የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ህልውና በገንዘብ እጥረት አደጋ ውስጥ ገባ

0
281

መንግስት 2100 ሜጋ ዋት እንዲያመነጭ አቅዶ በመገንባት ላይ የነበረው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በገንዘብ እጥረት በማጋጠሙ ግንባታው ከሚጠበቀው እጅግ ያነሰ አፈጻጻም ከማሳየት ባለፈ ለመቋረጥ የሚዳርግ ነው ተባለ። በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 21 ነጥብ 3 በመቶ መከናወን የቻለው ግንባታው፤ በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ደግሞ 34 ነጥብ 2 በመቶ ለማድረስ የታቀደ ቢሆንም በስምንት ወራት ውስጥ ግን መሰራት የተቻለው 10 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ መሆኑ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ተጠቁሟል።

በኃይል ማመንጫው ግንባታ ላይ የተጋረጠውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ መፍትሔዎችን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገሩ የሚታወስ ነው ። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት የገንዘብ እጥረቱ በመባባሱ ግንባታው ከመዘግየት ባለፈ ወደ መቆም መጠጋቱን ለማወቅ ተችሏል።

ጉዳዩን በሚመለከት በውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ፍሬህይወት ወልደሐና (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ የገንዘብ እጥረቱን ለመቅረፍ ሚኒስቴሩ የተለያዩ አማራጮችን እየተከተለ መሆኑን ይገልፃሉ።

አያይዘውም ፤ እንደመጀመሪያ አማራጭ የተወሰደው በመንግስትና በግል አጋርነት በመጠቀም ገንዘብ እጥረቱን መፍታት ነው። ፍሬህይወት በመቀጠልም እንደመፍትሔ የተቀመጠውን ሲናገሩ፤ ግንባታውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ሳሊኒ መሆኑን በመጥቀስ ወጪውን በሙሉ በሳሊኒ ወጪ እንዲሸፈን ማድረግና በተራዘመ ጊዜ ዕዳውን መክፈል እንደ አማራጭ መቀመጡን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሚኒስቴር ድኤታው ጨምረው እንደገለፁት በጉዳዩ ላይ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶት እየተሰራበት እንደሆነና በቅርቡ ችግሩ ተፈቶ መስመር የሚይዝበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አስታውቀዋል። በ2008 በጀት ዓመት ግንባታው የተጀመረው የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ አፈፃፀሙ 26 ነጥብ 2 በመቶ ላይ ይገኛል።

2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ እንደሚፈጅ በጀት የተያዘለት የኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተፋሰሱ 1 መቶ አስራ ዘጠኝ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ሚሸፍን ሲሆን ፤ ስድስት ቢሊዮን ሜትር ኩብ የመያዝ አቅም ያለው ግድብ እንደሚኖረው ታስቧል።

የውሃ ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኮይሻ በተጨማሪ የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫም በካሳ እና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት መዘግየቱን አስታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የገናሌ ዳዋ ግንባታው ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት የነበረበት ባለፈው አመት ቢሆንም እስካሁን ሥራ ባመጀመሩ ሚኒስቴሩ እንደትልቅ የአፈፃፀም ችግር እንደሚቆጥረው ተናግረው፤ በአሁኑ ሰዓት ግድቡ ውሃ መያዝ መጀሩንም አክሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here