በሐዋሳ በኃይል መቆራረጥ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ለመቀነስ መገደዳቸውን አስታወቁ

0
586

በሐዋሳ በኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሳቢያ የድርጅቶቻቸውን ሰራተኞች ለመቀነስ ከመገደዳቸውም በላይ የብድር ዕዳቸውን ለመክፈል መቸገራቸውን የድርጅት ባለቤቶችና ነዋሪዎች አስታወቁ።

የኃይል መቆራረጡ ምክንያት የመስመሮች እርጅና ነው የሚለው የደቡብ ክልል ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ነባር የኃይል መስመሮችን በአዲስ የመተካት ሥራ በማከናውን ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማው በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው ይገኛል። በከተማው አረብ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወጣቶች ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ በድንገት በሚከሰተው የኃይል መቆራረጥ መደበኛ ሥራቸውን ማከናወን አንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ከባንክ ባገኙት የገንዘብ ብድር በማኅበር ተደራጅተው በብረታ ብረት ሥራ ተሰማርተው የሚገኙት አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በኃይል መቆራረጥ ሳቢያ የማኅበሩን ሰራተኞች ለመቀነስ ከመገደዳቸውም በላይ የብድር ዕዳቸውን ለመክፈል መቸገራቸውን ተናግረዋል።

የክልሉ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የሥራ ኀላፊዎች፣ ነዋሪዎቹ ያቀረቡት ቅሬታ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠዋል። የኃይል መቆራረጡ እያጋጠመ የሚገኘው አነስተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች በማርጀታቸው ምክንያት መሆኑን የጽሕፍት ቤቱ የዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ ያዕቆብ ታሪኩ ገልጸዋል። የሐዋሳ ከተማ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የኤሌትሪክ ማሻሻያ ተግባራዊ እየተደረገባቸው ከሚገኙ ስምንት ከተሞች አንዱ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ነባር የኃይል መስመሮችን በአዲስ የመተካት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here