ሺዎችን የጨረሰው የአእዋፍት ወረርሽኝ ወደ ሰዎች እንዳይተላለፍ ተሰግቷል

0
815

በደቡብ ክልል በሐመር ወረዳ ዘመርጋ በተባለ ቀበሌ ውስጥ በአእዋፋቶች ላይ በተከሰተ ወረርሽን ምክንያት በወንዝ ዳርቻዎችና ኩሬዎች አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ አእዋፋት ሞተው ተገኙ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት፣ ወረርሽኙ ባለፈው የመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በወረዳው ከተከሰተ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ አጎራባች ቀበሌዎችና ወረዳዎች እየተዛመተ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የፌደራል ጤና ጥበቃና የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የቅርብ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝና የሞቱ አእዋፋት ናሙናዎች በአዲስ አበባ ሰበታ በሚገኘው የእንስሳ ጤና ምርምር ላብራቶሪ ተልከው ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል።

በቀጣይ የናሙናው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታዎች መከላከልና ጤና ማጎልበት የስራ ሂደት አስተባባሪ ታምራት አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በወረርሽኝ መልክ የተከሰተው በሽታ ከዚህ በፊት በአካባቢው ያልተለመደና አዲስ መሆኑን የጠቆሙት ታምራት፣ በተለይም በተለምዶ ዋኔ በመባል የሚታወቁ የእርግብ ዝርያዎችን የማጥቃት አቅሙ የበረታ ሆኖ እንደሚስተዋል ተናግረዋል። አእዋፋቶቹን ለሞት የሚዳርገው ይህ ወረርሽኝ አስከአሁን በሰዎች ላይ ያደረሰው ተመሳሳይ ምልክት አለመኖሩን አክለው ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ወረርሽኙ ምናልባት ወደ ሰዎች የመተላለፍ ሁኔታውን ለመቆጣጣር በሁለቱም ወረዳዎች በሚገኙ የጤና ተቋማት አማካኝነት የቅርብ ክትትልና ቅኝት እየተደረገ እንደሚገኝ ታምራት ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ኢትዮጲያ 25 የሚሆኑ አእዋፋትን በብርቅዬነት ያስመዘገበች ሲሆን በአጠቃላይ በሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኙት 860 አይነት የአእዋፍ ዝርያዎች ውስጥ 596ቱ በቋሚነት የሚነቦሩ ሲሆን 224ቱ ወቅትን ተከትለው የሚመጡ ናቸው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ጥበቃ ሊደረግባቸው የሚገቡት 31 ሲሆኑ ኢትዮፒያም ደህንነታቸውን የመጠበቅ ግዴታም አለባት፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here