕድሜ፣ የጋብቻ ሁኔታንና መሰል ሁኔታችዎችን ለመጠቆም ይረዳሉ። በተለይ ሹሩባ ጥንታዊና በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች በስፋት የሚታወቅ ነው።

ሹሩባን ሴቶችም ወንዶችም ከመሰራታቸው በተጨማሪም ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደ አርበኝነትና ጀግንነት ምልክት ይወሰድ ነበር። የጦር ተዋጊዎችና እንደ አጼ ቴዎድሮስ፣ አፄ ዮሐንስና አፄ ምኒሊክ ያሉ ንጉሦችና ጣይቱና ዘውዲቱን መሰለ ነገስታትም በሹሩባ ይታወቃሉ። የሹሩባ ዓይነቶች እንደየቦታውና እንደ ማኅበረሱቡ ባሕል የተለያየ ከመሆኑ ባሻገር ሹሩባውን ለማስጌጥ የሚጠቀሙበት ማስጌጫም ከቦታ ቦታ ይለያያል። ለምሳሌ በትግራይ ግልባጭና አልባሶን ጨምሮ በርካታ የሹሩባ ዓይነቶች አሉ። በተለምዶ የትግሬ ሹሩባ እየተባለ የሚጠራው የሹሩባ ዓይነት ጸጉር በቀጫጭኑ ወደ ኋላ እየተከፈለ የሚሠራ በመሆኑ ለመሥራት ረዘም ያለ ጊዜ ከመውሰዱ በተጨማሪ በቂ ልምድ ባለው ሰው የሚሠራ ነው። በትግራይ ከወርቅ፣ ከብር ወይንም ከነሐስ በተሰራ ጌጣጌጥ ሹሩባን ማስጌጥ የተለመደ ነው።

ምንም እንኳን ሹሩባ የኢትዮጵያዊያን ባሕህላዊ የጸጉር አሰራር ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለይ በከተማ አካባቢ ሹሩባ የተሠራ ብዙ ሰው ማየት አስቸጋሪ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያየ ቅርጽ በሹሩባ ተውበው የሚሔዱ ሴቶችን ቁጥራቸው እየጨመረ ነው።

በከተማችን ውስጥ ባሉ አብዛኛው የውበት ሳሎኖች ውስጥም እንደ ሞሮኮ ባዝ፣ ስቲም፣ ፌሺያልና መሰል አገልግሎቶች በተጨማሪ የሹሩባ አገልግሎትን ማግኘት ያን ያህል አዳጋች አይደለም። በጸጉር ቤቶች ውስጥ በደንብ ከሚታወቁት የሹሩባ ዓይነቶች መካከል አልባሶ አንዱ ነው። ከፊት ጸጉር ጀምሮ ወደ ኃላ እየተጎነጎነ ሔዶ ግማሽ ላይ የሚያልቀው አልባሶ በአብዛኛው ሰባት ቦታ የሚሠራ ሲሆን ከኋላ ያለው ጸጉር ተበጥሮ ይበተናል። በመሲ የውበት ሳሎን የጸጉር ሥራ ባለሞያ የሆነችው ያብሥራ አረጋ “በአብዛኛው ሴቶች ይህን የሹሩባ ዓይነት ለመሠራት የሚመርጡት በበዐል፣ በጾም ወይንም በሰርግ ወቅት ነው” በማለት ትገልጻለች።

ያብሥራ አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች ሹሩባ የሚዘወተር ሳይሆን ወቅትን መሰረት አድርጎ እንደሚሠራ ትናገራለች። “በዝናብና በጾም ወራት ብዙ ሴቶች ሹሩባ የሚሠሩ ሲሆን በሌሎች ወራት እንደ ፔስትራ (ተኩስ) ያሉ የጸጉር አሰራሮችን ይጠቀማሉ” ብላለች። በመሲ የውበት ሳሎን ሹሩባን በእራስ ጸጉር ለመሠራት ሀምሳ ብር የሚያስከፍል ሲሆን ዊግ ለሚጠቀም ሰው ደግሞ ዋጋው ወደ ሀምሳ አምስት ብር ከፍ ይላል። አብዛኛውን ጊዜም የአንድን ሰው ጸጉር ለመሥራት ኹለት ዊግ ያስፈልጋል።

ሰብለ ሞላ የመሲ የውበት ሳሎን ደንበኛ የሆነችና ወርቃማ ጸጉር ያላት የሃያ አራት ዓመት ወጣት ናት። አብዛኛውን ጊዜ ፔስትራ ወይንም መጠቅለል የምትሠራ ቢሆንም ጸጉሯን ከጉዳት ለመከላከል አልፎ አልፎ ሹሩባ ትሠራለች። ሰብለ “በወደዱት መንገድ ጸጉርን ማስዋብ ድፍረት ይጠይቃል። እንዲሁም የጸጉርን ቀለም ለመቀየርና ለማስዋብ የምንጠቀማቸው ኬሚካሎች ጸጉርን የመጉዳት አቅም አላቸው። በመሆኑም የጸጉርን ጉዳት ለመከላከል ሁሌ ፔስትራ ከመሰራት አልፎ አልፎ ሹሩባ መሰራት ጠቃሚ ነው” ትላለች። በውበት ሳሎኖች ውስጥ ሹሩባ የሚሠሩት እንደ ሰብለ ያሉ ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕፃናትና ልጆችም ጭምር ናቸው። እንደ ማርታ የልጆች ሳሎን ዓይነት ጸጉር ቤቶች ደግሞ ለልጆች ብቻ አገልግሎት በመስጠት ይታወቃሉ። ቦሌ ድልድይ ፊት ለፊት የሚገኘው ማርታ የልጆች ሳሎንን የከፈቱት ቶማስ ጎአ እና ወንድሙ ሥራቸውን የጀመሩት ከአራት ዓመት በፊት ነበር። “ሹሩባ በልጆች ዘንድ የሚዘወተር ነው” የሚለው ቶማስ የጸጉር ቤቱን የውስጥ ክፍል ልጆችን በሚማርክ መልኩ ያስዋበው ልጆችን ለማስደሰት እንደሆነ ይናገራል። በእረፍት ቀናት በቀን እስከ ዐሥራ አምስት የሚደርሱ ልጆች በማርታ የውበት ሳሎን ጸጉራቸውን የሚሠሩ ሲሆን በሥራ ቀናት ግን በአማካይ ሦስት ልጆች ብቻ ናቸው የሚሠሩት። “አብዛኞቹ ደንበኞቻችን ልጆች ስለሆኑ ሥራ የሚበዛው ቅዳሜና እሁድ ነው። ከሰኞ እስከ አርብ ባለው ጊዜ ደንበኞቻችን የሚመጡት ከሥራ በኋላ ነው” በማለት ቶማስ ገልጿል።

የሰዎች የገቢ ምንጭ ሲጨምርና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በቀላሉ በአቅራቢያ ማግኘት ሲቻል ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ጸጉር ቤቶች በመውሰድ ማሠራት ይጀምራሉ። የሦስት ልጆች እናት የሆነችው መስከረም ከበደ ከእነዚህ ወላጆች መካከል አንዷ ናት። መስከረም ልጆችዋን ወደ ጸጉር ቤት የምትወስድበትን ምክንያት ስታስረዳ “ብዙ ጊዜ ልጆቼን ይዤ ወደ ማርታ ሳሎን እመጣለው። የተወሰኑ አይነት የሹሩባ ዓይነቶችን መሥራት ብችልም የጸጉር ባለሞያዎች ግን ብዙ ዓይነት መሥራት ይችላሉ” በማለት ነው። መስከረም ለሹሩባ የምትከፍለው መቶ ብር ጥሩ ዋጋ እንደሆነ ታምናለች።

እነቶማስ ሥራቸውን የጀመሩት ሃያ ኹለት አካባቢ በአንድ ወንበርና በአንድ ሠራተኛ ቢሆንም አሁን ግን ቦሌ አካባቢ መጠነኛ ስፋት ያለው አንድ ክፍል ቤት በአስር ሺሕ ብር በመከራየትና እስከ ሦስት ሺሕ ብር ደረስ የወር ደሞዝ የሚከፈላቸው ሦስት ሠራተኛ በመቅጠር ሥራቸውን አሳድገውታል። እነቶማስ ሥራቸውን እያሳደጉት ቢመጡም እንዲሁም ሹሩባ በሁሉም ጸጉር ቤቶች ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ቢሆንም ብቻውን ግን አትራፊ ሥራ አይደለም ብለው የሚከራከሩ የጸጉር ቤት ባለቤቶች አሉ። ደንበል አካባቢ የሚገኘው ሚኪ የውበት ሳሎን ባለቤት የሆነው ሚኪያስ በለጠ ሐሳቡን “ሹሩባ ወቅትን ጠብቆ የሚሠራ ከመሆኑ ባሻገር ብዙ ሴቶች ሹሩባን እንደፋሽንና ዘመናዊነት ስለማይቆጥሩት ሁሌ አይሠሩም። በተጨማሪም አብዛኛው ሴቶች ሹሩባ መሥራት ስለሚችሉ እንደኛ ባሉ ጸጉር ቤቶች ውስጥ መቶ ሀምሳ ብር ለመክፈል ፈቃደኛ የማይሆኑ አሉ በማለት” አጠናክሯል። አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ማካተትና ሹሩባን በተገቢው ማስተዋወቅ ቢቻል ከሹሩባ ሥራ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚረዳ ሚኪያስ ያምናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here