ቀረጥ ያልከፈለው ድርጅት በጤና ሚኒስቴር ይሁንታ ዕቃው እንዲወጣለት ተደረገ

0
646

የሕክምና መሣሪያ አስመጪው ዶክ ኔት ትሬዲንግ አራት ሚሊዮን ብር የሚሆን ቀረጥ መክፈል እያለበት ከጤና ሚኒስቴር በተፃፈ ደብዳቤ ዕቃው ከጉምሩክ እንዲወጣ መደረጉ ታወቀ። ዶክ ኔት ትሬዲንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ (ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል) ጋር በገባው ውል መሰረት ለሥነ ደዌ ምርመራ ʻፓቶሎጂʼ መሣሪያ ለማስመጣት ውል የገባ ቢሆንም ቀረጥ ሳይከፍል በመቅረቱ የጉምሩክ ኮሚሽን እቃዎችን እንዲወረሱ አድርጎ እንደነበር አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ለመረዳት ተችሏል።

በዚህም መሰረት በአራት የተለያዩ ምዕራፎች መግባት የነበረበት የሕክምና መሣሪያ አራተኛው እና ዋነኛው ክፍል ለውል ሰጪ ማለትም ለሕክምና ሳይንስ ኮሌጁ ሳይደርስ መግባት ከነበረበት አንድ ዓመት መዘግየቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳዊት ወንድምአገኝ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሥራ አስፈፃሚው ጨምረው እንደገለፁት ከዓመት በፊት በግንቦት ወር 2010 ላይ መሣሪያው ገብቶ መጠናቀቂያ ጊዜው ማለፉን የሚያስታውስ ደብዳቤ መፃፉን አስታውሰው ከአስመጪ ድርጅቱ ያገኙት ምላሽ ግን “ቀረጥ ክፈሉልን” የሚል መሆኑን አስረድተዋል።

በ2009 ግንቦት ወር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የግዥ ውል ሲፈረም አስመጪው ድርጅት ዶክ ኔት ዕቃዎችን በሚመለከት ከማስመጣት ጀምሮ እስከ ማስረከብ ባለው ሒደት ውስጥ ያሉትን የቀረጥና ተዛማጅ ክፍያዎችን የመክፈል ግዴታ እንዳለበት በውሉ ላይ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ ከዋና ሥራ አስፈፃሚው ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው ከዶክ ኔት ትሬዲንግ በተደጋጋሚ ሰዎች በመምጣት አራት ሚሊዮን የሚሆነውን ቀረጥ ውል ሰጪው እንዲከፍልላቸው ድርድር ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን ወደ ግማሽም ዝቅ በማለት ኹለት ሚሊዮን እንዲከፍልም ለማግባባት ሞክረዋል። እነዚህ ሁሉ ድርድሮች ፍሬ ባለማፍራታቸው እና በጉምሩክ በኩል ቀረጥ ሳይከፈል ቀነ ገደቡ በማለፉ እንዲወረስ ተደርጓል። ይህንም ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር በደብዳቤ ዕቃው እንዲወጣ ካደረገ በኋላ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል እንዲቀመጥ አድርጓል።

ነገር ግን ዶክተር ዳዊት እንደሚሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዶክ ኔቶች ዕቃውን በምን አግባብ እንዳገኙት ባልታወቀበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ሀሰተኛ የሆነ የመረከቢያ ቅፅ (ሞዴል 19) በማዘጋጀት እንድንረከባቸው እየወተወቱ እንደሚገኙና አሁን ያለው አስተዳደር ዕቃውን ለመረከብ ሕጋዊነቱን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት በማመኑ መልሰው እንዲወስዱ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል። የመሣሪያው ጠቅላላ ዋጋ 44 ሚሊዮን ብር እንደሆነና 30 በመቶ አስመጪው ድርጅት ቅድሚያ እንደተከፈለው የታወቀ ሲሆን በጊዜ ባለማድረሱ ጋር ተያይዞም ዶክኔት 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እንዳይከፈለው ተደርጓል።

ስለ ጉዳዩ በኢትዮጵያ የተመዘገበው የዶክ ኔት ትሬዲንግ ባለንብረት የሆኑት ዶክተር ኪዳኔ ኪሮስ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ድርጅታቸው ዶክ ኔት የዓለም ዐቀፉ ዶክ ኔት ወኪል እንጂ በግዥ ሒደቱ ላይ በቀጥታ ውል አለመፈፀሙን ተናግረው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዱባይ ከሚገኘው ዓለም ዐቀፉ ዶክ ኔት ጋር በቀጥታ መዋዋሉን ተናግረዋል። ስለተፈጠረው የዕቃ መወረስም የእሳቸው ድርጅት ምንም እንደማይመለከተው እና የኢትዮጵያው ዶክ ኔት መሣሪያውን ለመግጠም ሠራተኞችን ለማቅረብ ብቻ እንደተስማማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በመቀጠልም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ወደ ተባሉት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አምርታ ለማጣራት ያደረገችው ሙከራ እንደሚያመለክተው፤ ጤና ሚኒስቴር ስለ ጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌለው ተናግሯል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የመንግሥት ግዢ እና ንብረት አስተዳደር የሕክምና እና የጦር መሣሪያ የመግዛት ሥልጣን እንደሌለው ለአዲስ ማለዳ ቢገልፅም ግዥውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማካሔድ እንደሚችል የሚገልፅ ደብዳቤ መፃፉን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ያልተከፈልው ቀረጥ በሚመለከት አዲስ ማለዳ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ጉምሩክ ኮሚሽን ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here