ዘላቂው መፍትሔ ሁሉን አካታች ነው

0
752

‘ኦሮማራ’ በሚል ቅፅል ሥም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው የኦሮሞ እና አማራ ፖለቲከኞች ትብብር በጥቅሉ መልካም ነው። ነገር ግን በርካታ ጎዶሎዎች ያሉት እና ዘላቂ መፍትሔም የማያመጣ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብሔር ተኮር ትርክቶች ከተዋወቁ ወዲህ የበዳይ ተበዳይ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቶች አብሮ ለመሥራትም ይሁን አብሮ ለመኖር አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠራቸው አልቀረም። ባለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት በተለይ በኦሮሞ እና አማራ የፖለቲካ ልኂቃን መካከል ተቀራርቦ መሥራት ያልተቻለው ይህ ትርክት በፈጠረው መቃቃር ሳቢያ የተሻለች አገር ለመገንባት ባለመቻሉ ነበር።

ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ውስጥ ላለፉት አራት እና ሦስት ዓመታት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ለብዙ ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ ሰበብ ሲሆኑ ከርመው ጥቂት እፎይታ የተገኘው የኦሕዴድ አመራሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በሚል አባገዳዎችን ያካተተ ልዑካን ቡድን ይዘው ባሕር ዳር ከተማ ከአማራ ክልል አቻዎቻቸው ጋር መወያየት በመቻላቸው ነው። የኹለቱ ክልሎች የፖለቲካ ልኂቃን አለመተባበራቸው እና በፖለቲካዊ ትርክት ምክንያት መቃቃራቸው ለኹለቱም ሕዝቦች እንዳልጠቀመና ለሌሎች የመጨቆኛ መሣሪያ መሆኑን በመተማመን ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት ቃል ተግባብተዋል። በዚህም መሠረት የኹለቱ (በወቅቱ ኦሕዴድ እና ብአዴን ይባሉ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች) ልኂቃን ሥምምነት በኢሕአዴግ ውስጥ የለውጥ ማዕበል በማስነሳት ኢትዮጵያን ያልተጠበቀ የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዕድል ከድንጋጤ መሐል ፈንጥቆላታል።

ይሁን እንጂ የኹለቱ ፖለቲከኞች ትብብር እና ግንኙነት በተለያዩ የውስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻዎች ብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፏል። ፖለቲከኞች የራሳቸውን ጥቅም ከሕዝብ ጥቅም ጋር የተሳሰረ በማስመሰል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን በሰበኩበት አንደበት የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ሊቀሰቅሱበት ሲሞክሩ ተስተውሏል። በዚያ ላይ የኹለቱ ልኂቃን ኅብረት የተወሰነ ለውጥ ማምጣት በመቻላቸው ብቻ በደቡብ ክልል የነበሩት ሕዝባዊ አመፆች እንዳልነበሩ ሲዘነጉ እያስተዋልን ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚያዝያ ወር 2011 በተደረገ የሚኒስትሮች ሹም ሽር የኹለቱ ድርጅቶች (ኦዲፒ እና አዴፓ) ልኂቃን በሥልጣን ድልድሉ መሥማማት በመቻላቸው ምክንያት ለጊዜው መሳቢያ ውስጥ ተሸጉጦ ተዘንግቶ የነበረው ‘ኦሮማራ’ (የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት) እንዳዲስ ይቀነቀን ጀምሯል። ኹለቱ ክልሎች እርስበርስ እንዲሥማሙ መጣር፥ በተለይም ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ክልሎች እንደመሆናቸው ክፋት የለውም። በተለይም ደግሞ በኹለቱ ክልሎች ልኂቃን መካከል ከፍተኛ የትርክት መጣረስ በመኖሩ ምክንያት እነርሱ ሰላም ካላገኙ እና ሥምምነት ላይ ካልደረሱ በስተቀር ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የፖለቲካ ልኂቃን ሰላም ማግኘት ይቸገራሉ፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባቱን ሙከራም ያከብዱታል። ሆኖም የኹለቱ ቡድኖች ብቻ የፖለቲካ ዋና ተዋናይ አድርጎ መሣልም ይሁን የነርሱን ወዳጅነት ማጠናከር ለኢትዮጵያ ሙሉ የዴሞክራሲ ዋስትና አይሰጣትም። ይልቁንም ‘የብዙኀን አምባገነንነት’ በመባል ለሚታወቀው በድምፅ ብልጫ የአናሳዎች ጥቅም እና መብቶች የሚጨፈለቁበት ስርዓት ሊዳርግ ይችላል።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እየተባሉ የምናያቸው ዘመቻዎች መልካም ጎን ያላቸውን ያክል ደካማ መልዕክትም እንዳላቸው መዘ፡ንጋት የለበትም። አንዱ ችግር የልኂቃኑን መቃቃር ሕዝባዊ መቃቃር አሥመስሎ ማቅረብ ነው። በመሠረቱ የኢትዮጵያ ብዙኀን የሆኑት ገበሬዎች እንኳን መቃቃር ደረጃ ሊደርሱ ይቅርና የሚተዋወቁትም በሩቅ ነው ማለት ማጋነን አይሆንም።

ሌላኛው ችግር የልኂቃኑም መቃቃር ቢሆን በኦሮሞ እና አማራ ፖለቲከኞች መካከል ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም መካከል እንደሆነ ምሣሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። በአማራና ትግራይ ፖለቲከኞች፣ በኦሮሞ እና ሶማሊ ፖለቲከኞች መካከል ብልጭ ድርግም የሚሉ ጣት መቀሳሰሮች አሉ። ስለዚህ የሕዝብ ለሕዝብም ይሁን የፖለቲከኞች ለፖለቲከኞች ግንኙነት ካስፈለገ ሁሉንም ወገን አካታች እና አሳታፊ መሆን አለበት።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የረዥም ጊዜ ፈላጭ ቆራጮች ከኦሮሞ፣ አማራ እና ትግራይ የወጡ ፖለቲከኞች ናቸው። ሆኖም ኢትዮጵያ የ70 እና 80 ብሔረሰቦች አገር እንደመሆኗ መጠን፥ ሁሉም በአገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እና ውሳኔ ሰጪ የሚሆኑበት ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል። ከዚያ ወዲህ ያለው መፍትሔ መርጦ ማስተናገድ ስለሚሆን ዘላቂ ውጤት የማምጣት ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው። አዲስ ማለዳ፣ ይህ ችግር ከወዲሁ ተስተውሎ ጊዜያዊ እሳት ማጥፊያ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ልኂቃንን ያሳተፈ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሕዝብ ክፍሎች ያካተተ የመፍትሔ እና የሕዝብ ለሕዝብ እንዲሁም የፖለቲከኞች ግንኙነት እንዲመሠረት ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 25 ሚያዚያ 19 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here