የ‘ኦሮማራ’ አንድምታ

0
1039

በኢትዮጵያ እያየነው ያለነውን የፖለቲካ ሽግግር ያመጣው የኦሮሞ እና አማራ ፖለቲከኞች ትብብር ነው። ‘ኦሮማራ’ የሚለው ሥያሜም የኹለቱን ሕዝቦች ኅብረት ያመላክታል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ኹለቱን ተዋናዮች ብቻ በማሳተፍ እና ሌሎቹን በማግለል ላይ የተመሠረተ አካሔድ አለ የሚሉት ሳምሶን ኃይሉ፥ በዚህ ዘመን ይህ ዓይነቱ አካሔደ አያዋጣም ይላሉ።

 

ባሳለፍነው ሳምንት የአማራና ኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የፌደራልና ክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች እና ከኹለቱ ክልሎች የተወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገኙበት የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ በአምቦ ከተማ ተካሔዶ ነበር። መድረኩ የሕዝብ ለሕዝብ ትሥሥርን በማጠናከር ትክክል ባልሆነ ትርክት ምክንያት የኹለቱን ክልል ሕዝብ ለማጋጨት የተወጠኑ ሴራዎችን ለማክሸፍና ሕዝቦችን በማስተሳሰር አገራዊ ለውጡን ማስቀጠልን እንደ ዓላማ አንግቦ የተነሳ ነበር። መድረኩም ከአንድ ዓመት ከግማሽ በፊት በኹለቱ ክልል ባለሥልጣናትና ሕዝቦች ማካከል በባሕር ዳር የተካሔደው ውይይት ቀጣይ ምዕራፍ ነው።
ሁላችንም እንደምናስታውሰው በባሕር ዳር የተካሔደው ውይይት በኹለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል ለዘመናት አንዱን በዳይ ሌላውን ደግሞ ተበዳይ አድርጎ በሳለ ትርክት ምክንያት ሰፍኖ የነበረን የተቃርኖ መጋረጃ በመቅደድና ልዩነት በማጥበብ አገርን ከመበታተን ከመታደግ በሻገር ለጥቆ ለመጣው የፖለቲካ ለውጥ መሠረት የጣለ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም።

እንደዚህ ዓይነት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር መድረክ የአገር ግንባታ ሒደቱን እንደሚያፋጥነው እሙን ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩባት አገር በመሆኗ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያሳልጡ መድረኮች ልዩነትን በማጥበብ ሁሉም ዜጎች የሚጋሩት የጋራ የሆነ አገራዊ ማንነት (shared national identity) ለመፍጠር ይረዳሉ። ይህን እውነታ ከግምት ውስጥ አስገብተን በተለይም ከለት ተዕለት በአማራና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ፖለቲካኞችና ልኂቃን መካከል እየጠበቀ የመጣውን ጥምረት ስንመለከት አሉታዊ መልክ ያለው ቢመስልም ጠለቅ ተብሎ ሲመረመር ግን የአገር ግንባታ ሒደቱ ላይ የሚኖረው አስተዋፅዖ የተገላቢጦሽ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።

ይህንን ለመገንዘብ በተለይም በአምቦ የተካሔደውን ውይይት ጨምሮ በኹለቱ ብሔሮች ፖለቲካኞችና ልኂቃን መካከል የተመሠረተው ጥምረት ዓላማ በዝርዝር መመርመር ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ጥምረቱ በዋነኝነት ዓላማ ያደረገው ለዓመታት የኹለቱን ክልል ፖለቲካኞች፣ ልኂቃንንና ሕዝቦች ሲያነታርክና ብሎም ሲያባላ የነበረውን የትርክት መርዝ አርክሶ በቀጣይነት ኢትዮጵያን ለምታደርገው የአገር ግንባታ መሠረት ለመጣል ነበር። ይሄ ዓላማ ግን ቀስ በቀስ ወደ ጎን በመገፋት በኹለቱ አብላጫ ቁጥር ባላቸው ሕዝቦች ላይ የተመረኮዘና በአብዛኛው እነዚህ ኹለት ብሔሮች ላይ ትኩረትን አድርጎ ሊተገበር በታቀደ የአገር ግንባታ ውጥን ግብዓት ወደማሰናዳት አዘንብሏል።

በግልጽ እንደምናየው በአማራና ኦሮሚያ ብሔሮች መካከል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚደረገው ሙከራ ሁሉ በሌሎች መካከል ሲደረግ አይስተዋልም። በዚህ ረገድ ጥቂት የሚባሉ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም እንኳን በቂ የሚዲያ ሽፋን አላገኙም። ይህ የሚያሳየው ሒደቱ አግላይነት እንደሰፈነበት ነው። በተደጋጋሚ የአማራና ኦሮሞ ፖለቲካኞና ልኂቃን የሚያሰሙት ንግግር ይህን ያጠናክራል። እንደውም በዚህ ሰዓት ከኹለቱ ብሔሮች የተውጣጡ ፖለቲካኞና ልኂቃን በአማራና ኦሮሞ አንድነት ላይ የተገነባ ስርዓት እንደማይፈርስ ሲናገሩ ማድመጥ የተለመደ ሆኗል። ከዚም አልፎ የፊደራሉን ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች በአብዛኛው ከኹለቱ ክልል ብቻ በመጡ ሰዎች እንዲያዝ ተደርጓል።

እንደሚታወቀው የአማራና ኦሮሞ ብሔሮች ሲደመሩ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በላይ ቁጥር አላቸው። በተጨማሪም በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አብላጫውን ወንበር ይይዛሉ። ስለሆነም እነዚህ ብሔሮች በአገር ግንባታው ሥራ ላይ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። ይህ ማለት ግን የተቀሩት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገር ግንባታው ላይ ያነሰ ሚና ይኖራቸዋል ማለት አይደለም።

የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው በአገር ግንባታ ሒደት ውስጥ ብዙ ተሳታፊወች ቢኖሩም በዋነኝናት ግን ኹለት ስብስቦች ይኖራሉ። የመጀመሪያው አውራ ቡድን (core group) የሚባለው ሲሆን በውስጡ ፖለቲካኞና ልኂቃን ያካተተ ነው። ይህ ቡድን ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊዋቀር ይችላል። ለምሳሌ በአሜሪካ ነጭ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮችና የአንግሎ ሳክሰን ደም ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገነባ ነው። በጃፓን ደግሞ የሳሞራይ ጦረኞች ወገን የተገኙ ሕዝቦች የአውራ ቡድን ዋነኛ መሠረቶች ናቸው።

ከጦርነት በኋላ ድል በሚያደርግ ስብስብ ይህ አውራ ቡድን ሊዋቀር ይችላል። ለምሳሌ 1983 የደርግ መንግሥትን ድል ያደረገው በሕወሓት የበላይናት ከሚመራው የኢሕአዲግ መንግሥት የመጡ ፖለቲከኞችና ልኂቃን የአገር ግንባታ ዋነኛ ተሳታፊዎች እንደነበሩ የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። ከዚህም ባሻገር የሕዝብ ቁጥር አብላጫ ባላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አውራው ቡድን ሊገነባ ይችላል። በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት ያለው አሰላለፍ ይህንን የተከተለ ይመስላል። አብላጫ ቁጥር ባላቸው የአማራና ኦሮሞ ፖለቲከኞችና ልኂቃን የፖለቲካው ምኅዳሩ ተሞልቷል።

ኹለተኛው ስብስብ ደግሞ አናሳ ቡድን (minority group) የሚባለው ሲሆን ከፖለቲካ ምኅዳሩ በተለያየ ምክንያት የተገለሉ ወይንም አናሳ ቁጥር ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚዋቀር ነው። አሁን ባለው የፖለቲካ አሰላለፍ ይህ ቡድን በትግራይ ክልል ያሉ ፖለቲከኞችና ልኂቃን እና በሌሎች አናሳ ክልሎች ከዓመት በፊት ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎችን ያካትታል። እንግዲህ በነዚህ ኹለት ቡድኖች መካከል የሚኖረው መስተጋብር ነው የአገር ግንባታውን አቅጣጫ የሚወስነው።
የአገር ግንባታ ስልቶች

የአውራው ቡድን ዋናው ዓላማው የአገር ግንባታውን የተለያዩ ፖሊሲዎች በመተግበር ማሳካት ነው። አገር ለመገንባት የሚጠቅሙ ሦስት ዓይነት ስልቶች አሉ። የመጀመሪያው የአውራው ቡድን ከሱ የተቃረነ አስተሳሰብ የሚያራምደውን አናሳውን ቡድን ከአገር ግንባታ ሒደቱ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም በማግለል (exclusion strategy) አንድን አገር በራሱ አምሣያ መገንባት የሚያስችል ነው።

ከምዕተ ዓመታት በፊት የአገር ግንባታ የቤት ሥራቸውን ያጠናቀቁ የአውሮፓ እና እንደ አሚሪካ ያሉ አገራት ይህን ዘዴ በስፋት ተጠቅመውበታል። ለምሳሌ አሜሪካንን የገነባው ቡድን ተቀናቃኝ የነበሩትን ከ1861 እስከ 1865 በተደረገው የርስበርስ ጦርነት ድል በማድረግ ከሒደቱ እንዲገለሉ አድርጓል። በኢትዮጵያም ቢሆን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የነበሩት አገርን የመገንባት እንቅስቃሴዎች ተመሳሳይ ይዘት ነበራቸው።

ኹለተኛ ስልት የአናሳው ቡድን አስተሳሰቦች፣ ባሕሎችና ቋንቋዎች የተለያዩ ዘዴዎቸን በመጠቀም በአውራው ቡድን አስተሳሰቦች፣ ባሕሎችና ቋንቋወች እንዲዋጥ በማድረግ (assimilation strategy) የአገር ግንባታውን ከዳር የሚያደርስ ነው። ከእርስ በርስ ጦርነቱ በኋላ ከተለያየ አቅጣጫ በስደት ወደ አሜሪካ በስደት የገቡ ሕዝቦች በተለያየ መንገድ ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውን እና አስተሳሰባቸውን በማጥፋት የአገሪቱ አካል እንዲሆኑ ተደርጓል።

ሦስተኛውና በዚህ ዘመን ተመራጭ የሆነው ስልት ደግሞ በአውራውና አናሳው ቡድን የሚራመዱ የተለያዩ ሐሳቦችን፣ ቋንቋዎችንና ባሕሎቸን በማሥማማትና በማቀራረብ (accommodation strategy) ሁሉም ዜጎች የሚጋሩት ማንነትን ቀስ በቀስ ለመፍጠር የሚያስችል ነው። ይህ ስልት በተቻለ መጠን የአናሳ ቡድኑን ፍላጎት ሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ ተመሥርቶ በማካተት ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአገር ግንባታው ላይ አስተዋፅዖ እንዲኖራቸው ያደርጋል።

የመጀመሪያውና ኹለተኛው ስልቶች ግን ይህን ዕድል ለዜጎች አይሰጡም። ይህን ለማየት ሩቅ ሳንሔድ 1983 ቡኋላ በህወአት የበላይናት የሚመራ የነበረው የኢህአዲግ መንግስት የተጠቀመበትን ስልት ማየት በቂ ነው። ይህ ቡድን ከተቻለ ሀይልን በመጠቀም ተቃራኒ ሀሳቦችን ወደራሱ በማምጣት አለበለዚያም ደግሞ የተለያዩ የፖለቲካ ሐሳቦችን የሚያራምዱ አካላትን በማሰርም ሆነ ከአገር በማባረር የአገር ግንባታውን እውን ለማድረግ ሞክሯል። ይህም አካሔድ በዋነኝነት ከፋፍሎ መግዛት መርሕን በመጠቀም በተለይም ትልቅ ተፅዕኖ ሊኖራቸው የሚችሉትን የአማራና ኦሮሞ ብሔሮች መካከል የነበረውን ቅራኔዎች በማስፋት ከሒደቱ ማግለልን መርጧል።

በተመሳሳይ መንገድ የአውራ ቡድኑን ለማዋቀር ዕድል ያገኙት የአማራና ኦሮሞ ፖለቲከኞችና ልኂቃን ከተቻለ የተለያየ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱ አካሎችን ከሥልጣን ማማው በማስወገድ አለበለዚያም ደግሞ ከሒደቱ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲገለሉ በማድረግ አገርን የመገንባት ሥራውን ጀምረውታል። ይህን ለመገንዘብ በቅርብ ወራቶች እንደ አፋር፣ ሱማሌ እና ቤንሻንጉል ዓይነት ክልሎች ከታየውን ሹም ሽር በተጨማሪ የትግራይ ፖለቲከኞችና ልኂቃንን ከሒደቱ ለማግለል የሚደረገውን ጥረት ማየት ይበቃል።

ከራሳችን ተሞክሮ በቅርቡ የተረዳነው በኢትዮጵያ የሚደረግ የአማራና ኦሮሞ ብሔሮች ያላቀፈና ያላሳተፈ የአገር ግንባታ ትርፉ ኪሳራ መሆኑን ነው። በተመሳሳይ መንገድም ኹለቱን ብሔሮች ብቻ አቅፎ ሌላውን የሚያገል ሒደት መጨረሻውን ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here