አረና በአባላቱ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ክስ መሰረተ

0
902

• ህውሓት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነዱን እያከበረ አይደለም ብለዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሚያዚያ 6፣ 2011 ቀን አካባቢን ለማፅዳት ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው በመቀሌ ከተማ ኵሃ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፅዳት ስራ በሚሰሩ ወጣቶች እና የፓርቲው አባላት ላይ ጥቃት አድርሰዋል ባሏቸው የወረዳው አመራሮች ላይ ዓረና (አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ) ክስ መመስረቱን አስታወቀ፡፡

የፓርቲዎችን ግንኙነት የሚገዛው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ፓርቲዎቹ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አለመግባባት ሲኖርና የቃል ኪዳን ሰነዱ ተጥሷል የሚል አቤቱታ ሲቀርብም በኮሚቴ እንዲጣራ ያደርጋል ቢልም ይህንን ሕግ ህውሓት ሊተገብረው ፈቃደኛ አይደለም ሲሉ የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ገብሩ አስራት ይናገራሉ። በትግራይ አምባገነናዊ ስርዓት መስፋፋቱንና ሁሉንም ነገር በኃይል የማድረግ እንቅስቃሴዎች ዕለት ተዐለት እየተበራከቱ መምጣታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ በነበሩበት ወቅት በኵሃ ወጣቶችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ ፖሊስ ባደረሰበቸው ድብደባ እና ህገወጥ እስራት ተቃዋሚው ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ዴሞክራሲ የዓረናው ሊቀ መንበር አብርሃ ደስታ ተቃውመውታል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ፓርቲው ይህንን ፈጽመዋል ባላቸው የወረዳና ዞን አመራሮች ላይ ክስ መመስረቱን የነገሩን ገብሩ፣ ጠበቃ ቀጥረው ወደ ክስ መግባታቸውንና እስከመጨረሻው ድረስ ጉዳዩን ተከታትለው የሕግ ውሳኔ ማግኘት እንደሚፈልጉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡

ህውሓት በትግራይ ክልል ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ መሆኑን ያስታወቁት ገብሩ፣ በፍርሃት ስሜት ሕዝቡን ወደባሰ አፈና ውስጥ እየከተተው በመሆኑ አረና ለትግራይ ሕዝብ ነጻነት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚታገል አክለው ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ህዝብ ባጠቃላይ፣ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ በህወሓት አመራር እየተወሰደ ያለው ጭካኔ የተሞላው የድብደባ፣ የእስር እና የግድያ እርምጃዎች የዴሞክራሲና የአንድነት ትግሉን ያጠነክረዋል እንጂ በምንም መንገድ ሊገታው አይችልም ሲሉ ገብሩ ገልፀዋል።

በህወሓት ያለ አግባብ በእስር ቤት እንዲቆዩ የተደረጉትን ወጣቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ በፖሊስ ድብደባ ለተጎዱትም ህክምና እንዲደረግላቸውና ተገቢ ካሳ እንዲከፍላቸው፣ እንዲሁም ይህንን አሰቃቂ ግፍ የፈጸሙትን በህግ እንዲጠየቁ እንጠይቃለን ብለዋል።

ቀደም ሲል የህውሓትን አመራሮች ብኩንነትና አቅመ ቢስነት በፖሊሲ ደረጃ ሲተቹ በነበሩ እንደነ ነቢዩ ስሑል፣ ፅጋቡ ቆባዕ /የዓረና አባል/ ላይ አካላዊ ጉዳት አድርሰውባቸው ወጣቶቹ ዓይደር ሆስፒታል ገብተው በመታከም ላይ እንደሚገኙ እና በዛው እለት ተደብድበው ጉዳት የደረሰባቸው፣ ሽዋዓለም ለማን ጨምሮ ሌሎች 21 ወጣቶች እቤታቸው ተኝተው በማገገም ላይ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ በሳምንት እትሟ መዘገቧ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here