የፓልም ዘይት አቅርቦት ለተፎካካሪ ኩባንያዎች ሊፈቀድ ነው

0
488
  • 60 በመቶ የሚሆነውን የዘይት ፍጆታ የሚያስመጡት ዘጠኝ ድርጅቶች ብቻ ነበሩ

በአሁኑ ሰዓት ከ60 በመቶ በላይ የአገሪቷን የዘይት ፍጆታ በማቅረብ ላይ ከሚገኙት አምስት የግል ኩባንያዎችና አራት ኢንዶውመንቶች በተጨማሪ ሌሎች አቅራቢዎች እንዲሳተፉ ለማድረግ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አዲስ አሰራር መዘርጋቱን አስታወቀ።

ከሐምሌ 2008 አንስቶ በአስመጪነት ፈቃድ ያላቸው እነዚህ ድርጅቶች በየወሩ ከ40 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት እያቀረቡ የሚገኝ ሲሆን በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ድርጅቶች ካሉ ተቀብሎ ፈቃድ እንደሚሰጥ ሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

ገበያ እንዲያረጋጉ በሚል የተመረጡት ድርጅቶቹ ለባለፉት ሦስት ዓመታት 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ያቀረቡ ሲሆን ፍላጎትና በቂ የገንዘብ አቅም ያላቸውን ድርጅቶች ለማሳተፍ መታቀዱን የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንድሙ ፍላጎቴ ገልፀዋል።

በአሁኑ ሰዓት እያቀረቡ የሚገኙት አልሳም፣ አህፋ፣ ደብሊው ኤ፣ ሃማሬሳ እና በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ በአሁኑ ሰዓት እያቀረቡ የሚገኙት የግል ድርጅቶች ሲሆኑ በሥልጣን ላይ የሚገኙት የኢሕአዴግ ግንባሮች የተያዙ እንደ ጉና፣ ቢፍቱ፣ አምባሰል እና ዲንሾ የተባሉት ኢንደውመንቶች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

የግል ባለሀብቶቹ ወደ አቅርቦት እና ስርጭት ስርዓቱ ሲገቡ መንግሥት ያስቀመጠው ዓላማ የነበረው የምግብ ዘይት የማምረቻ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ እና ወደ ማምረት በመግባት በዘላቂነት አገሪቱ ከውጪ የምታስገባውን የፓልም ምግብ ዘይት በማስቀረት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የነበረ ቢሆንም አንዳቸውም ይህንን ማሳካት አልቻሉም።

ይሁን እንጂ አቅራቢዎች በመንግሥት በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው በራሳቸው ፓልም የምግብ ዘይት ለአገሪቷ እያቀረቡ ይገኛሉ። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የአገር ውስጥ አምራቾች በማኅበራቸው በኩል ያልተገባና ፍትሐዊ አይደለም በማለት ለድርጀቶቹ የተሰጠውን ልዩ ጥቅም ተቃውመዋል።

በተጨማሪ አቅራቢዎቹ በራሳቸው በቀጥታ ምርቱን የሚያስመጡት ከመንግስት ዶላር ተበድረው በመሆኑ በሚኖረው የዶላር እጥረትና በአቅራቢዎች አፈጻጸም ችግር ምክንያት እንዲሁም በክልሎች ያሉ የተቆጣጣሪ አካላት በሚፈለገው ልክ ክትትልና ቁጥጥር ባለማድረጋቸው በተለያዩ ጊዜያት የምርቱ አቅርቦት መቆራረጥ ችግር የተከሰቱባቸው ጊዜያቶችም እንደነበሩ በቀድሞ ንግድ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት የተደረገ ጥናት ያሳያል።

የግል ባለሀብቱና ኢንዶውመንቶች እንዲያስገቡ የዛሬ ሦስት ዓመት በተደረግበት ወቅት የዓለም ፓልም የምግብ ዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ስለነበረ ከ2008-2009 በምርቱ ላይ ምንም ዓይነት ድጎማ አልተደረገም ነበር። ነገር ግን በጥቅምት 2010 በተደረገው የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት አቅራቢዎቹ ከመንግሥት ዶላር የሚገዙበት ዋጋ በ15 በመቶ ስለጨመረና ከጭማሪው ጋር ተያይዞ፤ የፓልም የምግብ ዘይት ለኅብረተሰቡ የሚቀርብበት ዋጋ ስላልጨመረ አቅራቢዎቹ ለኪሳራ እንዳይዳረጉ በውጭ ምንዛሪ ለውጡ ምክንያት እያወጡ ያሉትን የገንዘብ ልዩነት በሦስት ዙር ውስጥ 825 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር መንግሥት ለዘጠኙም አቅራቢዎች ከፍሏል።

በተጨማሪ መንግሥት በሊትር 0.36 ሳንቲም ድጎማ ማለትም በየወሩ 14 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ድጎማ ያደርግ የነበረ ሲሆን ከባለፈው ወር አንስቶ ተግባራዊ እንዳይደረግ መወሰኑ ታውቋል። ይህንን ወሳኔ ሚኒስቴሩ የወሰነው ፓልም ዘይት በዓለም ገበያ ቅናሽ ማሳየቱን ተከትሎ እንደሆነ ወንድሙ ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here