መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳየኑሮ ውድነት ያጠላበት የበዓል ዋዜማ

የኑሮ ውድነት ያጠላበት የበዓል ዋዜማ

ለዓመታት በአገሪቱ የታየው የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ዕለት ተዕለት እየጨመረ መጥቶ አብዛኛውን ሕዝብ በመፈታተን ላይ ይገኛል። የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት፣ የምንዛሬ እጥረት፣ የትምህርት ቤት ክፍያዎች ማሻቀብና ሌሎችም ማኅበረሰቡን ሰቅዘው ከሚገኙት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ሸማቾችን፣ ነጋዴዎችንና  የዘርፉን ባለሙያዎች በማነጋገር የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

“የተለያዩ ዓይነት የምግብ ሸቀጦችና የእርድ እንስሳት ሥጋ ዋጋ ከአቅም በላይ ሆኗል። በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሲሔድ እንጂ ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር ሲጣጣም አይታይም።

በዚህም የተነሳ ‹‹በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን ትንሳኤን የሚያክል ታላቅ በዓል በጥሩ ዝግጅት ለማሳለፍ ቀርቶ የዕለት ፍጆታን ለመሸፈን በማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ለዘመናት ʻዶሮ ዶሮʼ ይሸትበት የነበረው በዓል ዛሬ የሰንበትን ያክል ሊከበር የሚችል አይመስልም።››

ይህንን አስተያየት የሰነዘሩት በተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ለትንሳኤ በዓል ቅቤና ዘይት፣ ዶሮ፣ በግ፣ እንቁላል፣ የጤፍና የስንዴ ዱቄት ሲሸምቱ ካገኘናቸው ሸማቾች መካከል አንዳንዶቹ የበዓሉን ዝግጅትና የገበያውን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡን አስተያየት ነው። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አባባል ከሆነ በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ የተደረገው ጭማሪ መሰረታዊ ነገሮችን ለመሸፈን እንኳን የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ነው።

ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከተደረገባቸው የምግብ ሸቀጦች መካከል የምግብ ዘይትና ቅቤ፣ በአባይ ሚዛን የሚቸረችሩት ጥራጥሬዎችና የእህል ዱቄት፣ ሥጋ የመሳሰሉና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመው፣ ይህንን የሚከታተልና የሚቆጣጠር መንግሥታዊ አካል መኖሩን በመገናኛ ብዙኀን እንደሚሰሙ፣ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አካል በሥም እንጂ በገቢር እንደማይታይና በአሻጥረኞችም ላይ ዕርምጃ ሲወስድ እንዳልተሰማ ወይም እንዳልታየ ነው ያስረዱት።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነዋሪ የሆኑና መርካቶ ቅቤ ተራ ያገኘናቸው ወይዘሮ ጸሐይ አበበ “ኑሮዬ መካከለኛ ገቢ ካላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይመደባል። ቢያንስ ቢያንስ በአንድ ኪሎ ቅቤና በአንድ ዶሮ በዓሉን መጠን ባለ ሁኔታ ከቤተሰቤ ጋር በደስታ አሳልፋለሁ ብያለሁ። ይህም የሆነበት ምክንያት የኑሮ ውድነቱ የበዓሉን ዝግጅት አደብዝዞታል የሚል እምነት ስላለኝ ነው፤” ብለዋል።

ፒያሳ አትክልት ተራ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 16 ብር ሲቸረቸር ብንመለከትም፣ በየመንደሩ በሚገኙ ሱቆችና ጉልቶች አንድ ኪሎ ሽንኩርት 22 ብር፣ ድንች 17 ብር፣ ካሮት 28 ብር፣ ቅቤ 300 ብር፣ አይብ በመርቲ ጣሳ 200 ብር ሲሸጥ ታዝበናል። ሽንኩርቱ በጣም እርጥብና እሸት ከመሆኑም ሌላ ደረጃውን ያልጠበቀና አልፎ አልፎም የበቀለ ነው። “ውድ የሆነበት ምክንያት ወቅቱ ገና ስለሆነና ስላልደረሰ ነው፤” ያለን ሚዛን አንጠልጥሎ ሲቸረችር የነበረው ወጣት ነው። በገበያ ላይ ተፈላጊና አንገብጋቢ የሆነው ቀይ ሽንኩርት ከተወደደ ዶሮ ሰርቶ መብላት የማይታሰብ ነው እንደሸማቾቹ አስተያየት።

በሾላ ገበያም ቢሆን የእህል ጥራጥሬና የአትክልት ዋጋ ከሌላው ጊዜ ዋጋው ጨምሮ ተስተውሏል። ነጋዴዎች ስለምክንያቱ ለማስረዳት ግን ፍላጐት የላቸውም። የሚናገሩት ቢሆኑም ስናመጣውም ውድ ነው ከማለት ውጭ ዝርዝር መረጃ አይሰጡም።
ልጃቸውን አስከትለው በግ ሲያማርጡ ያገኘናቸው አባወራ ዋጋው እንደማይቀመስ ነው የተናገሩት። የያዙት ገንዘብና በግ ነጋዴዎቹ የሚጠሩት ዋጋ ፍጹም አይገናኝም። ሙክት በግ 4 ሺሕ ብር፣ መካከለኛ እስከ 2 ሺሕ 500፣ አነስተኛ ጠቦት እስከ አንድ ሺሕ ስምንት መቶ ብር ይጠሩባቸዋል። ጉማሬ አለንጋ በትከሻው ላይ ጣል ያደረገ አንድ በግ ነጋዴ ወደ አጠገባችን ቀረብ ብሎ “ምን እናድርግ! አሁን ይችን አነስተኛ በግ ከገበሬው የገዛሁት በአንድ ሺሕ አራት መቶ ብር ነው፤ የትራንስፖርት ወጪውንና ድካሜንም አስባችሁ ስንት ብር ብሸጥ ያዋጣኛል ትላላችሁ? እስቲ ፍረዱ፣ ፍርድ ከራስ ነው” አለን። ይኸው ነጋዴ የጠቆመንን በግ 1 ሺሕ 800 ብር ሲጠራባት ሰማን።

ወደ ዶሮ ተራም አቅንተን ነበር። በሥፍራው ያነጋገርናቸው ሒሩት ብርሃኑን ነው። በጉያቸው አንድ ቀይ ዶሮ አቅፈው፣ በግራ እጃቸው በሸቀጥ የተሞላ የፕላስቲክ ከረጢት አንጠልጥለዋል። ዶሮውን ስንት ገዙት? አልናቸው። “300 ብር” አሉን። “እንቁላል ውድ ስለሆነ ተውኩት። ዶሮ አለእንቁላል አይሠራም ያለው ማንነው? እኔ ከድንች ጋር በጥሩ ሁኔታ አዘጋጅቼ አቀርባለሁ፤” ብለውን ተለዩን። የዶሮና የእንቁላል ዋጋ አይቀመስም። ከፍተኛ እስከ 300 ብር፣ መካከለኛው 180 ብር፣ ሴት ዶሮ 150 ብር ሲሸጥ አንድ እንቁላል በአራት ብር ሲቸረቸር ተመልክተናል። አንዳንድ የዶሮ ነጋዴዎች ይህንኑ አስመልክተው እንዳብራሩልን ከሆነ እነሱም ከገጠር የሚገዙት በውድ ዋጋ መሆኑንና የትራንስፖርትም ወጪ ለዋጋው መናር ምክንያት ሆኗል።

ለዳቦ የሚሆን የስንዴ ዱቄት ነጋዴዎች ኪሎውን በ23 ብር ሲሸጡ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሱቆች ደግሞ በ18 ብር በመሸጥ ገበያውን ለማረጋጋት ሲሞክሩ አስተውለናል። በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር ካነጋገርናቸው አንዳንድ እናቶች እንደነገሩን ከነጋዴውም ሆነ ከማኅበራቱ የሚገዙት የስንዴ ዱቄት ጥራቱን የጠበቀ አይደለም። ዱቄት ተቦክቶ ከተጋገረ በኋላ ቶሎ የመድረቅና የመፈርፈር ባሕሪ አለው፤ የሚቀልጥም ያጋጥማል።

በታሸጉ ምግቦች ላይም መጠነኛ የሆኑ ጭማሬዎች መኖራቸውን በሾላ ገበያ ባደረግነው ቆይታ የታዘብን ሲሆን፣ በልብስና በጫማ ምርቶች ላይ ግን በመርካቶና ሾላ ገበያ ብዙ የሚባል ጭማሬ አለመኖሩን ታዝበናል።

የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት
የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት (inflation) የከተሜውን ኑሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል። በቤት ኪራይ መወደድ፣ ምግብ ነክ ባልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ጣሪያ መንካትና በትራንስፖርት ችግር ዘወትር የሚቆዝመውና ብቻውን እያወራ የሚጓዘው ከተሜ የምግብ እህሎችን ዋጋ ጭማሪ ተቋቁሞ የሚኖር አይመስልም። እንኳንስ አንድ ኩንታል ጤፍ ሦስት ሺሕ ብር ሸምቶ ቀድሞውንም መንገዳገድ ከጀመረ ሰነባብቷል።

ባሳለፍነው መጋቢት/2019 ወርም የማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረት፣ የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ባሳደረው ተጽዕኖ ሳቢያ ጠቅላላ ግሽበቱ ወደ 11 ነጥብ 1 በመቶ እንዲያሻቅብ አድርጎታል። ይህ ደግሞ ባለፉት አምስት ወራት ከተመዘገቡት ከፍተኛው ነው። የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ከሌሎቹ ከፍ ብሎ መታየቱ ደግሞ አዝማሚያው አደገኛ መሆኑን አመላካች ነው። ምክንያቱ ደግሞ አገሪቱ የምትመራበት የፖሊሲ ማዕቀፍ ግብርና ተኮር መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል የተሰማራበት የሥራ መስክም በመሆኑ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ሃቢስ ጌታቸው በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት ሊመዘገብበት ይገባ ነበር ይላሉ።

በእርግጥ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተንገታገተችና በውጭ ንግድ ሚዛኑ ማሽቆልቆል አጣብቂኝ ውስጥ ላለችው ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች ዋጋም በድንገት ላለማደጉ እርግጠኞች አይደለንም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ሃቢስ ግብርናው ለኢትዮጵያ ጠቅላላ ምጣኔ ሀብት ዕድገት 33 በመቶ ድርሻ አለው፤ 80 በመቶ የሚሆነውን የሰው ኃይልም ቀጥሯል ሲሉ ያወሳሉ። ለምጣኔ ሀብቱ ዕድገት ይህን ያህል አስተዋጽዖ ባለው መስክ ላይ የሚታይ ችግር በጠቅላላው ምጣኔ ሀብት ላይም አደገኛ ተጽዕኖ ያመጣል ሲሉ ስጋታቸውን ያነሳሉ።

በምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት በቂ አቅርቦት ባለመኖሩ እንደሆነ የሚገልጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ታደለ ፈረደ (ዶ/ር)፣ በአቅርቦት ላይ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሰራቱ፣ የፍላጎት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ፣ የሕዝብ ቁጥር እያደገ በመሔዱና የምግብ ሥርዓቱ መልክ የሌለው በመሆኑ የዋጋ ንረቱ እንዲታይ ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ።

ሌላው የመንግሥት ስህተት በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ከውጭ መግባታቸው እንደሆነ የሚያስረዱት ታደለ በርካታ ሸቀጦች በአገር ውስጥ ምርት እንዲተኩ ባለመደረጋቸው አገሪቷን ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በሌላ በኩል፤ የአገሪቱን 70 በመቶ ያህል ሕዝብ የወር ገቢው ከ1 ሺሕ ብር በታች በሆነበት ሁኔታና በግጭትና መፈናቀል ምክንያት ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለዕለት ደራሽ የምግብ እርዳታ በተጋለጡበት ጊዜ በምግብ ዋጋ ላይ የሚታይ ማናቸውም ጭማሪ አገርና ሕዝብን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል የሚሉት ሃቢስ፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ንረት አምራች የሚባለው የገጠሩ ነዋሪ የከፋ ጉዳት አይደርስበትም ተብሎ ቢገመትም፣ የገቢ መጠኑ ባለበት ዳዴ እያለ ላስቸገረው ከተሜ ግን ፈታኝ መሆኑ አያጠያይቅም ይላሉ። የከተሞች መስፋፋት ለአንድ አገር ዕድገት የሚያበረክቱት ጉልህ ሚና ባይካድም አስፈላጊውን ሥራ የሚፈጥሩና የከተሜውን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ ነገሮች አብረው ካልተሟሉ ጠቀሜታቸው ያን ያህል ነው ሲሉም ያክላሉ።

ለዚህም ነው ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ጫናዎች ቅድሚያ ከተሜውን ገፈት ቀማሽ የሚያደርጉት ይላሉ ሃቢስ። ችግሩ በዚህ ከቀጠለና መንግሥት አፋጣኝ እርምጃዎችን ካልወሰደ ችግሩ የኅብረተሰቡን ኑሮ ከማቃወስ ባሻገር የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ክፉኛ ሊያንገራግጨው ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። ይህን ለማለት የሚያስደፍረው ደግሞ በተከታታይ ዓመታት እንደታዘብነው የሸቀጦች ዋጋ አንዴ ጭማሪ ካሳየ ያንኑ መነሻ (baseline) አድርጎ በጭማሪው ሲቀጥል እንጅ በመኸር ወቅትም ቢሆን የዋጋ ቅናሽ አይስተዋልም።

ከትራኩ እየወጣን ይመስለኛል የሚሉት ታደለ ትክክለኛ የምጣኔ ሃብት ፍኖተ ካርታ ዘርግተን መንቀሳቀስ ካልተቻለ አሁን ካለው የባሰ ነገር ሊመጣ እንደሚችል ያሳስባሉ።

(ዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄት)
እንግዲህ በኑሮ ውድነት ፈተናና በዋጋ ግሽበት የሚጨፈለቀው በዋናነት ይህ ዓይነቱ ሕዝብ ነው። በተለይ አዲስ አበባ በየዕለቱ ከሦስት ዶላር በታች ከሚያገኘው ብዙኀኑ ሕዝብ አንስቶ ሞልቶት ተርፎት መጣያ እስካጣው ድረስ የሚገኝባት መሆኗ የደሃውን ጭንቅ ያብሰዋል። ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት ʻበድጎማʼ የሚያቀርባቸው ሸቀጦች (ዘይት፣ ስኳር፣ ዱቄት) ቢኖሩም፣ በደካማ የሸማቾች ማኀበራት ሱቆች የተዝረከረከ አሠራር የታለመላቸውን ያህል አልሆኑም ያሉት ሃቢስ ችግሩን ለመቅረፍ የማኅበራቱ ሚና እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ያስረዳሉ።

ከሁሉ በላይ በእህል (ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎ…) ጥራጥሬ (ምስር፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሽንብራ …) ማጣፊጫዎች (በርበሬ፣ ቅማማ ቅመም …) ላይ እየታየ ያለው ሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ ከልካይ ያጣ የፈረስ ግልቢያ ሆኗል። እንኳንስ የመንግሥት ድጎማና ማረጋጊያ ይቅርና በአምራቹም ሆነ መሀል ላይ ባለው ሕገወጥ ደላላ አዕምሮ ውስጥ ʻሰብዓዊነትʼ የመንጠፉ ማሳያ ነው።
ዛሬ በአዲስ አበባ ከዕለት ወደ ዕለት የሚታየው ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት፣ የምግብ እህልና የሸቀጦች እጥረት ብቻ ሆኗል። ለዚህ አባባል ማሳያው ከሰሞኑ በሽንኩርት፣ በድንች፣ በቲማቲም፣ ወዘተ ዋጋ ላይ ገባ ወጣ እያለ እስከ 150 በመቶ ጭማሪ መከሰቱና አልወርድም ብሎ መሰቀሉ ነው። የዛሬ ሦስት ዓመት ተመሳሳይ ጭማሪ ካሳየ በኋላ ሊመለስ ያልቻለው በአሁኑ ወቅት በኪሎ እስከ 160 ብር የሚሸጠው የበርበሬ ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያላት መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የኹለት ወር ከስድስት ቀን ፍላጎትን የሚሸፍን እንደሆነና ይህም ለመድኀኒትና ለነዳጅ የሚውል እንደሆነ ከሳምንታት በፊት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ገልፀው ነበር።

በርግጥ፤ አገሪቱ በመደበኛ ሁኔታ ባለፉት ዓመታት ከዚህ የሚበልጥ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ኖሯት አያውቅም። “ያለው መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለኹለት ወር ብቻ የሚሆነው ማለት ያለውን አሟጠን እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን ማለት አይደለም” በማለት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) በተጠቀሰው ኹለት ወር እና ጥቂት ቀናት ጊዜ ውስጥ ከውጭ በሚላክ ገንዘብ፣ በእርዳታ፣ በብድርና በወጪ ንግድም የሚመጣ የውጭ ምንዛሬ ይኖራል ይላሉ።

ከውጭ እቃዎችን ለማስገባት የሚውል መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አስፈላጊ ቢሆንም አገሪቱ ለኹለት ወራትና ጥቂት ቀናት የሚሆን ነው ያላት ማለት የሚያሸብር ነገር እንዳልሆነ ያስረግጣሉ። ምንም እንኳን በተፃፈ ሕግ ባይሆንም እንደ አሰራር የዓለም የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ አገራት ከሦስት እስከ ስድስት ወር መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲኖራቸው ይመክራል። ያነጋገርናቸው ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ታደለ የሦስት ወር ክምችት በቂ ሊባል የሚችል ሲሆን ብዙ ጊዜ ችግሮች ሊከሰቱ የሚችሉት መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ከሦስት ወር በታች ሲሆን እንደሆነ ይገልፃሉ።

- ይከተሉን -Social Media

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት የሦስት ወር ክምችት መያዝ ጥሩ እንደሆነ ቢመከርም መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሦስት ወር ያነሰ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ይዞ መገኘትን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተላመደው እንጂ እንግዳው አለመሆኑን ነው። በአስቸጋሪ፤ በመደበኛ ሁኔታም እውነታው ይህው ነው ይላሉ።

ከኤክስፖርት የሚገኘው ገቢ በጣም ውስን በመሆኑ፣ ከውጭ ከሚላክ ገንዘብ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬም የተሻሻለው በቅርብ በመሆኑና አሁንም ብዙው በጥቁር ገበያ የሚተላለፍ በመሆኑ፣ ከአገልግሎት ሰጪ ዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የተሻሻለው ገና በቅርቡ በመሆኑ የመጠባበቂያ ክምችቱ ሊያድግ እንዳልቻለም ያስረዳሉ።
ነገር ግን የአሁኑን የአገሪቱ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሬ ክምችት አነስተኛ መሆንን የተለየ የሚያደርገው የውጭ እዳ ጫና የበረታበት ጊዜ ላይ መሆኑ እንደሆነ ይገልፃሉ። ስለዚህም በዚህ የእዳ ጫና ምክንያት መጠባበቂያው ሳይነካ ከውጭ ለሚገቡ እቃዎች የሚቀርብ የውጭ ምንዛሬም ከፍተኛ እጥረት አለ። ይህ ከዚህ ቀደምም ሞልቶም አያውቅም።

መጠባበቂያ በዓለም አቀፍ ገበያ ባልተጠበቀ መልኩ የነገሮች ዋጋ ሲንር፤ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ ሳይታሰብ ቢጨምር ወይም በአገራት መካከል በተፈጠረ ግጭት የእቃዎች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሲጨምር የሚፈጠር ችግርን ለመቋቋም የሚውል ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለኢንቨስተሮች መተማመኛም ነው።

ነገር ግን፤ ከመጠባበቂያው ባሻገር በአገሪቷ ለባለፉት ዐሥር ዓመታት የቆየው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ጭማሪ ለማሳየታቸው ምክንያት ሆኗል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በባለፈው ወር አጠቃላይ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች የዋጋ ግሽበት 11 ነጥብ 2 በመቶ ተመዝግቧል። ይህ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፤ እያንዳንዱ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች የ11 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ማለት ነው። ልብስ እና ጫማ የ19 ነጥብ 7 በመቶ እና 23 በመቶ ዋጋ ጭማሪ በማሳየት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያስመዘገቡ ምርቶች ሆነዋል።

የትምህርት ቤት ክፍያ
ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች በአገሪቱ ያላቸው የትምህርት አገልግሎት ድርሻ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለአንድ ተማሪ የሚጠይቁት ወርኃዊ ወይም ተርም (2 ወር ከ15) ክፍያ ቀላል የሚባል አይደለም። በዓመት ወይም በኹለት ዓመት አንዴ ከ10 በመቶ እስከ 50 በመቶ እንዲሁም ከዚህ በላይ ሲጨምሩም ይስተዋላሉ። አንድ መካከለኛ የግል ትምህርት ቤት በወር ከ1250-1300 ሲያስከፍል ገቢያቸው ከፍተኛ የሆነ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ደግሞ ለልጆቻቸው ከ2 ሺሕ ብር እንስቶ 16 ሺሕ ብር በየወር ለትምህርት ቤቶች ይከፍላሉ።

የኑሮ ውድነቱን ከሚያንሩት ምክንያቶች መካከልም አንዱ ይኸው የትምህርት ቤት ጭማሪ ነው ሲሉ ዜጎች ያነሳሉ። ይህ ወላጆችን በተደጋጋሚ ለመንግሥት አቤት እንዲሉ ያደረገ ቢሆንም፣ ትምህርት ቤቶች ወርኃዊ ክፍያ ላይ የሚያደርጉትን ጭማሪ ሊያለዝብ አልቻለም። በዚህም ሳቢያ የትምህርት ቤት ዋጋ ጭማሪው ሌላው የኑሮ ውድነትን አብሶታል።

በየዓመቱ አሊያም በየኹለት ወላጆች ለልጆቻቸው የሚጠየቁት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ራስ ምታት እንደሆነባቸው በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ ተደምጠዋል። አቤቱታዎችም በተለያዩ ጊዜያት ይሰማሉ። የግል ትምህርት ቤቶች ባለቤቶች በበኩላቸው ባገኟቸው መድረኮች ሁሉ የተማሪ ክፍያ በየጊዜው የሚጨምሩት አብዛኞቹ ተከራይተው የሚሠሩ በመሆናቸው፣ በደመወዝ ተወዳዳሪ ሆነው መምህራን ለማግኘትና የትምህርት ሥራ ወጪው ከባድ ስለሆነ ነው ይላሉ።

በመንግሥት ትምህርት ቤት በሚሰጠው ትምህርት ጥራት እንደማይተማመኑና ለዚህም ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ማስገባታቸውን የገለጹልን ወላጅ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ በየዓመቱ እየጨመረ ኪሳቸውን ቢፈታተነውም የቱንም ያህል ዋጋ ከፍለው ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ማስተማርን እንደሚመርጡ ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያታቸው በግል ትምህርት ቤት ከመንግሥት በተሻለ የልጆቹን የትምህርት አቀባበልና የሥነ ምግባር ሁኔታ በየቀኑ የሚለዋወጡበት የመምህሩና የወላጅ መዝገብ ማግኘት መቻላቸውን ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ወላጅ ለትምህርት ቤቱ ቀድሞ ሳያሳውቅ ተማሪው ቢቀር፣ የቤት ሥራ ባይሠራ፣ በባህሪው ላይ ትላንት ከነበረው ዛሬ ለውጥ ቢያሳይ፣ (በጎም መጥፎም) የግል ትምህርት ቤቶች ለወላጅ ማሳወቃቸው፣ ተማሪዎችንም ያለወላጅ ፈቃድ ከትምህርት ቤት ግቢ የማያስወጡ መሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ።

ክፍያው ሲታይ ግን ለወላጆች ከባድና የተጋነነ ነው። ወላጆች በደመወዛቸው ላይ ጭማሪ ሳያገኙ የተማሪዎች የወር ሒሳብ በየዓመቱ እየጨመረ መሔዱም፣ የቤት ውስጥ አኗኗርን እየጎዳው፣ ወላጆችንም ለጭንቅ እየዳረገ ይገኛል ይላሉ።
በየዓመቱ የሚደረግ የትምህር ቤት ክፍያ ጭማሪ ላይ መንግሥት ገደብ አያበጅም ወይ? ሲሉ የሚጠይቁት ቅሬታ አቅራቢ፣ በተለያዩ ጊዜያት ክፍለ ከተማና ትምህርት ቢሮ ድረስ በመሔድ ቢጠይቁም በነፃ ገበያ ትምህርት ቤቶችን ይህንን ያህል ብቻ አስከፍሉ ብሎ ማስገደድ እንደማይቻል ተገልጾላቸዋል።

እንደመፍትሔ
ሰይድ ኑሩ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እስካሁን የመጣንባቸውን አገሪቷ ያለፈችባቸው ሒደቶችና አፈጻጸሞች በመመርመርና ጉድለቶችን በመንቀስ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ እንዲሁም ፖሊሲዎችን መፈተሽ ባለ ሁለት አኀዝ ሆኖ መመዝገብ ከጀመረ ኹለት ዓመት ከግማሽ የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ተገቢ እንደሚሆን አውስተው፣ በተለይ በመዋቅራዊ ለውጥ ሒደት ውስጥ ከነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ባሻገር የሰው ኃይል፣ የቁሳዊ ካፒታል እና የቴክኖሎጂ አጠቃላይ አገራዊ አቅሞቻችንን መፈተሽ እንዳለበት ይናገራሉ።

ምጣኔ ሀብቱ የሚመራው በተወዳዳሪነት በሚዘልቅ አቅም ወይም መሬት ባልያዘ አቀባባይ የአገልግሎት ዘርፍ ስለመሆኑ መለየት አለበት። የአንድን አገር ምጣኔ ሀብት በዘላቂነት የሚያሳድገው ቁሳው ካፒታል በየትኛውም መንገድ ማከማቸት ስለተቻለ ሳይሆን ሀብቱን በፍጹም ተወዳዳሪነት፣ ቅልጥፍና ማምጣት በሚያስችሉ ዘርፎችና አግባቦች ማዋል ሲቻል ነውም ባይ ናቸው። ይህም ዋጋ ግሸበቱን ለመቆጣጠር ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።

በመጨረሻ በልማት ሒደት ውስጥ ወሳኙ ነገር ሥርዓታት ወይም ተቋማት መሆናቸውን የሚናገሩት ሰይድ መንግሥትንና ማኅበረሰብን ጨምሮ የሥርዓታት ወይም ተቋማት ለውጥ ከሌለ፣ ልማትና ምጣኔ ሀብቱን ዋጋ ግሽበትን በሚገባ መቆጣጠር ማሰብ አይቻልም።

ግብርናው በራሱ የኢንዱስትሪውን ግብዓት ይፈልጋል የሚሉት ሃቢስ በበኩላቸው፣ ግብርናው ዘመናዊ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ምርት ያስፈልገዋል ሲሉ ያወሳሉ። ግብርናው ገበያ እንዲያገኝ እንደገና ኢንዱስትሪውን ይፈልጋል ይላሉ። “ሰሊጥ እያመረትን የዘይት ችግር አለብን። ኢንዱስትሪውን ተጠቅመን ስለማናመርተው እኛው የላክነው ሰሊጥ ዘይት ሆኖ እንደገና ይመጣልናል። የእኛ ገበሬ ሰሊጥ አምርቶ ወደ ቻይና ይልካል፤ እኛ ደግሞ የረጋ ዘይት ከውጭ እናስመጣለን። ይህ መሰረታዊ ችግር ነው። እናምርተው አላልንም እንግዛው እንጂ፤ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት መደረግ አለበት።

የተጀመሩ ብዙ ነገሮች ነበሩ፣ እየቀሩ ሄዱ እንጂ” ሲሉ ባጠቃላይ የአገራችንን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ እነዚህ መታየት እንዳለባቸው ሃቢስ ይመክራሉ።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ከውጪ የምናስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት እንችላለን የሚሉት ታደለ በበኩላቸው፣ ቅጥ ያጣ የምግብ ስርዓት ባለበት ሁኔታ ችግሮችን መቅረፍ የማይታሰብ በመሆኑ ትክክለኛውን የምጣኔ ሀብት ፍኖተ ካርታ በመዘርጋት ችግሩን መቅረፍ አዋጪ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች