ለውጡ በነቢብ ወይስ በገቢር?

0
866

አንድ ዓመት ባስቆጠረው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር መንግሥት ሁለንተተናዊ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ሙከራዎች እያደረገ ስለመሆኑ በሰፊው ሲነገር ይሰማል። በተለይ ደግሞ ለውጡን ተከትሎ የፌደራል መሥሪያ ቤቶች የአርማ እና የሥራ ከባቢ ለውጥ ማድረጋቸው አንደምታው ምንድነው? እንዲሁም የተደረጉ የተቋማት መዋቅራዊ ለውጦችና አደረጃጀቶች ከሥራ ውጤታማነት አንፃር እንዴት ይታያሉ የሚሉትን ጉዳዮች በማንሳት የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በአካል የተወሰኑ ተቋማትን በመጎብኘት፣ የዘርፉን ባለሙያዎች በማናገርና ጥናታዊ ጽሑፎች በማገላበጥ የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀድሞ አጠራሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚባለው ተቋም አዘውትረው ለሚመላለሱ ተገልጋዮች አመቺ ካለመሆኑም በላይ ውስጥ ገብተው እስኪወጡ የሚቸኩሉበት፣ ለተገልጋዮች የማይጋብዝ መሥሪያ ቤት ነበር። ሕንፃው በቂ ብርሃን ያልነበረው፣ በወጉ ከሚሠራበት የማይሠራበት ጊዜ የሚያመዝን አሳንሰር ያለው፣ መኪና ለማቆም ወይም ካቆሙበት አስነስቶ ለመሔድ ቀላል የማይባል ትግል የሚጠይቅ ምቹ ያልሆነ የመኪና ማቆሚያ የነበረው፣ በአጠቃላይ ሰዎች ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ከመሔድ ይልቅ ለአለመሔድ ጥረት የሚያደርጉበት፣ የማይመርጡት ወይም ደግሞ ከሔዱ “መቼ ነው ቶሎ የምወጣው” ብለው የሚቸኩሉበት አንደኛው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነበር።

ለተቋሙ አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፤ ተረት ሆነዋል ማለት ይሻላል። በአሁኑ ሥያሜው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመባል የሚታወቀውና 2006/2007 በጀት ዓመት ላይ አዲስ ባስገነባውና በተለምዶ ተረት ሰፈር በሚባለው አካባቢ ወደሚገኘው ግርማ ሞገስ በተላበሰ ሕንፃና በተንጣለለ ግቢው ውስጥ ከትሟል።

ከአሉሚኒየም የተሠራው የሚኒስቴሩ ዋና በር ገና ሲያዩት ወደ አንድ መንግሥታዊ ተቋም እየገቡ ለመሆንዎ ይጠራጠራሉ። ወደ ቅጥር ጊቢው ገብተው ጉዳዩዎትን ለማስፈፀም የሚሔዱበትን ቢሮ ጠቋሚ ሰው ሳያሻዎት በቀጥታ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቴሊቪዥን መሳይ ሰሌዳ ላይ የሁሉም ቢሮዎች ዝርዝር እና አድራሻ ተገልፆ ያገኛሉ። አሁን የሚሔዱበትን ቢሮ ስንተኛ ፎቅ ላይ እንደሚገኝ አውቀዋል፥ ቀጣዩ ሥራዎት አሳንሰር መጠበቅ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ታዲያ የሚኒስቴሩን የቀድሞ ታሪኩን አስታውሰው ደረጃዎችን በእግርዎ ለመውጣት ሐሳብ ወደ አዕምሮዎ ሊመጣ ይችላል። ይሁንና እንደእንዝርት የሚሾሩት ኹለት አሳንሰሮች ከተፍ ይላሉ አማርጠው የገቡበት አሳንሰር የማሳቢያ ጊዜ ሳይሰጥዎ ያሰቡት ወለል ላይ ያደርስዎታል።
ለቢሮው ዋነኛ የብርሃን ምንጭ ሆኑት አምፖሎች የሚፈነጥቁት ብርሃን ቢሮዎች ከተቀቡት ነጭ ቀለም ጋር ተዳምሮ ቀልብን ይገዛል። በሰው ቁመት ልክ የተከለሉት የሠራተኞች የመሥሪያ ቦታ (ʻወርክ ስቴሽንʼ) ተገልጋዮች ቀለል ብሏቸው እንዲስተናገዱ የሚያደርግ ስሜትን የሚፈጥር ነው።

ሌላው የሥራ ከባቢ ለውጥ የተደረገበት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ነው። በጽሕፈት ቤቱ ለረጅም ዓመታት የሠሩ ሠራተኞች እንደሚሉት ጽሕፈት ቤቱ አሁን ያለበት ገጽታ ከቀድሞው ጋር ለንፅፅር የሚቀርብ አይደለም ይላሉ። አዲስ ማለዳ በሥፍራው ተዘዋውራ እንደታዘበችው ጽሕፈት ቤቱ የተወሰኑ ቢሮዎች ላይ እንደማሳያ የቀየራቸው የሥራ ከባቢዎች ምቹ መሆናቸውን በመገንዘቡ በሌሎች ተጨማሪ ቢሮዎች ላይም ተግባራዊ ለማድረግ እድሳት እየተካሔደ እንደሆነ ታውቋል። የታደሱት ቢሮዎች የሥራ ተነሳሽነትን የሚጨምርና ለተገልጋይም ምቾትን የሚጨምር ነው። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ የቢሮ ጉብኝት ባደረገችበት ወቅት አብዛኞቹ ሥራተኞችን በሥራ ሰዓት በሥራ ቦታቸው ላይ ማግኘት አልቻለችም። በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ከሥራ ከባቢ ለውጥ በተጨማሪ የመዋቅር ለውጥም ተደርጓል። ይህም ቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ይባል የነበረው አሁን ፕሬስ ሴክሬታሪ በሚል በአዲስ መዋቅር ወደ ሥራ ተገብቷል።

በአርማና በሥራ ከባቢ በኩል ማሻሻያ ከተደረገባቸው መሥሪያ ቤቶች የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴርን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን እንደማሳያ አነሳን እንጂ፣ ሌሎች ጥቂት የማይባሉት ሚኒስቴሮችም አንፃራዊ ለውጦች ተስተውሎባቸዋል።

የመሥሪያ ቤቶች የአርማ ለውጥ
ከመስከረም ወር 2011 ጀምሮ በርካታ የፌደራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አርማቸውን ቀይረው ወደ ሥራ መሠማራታቸው የሚታወቅ ነው። የአመራር ለውጡን ተከትሎ ወደ እንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የገባው የለውጥ ንፋስ አርማቸውን አስቀይሮ “በአዲስ መልክ ሥራ ጀምረናል” ዓይነት ነገር እንዲስተዋልባቸው ሆኗል። ከዚህ ቀደም በአንድ የፌዴራሉ የባንዲራ አርማ ኹሉም ሚኒስቴሮች ይተዳደሩ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ግን በግላቸው አርማቸውን አሠርተው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

“ሁሉም መሥሪያ ቤት የራሴ የሚለው መገለጫ አርማ ሊኖረው ይገባል” የሚለው ሚኪያስ ይትባረክ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የፕረስ ሴክሬታሪ ውስጥ ባልደረባ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የሚታወቅበትን አዲሱን አርማ ዲዛይን ያደረገውም እሱ ነው። ሚኪያስ እንደሚለው አሁን ያለው አርማ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከበርካታ አማራጮች መሐል መሆኑን ይናገራል። የትኛውም መሥሪያ ቤት አርማ ሲኖረው በመጀመሪያ ደረጃ የመሥሪያ ቤቱን ምንነት በግልጽ የሚናገር መሆኑ መታመን ይኖርበታል፤ ቀጥሎ ደግሞ በተገልጋዩ ወገን የሚኖረው አንደምታ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስገነዝባል።

ስለከዚህ ቀደሙ አንድ ወጥ ስለሆነው የአርማ ጉዳይ ሚኪያስ ሲናገር፣ ሁሉም ፌደራል ቢሮዎች በአንድ ኮከብ አርማ የተወሰኑ ከመሆናቸውም በላይ የእያንዳንዱ መሥሪያ ቤት ሥም እስካልተጻፈበት መለየት ከባድ እንደነበር ያስታውሳል። “ለምን ሰውን እዚህ ሁሉ ማምታታት ውስጥ እናስገባዋለን?” የሚለው ሚኪያስ ሁሉም ቢሮ የራሱ የሆነ አርማ እንዲኖረው መደረጉ ከመለያነቱም በተጨማሪ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከበላይ አካል ተፅዕኖ ነጻ መሆናቸውንም የሚያሳዩበት ነው ሲል ያብራራል።

የሚኒስቴሮች አርማ ለውጥ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ የሥራ ከባቢን ፅዱ እና አመቺ ማድረግ በሚል የቢሮ ገጽታቸውን እስከመቀየር፣ በአዳዲስ የቢሮ ዕቃዎች ማስዋብና ቀለም በመቀየር ነጭ ቀለም ቀብተዋል። ይህን በሚመለከት ተቋማዊ መዋቅርና ባሕል (organizational structure and culture) ጥናት ሚያደርጉት ሁሴን መሐመድ አዲስ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር መጣር እጅግ የሚበረታታ ቢሆንም የአንድ ተቋም ውድቀትና ትንሣኤ በእያንዳንዱ የመሥሪያ ቤቱ ባልደረባ አዕምሮ ውስጥ ነው ይላሉ። ስለዚህ ትልቅ ለውጥ የሚያሻው ጉዳይ ቢኖር የሠራተኞች የአስተሳሰብ ለውጥ እንጂ አርማና የቢሮን ቀለም መቀየር የትም አያደርስም በሚል በተቃራኒው ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

ሁሴን ሲቀጥሉ፣ ምናልባትም ለአርማና ለቢሮ ማስዋብ የወጣው ወጪ በሠራተኞች አቅም ግንባታ ላይ ቢውል በእርግጥም ለውጡ እውን የመሆን ዕድሉ ከፍ እንደሚል ያክላሉ። እንደ ሁሴን ሐሳብ ከዚህ ቀደም የነበረው የሥራ ከባቢ በሰዎች ምክንያት የተወሳሰበ እንጂ ቢሮዎች የራሳቸው አርማ አለመኖር ወይም ቢሮዎች አለመታደሳቸው ያመጣው እንዳልሆነ ነው።

“አዲሲቷ የተስፋ አድማስ”
የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ አዲስ ከሚታወቅበት አርማ በተጨማሪ “አዲሲቷ የተስፋ አድማስ” በሚል ኢትዮጵያን የሚገልጽበት መሪ ቃል እንዳለው የሚታወቅ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ታዲያ እውነትም ኢትዮጵያ አዲሲቷ ተስፋ አድማስ ናት የሚሉ ቢኖሩም ተቃውሟቸውን የሚያሰሙም አልታጡም።

በተለይ ደግሞ አዲሱ አመራር ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም ከሚሉት ወገን የሚሰነዘረው ትችት ጠንከር ያለ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት ይፋ የሚያደርጓቸው አሠራሮች ካለመተግበራቸው ጋር ተያይዞ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ የሚለው መፈክር ከወሬ የዘለለ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። ሕዝብ በተስፋ እጦት እየተሰቃየ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያን የተስፋ አድማስነት መናገር ትልቅ ምፀት መሆኑን የሚናገሩ ጠንካራ ተቺዎች መፈክር በመጻፍ የሚለወጥ ነገር እንደሌለ ሲናገሩ ይደመጣል።

“ኢትዮጵያ አዲሲቷ የተስፋ አድማስ” ስለሚለው ሐሳብ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ አዕምሮ ሐኪም ዶክተር እየሩሳሌም ሰለሞን “ተስፋ ትልቅ ነገር ነው። ሰው ተስፋውን ሲያጣ የመኖሩ ኅልውና እዛው ላይ እንደቆመ ይቆጠራል” ይላሉ። አያይዘውም ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምንም ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ነገን አሻግረን መልካሙን ቀን ተስፋ ካላደረግን የዛሬ ኅልውናችንም አደጋ ውስጥ እንደሆነ ያስረዳሉ። ዶክተር እየሩሳሌም እንደሚሉት አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የምንሰማቸው አገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የምንንቀሳቀሰው፣ ነገ ላይ አዲስ አገር፣ የተሻለች ምድርን እንደምንፈጥር ተስፋ በማድረግ እንጂ ያለተስፋ አይደለም።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ስለሚጠቀምበት መፈክርም ሲያብራሩ፣ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ዓይኑን ያነሳው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ወደ ቢሯቸው እንደሆነ ጠቁመው ከቢሮው ወደ ሰፊው ሕዝብ የሚደርሰው የትኛውም ነገር በተለይ ባለንበት ጊዜ ልብን በተስፋ የሚሞላና ነገ የተሻለች ኢትዮጵያን የሚያስናፍቅ መሆኑ በሕዝቡ ዘንድ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም ይላሉ።
በመቀጠልም የተለያዩ ሚኒስቴሮች አዲስ የሥራ ከባቢን ለመፍጠር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በተለመከተ ሙያዊ አስተያየታቸውን ሲያስቀምጡ “ሰው በተፈጥሮው መልካም እና ደስ የሚያሰኝ ነገርን መመልከት ይወዳል” ሲሉ ይጀምራሉ። ንፅሕናው በተጠበቀ አካባቢ መሥራት በራሱ ደስ የሚያሰኝ ከመሆኑም ባሻገር የሥራ ተነሳሽነትን በመጨመር ከፍተኛ የሥራ ክንውን እንዲኖር እንደሚያደርግ ይገልጻሉ። ወደ ሙያቸውም በመምጣትም በርካታ በሽተኞችን በተለይም በአዕምሮ ጭንቀት የሚሰቃዩ ሰዎችን ቤትና ቢሮዎቻቸውን የቀለም ምርጫ በማስተካከል የሚታከሙበት አጋጣሚም እንዳለ የሚናገሩት ዶክተር እየሩሳሌም፣ የሥራ ከባቢን በመቀየር ትልቅ ለውጥ እንደሚመጣ አልሸሸጉም።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ርቋል
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት በትዊተርና በፌስቡክ ገጾቹ የሚያከናውናቸውን ሥራዎችን በየጊዜው ለሕዝብ እንዲደርስ ማድረጉ ይታወቃል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እንቅስቃሴዎች፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ ፖለቲካዊ ዑደቶችን ጨምሮ ሳይዘገይ ለሕዝብ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ከመቼውም በላይ ርቆብናል የሚሉም አልታጡም። በዚህ በኩል ደግሞ ግንባር ቀደም አስተያየታቸውን የሚሰጡት የመገናኛ ብዙኀን አካላት ናቸው። የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ወደ ሕዝብ ስለደረሰ ቅርብ ሊመስል ቢችልም ለመገናኛ ብዙኀን ግን እጅግ የራቀበት ዘመን እንደሆነ ይገልጻሉ። አያይዘውም በማኅበራዊ ድረ ገጽ ከተነገረው እና ከሌሎች ጥቆማዎች በመነሳት ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በስልክም ሆነ በአካል ቀርቦ መረጃ ማግኘት የማይሞከር መሆኑ ቢሮው ርቆብናል ለሚሉት አንደኛው ምክንያት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም የዜና አውታሮች በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እኩል አለመታየታቸው ሌላው ችግር ነው። እንደምሳሌ ለመጥቀስ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ አልተመዘገበችም፣ መረጃዎችንም ለማግኘትም ሆነ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ከሌሎች እኩል የመጋበዝ ዕድልም አይኖራትም። በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሰጡት በአሃዱ ቴሌቪዥን የዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች አርታኢ ስንታየሁ አባተ፣ ኹሉም የዜና አውታሮች እኩል አለመወከላቸው በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ላይ ቅሬታን የሚፈጥር ነው ይላሉ። አያይዘውም በዜና አውታሮችም በኩል ለአገር ጥቅም የበኩሌን እያደረግኩ አይደለም ወይ የሚል ጥያቄ ሊፈጥር እንደሚችል ገልጸው፥ በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ሳይሰሙ ከኹለተኛ ደረጃ ምንጭ በመቀበል ዜና በመሥራት የተሳሳተ መረጃንም ለሕዝብ የሚያደርስበት አጋጣሚው ሰፊ እንደሚሆን አልሸሸጉም።
በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ለውጡን ተከትሎ ወርሐዊም ይሁን ሳምታዊ የመገናኛ ብዙኀን ቀን እንደሚኖር ቃል የተገባ ቢሆንም እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ መሆኑ፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመገናኛ ብዙኀን ቀርበው የሚናገሩበት፣ ጥያቄዎችን የሚመልሱበት የተወሰነ የጊዜ ገደብ አለመኖሩ አሁንም ቢሮው እንዲርቅ እንዳደረገው የመገናኛ ብዙኀን እንደምክንያት የሚያነሱት ጉዳይ ነው።

ለዚህ መንሥኤው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ራሳቸው መግለጫውን ለመስጠት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ የተጣበበ ጊዜ ስለሚኖራቸው፣ በታሰበለት ጊዜ ጽሕፈት ቤቱ ጋዜጠኞችን ማስተናገድ አለመቻሉ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያሉ የፕሬስ ሴክረታሪ መዋቅርም መግለጫዎችን ለመስጠት ብቁ አለመሆኑም አስተያየት ሲሰጥበት ይደመጣል። ይህን በሚመለከት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አሕመድ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩር አንድ ጽሑፋቸው እንደሚገልጹት፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሁን ያለው የኢትዮጵያን ሁኔታ ብቻቸውን የሚጋፈጡት ባለመሆኑ በሥራቸው ባሉት ባለሙያዎች ላይ እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባና ዕድልም ሊሰጧቸው እንደሚያስፈልግ ጽፈዋል።

የመገናኛ ብዙኀን አስተያየት በዚህ ብቻ አያበቃም፤ በተለያዩ ጊዜያት ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የሚገኙት መረጃዎች ራሳቸውን የሚቃረኑ ከመሆናቸውም በላይ ተለዋዋጭ በመሆናቸው በመረጃዎች ላይ ተመርኩዞ ዜና መሥራት ወይም ማስተላለፍ አስቸጋሪ እንደሆነም ከወደ መገናኛ ብዙኀኑ መንደር የሚደመጥ አስተያየት ነው።

እንደማሳያ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትን አነሳን እንጂ፣ ከተለያዩ የክልል እና የፌደራል መሥሪያ ቤቶች መረጃን ማግኘት ወይም የተገኘውን መረጃ ለማረጋገጥ የሚደረገው ሒደት ፈታኝ ነው። በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚታየው ይህ ዓይነቱ ማነቆ የተባለው ʻለውጥʼ ከመምጣቱ በፊት በርካታ የኅትመት መገናኛ ብዙኀን እንዲከስሙ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገብረጊዮርጊስ አብረሃ ችግሩ አሁንም እንዳለ ያምናሉ። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ባልሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ለመንግሥት ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት የመረጃ ክልከላው እንዲቀንስ እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

መነሻችን ላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርነው እውን ʻለውጥʼ ታይቷል ወይ ለሚለው ጥያቄ እንደ አህመድ ሱሌማን ዓይነት የፖለቲካ ተንታኞች የግል አስተያታቸውን አስቀምጠዋል። አንዳንዶች ደግሞ ለውጥ ያልታየበትን ምክንያት ሲገልጹ የታሰበው ለውጥ በአንድ ሰው ብቻ እንደማይመጣ እና ለውጡን የሚደግፉ ባለሥልጣናት አሁንም አለመኖራቸው አንደኛው ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ።

ይህን ሐሳብ የሚያጠናክርልን ደግሞ የዓለም ዐቀፉ የሰላም ፋውንዴሽን ዳይሬክተሩ አሌክስ ዳ ዋል ነባራዊው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ (The Real Politics Of The Horn of Africa) በሚለው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት በሕግ የተጠረነፉ ናቸው ሲል ይገልጻሉ። አያይዞም ባለሥልጣናት ሕግና ደንብ ላይ ከማተኮራቸው የተነሳ በዛው የተተበተቡ መሆናቸውንም ያስቀምጣሉ፤ ባለሥልጣናት ለውጥን ለመቀበል ዝግጁ ካለመሆናቸው የተነሳ በፖለቲካ የበላዮቻቸውን እና ሰፊውን ሕዝብ በመፍራት ውስጥ እንደሚኖሩ ጽሑፉ ያትታል። አሌክስ ሲቀጥሉም በጽሑፉ፣ በአብዮታዊ የለውጥ ሒደቶች ውስጥ የተንዛዛው ቢሮክራሲ መለወጥ ባለመቻሉ በዕለት ተዕለት ሥራ ላይ እንደሚስተዋል ያረጋግጣል።

የ30 ዓመታት የጥናት ጽሑፍ በሆነው መጽሐፉ አሌክስ ስለ ኢትዮጵያ የሥልጣን ፅንሰ ሐሳብ ሰፊ ማብራሪያ አስፍረዋል። በኢትዮጵያ ሥልጣን ሊካፈሉት የማይችሉት ነገር ተደርጎ ከመወሰዱም በላይ ሊገኝ የሚችለው በጦር መሣሪያ ትግል ብቻ እንደነበር ነው የሚያስቀምጡት። መሪዎችም በብዙኀኑ ከመመረጥ ይልቅ የተከበሩ እና የተፈሩ መሆናቸው ብቻ በቂ እንደሆነ እንደሚያምኑ ይነገራል።

የሰላምና ደኅንነት ፖሊሲ ጥናት ባለሙያዋ ፌበን “አሁን ያለው መንግሥታዊ አስተዳደር ከመፈራት ይልቅ በተቃራኒው በፍቅር ሁሉን ለማድረግ በመሞከሩ፣ ከሕዝቡም ሆነ ከመንግሥት ሹመኞች ንቃተ ሕሊና ጋር አብሮ ባለመሔዱ የሚፈለገው ለውጥ ላለመምጣቱ ምክንያት ነው” ይላሉ። በእርግጥ መፈራት ማለት በአፋኝ እና ጨቋኝ አካሔድ ሕዝብን እያንቀጠቀጡ ማስተዳደር ሳይሆን፥ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ወደ ኋላ የማይል እና ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖረው ለማድረግ የማያቅማማ መንግሥታዊ አስተዳደር ማለት እንደሆነ ያብራራሉ።

እንደ ፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አሕመድ ሱሌማን ጽሑፍ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ላይ የፈጠሩት የዲፕሎማሲ መሻሻል ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም በአመዛኙ ከሚስተዋልባቸው የሦስትዮሽ ግንኙነት ወጥተው ከፍ ወዳለ እና ተጨማሪ አገራትን ወደሚያሳትፍ ግንኙነት ቢሔዱ መልካም እንደሆነ ያስገነዝባል። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመካካለኛው ምሥራቅ የገነቡት ጠንካራ ዲፕሎማሲ በአገር ውስጥ በየቀኑ እየጨመረ የመጣውን ብሔርን መሥረት ያደረገ ግጭትና መፈናቀል እንዲቀንስ ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደሌለው አስምሮበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ዐቢይ ኢሕአዴግ ተዋሕዶ አገር ዐቀፍ ፓርቲ እንዲመሠረት ያላቸውን ሐሳብ በሚመለከት፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም እንደገና እንዲመረጡ ያቀዱበት የአጭር ጊዜ ቀመራቸው መሆኑን በጽሑፋቸው ላይ ገልጸውታል።

ሰላም ሚኒስቴር
የዐቢይን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን መያዝ ተከትሎ በዓለም መነጋገሪያ ያደረጋቸውን ግማሹን ካቢኒዎቻቸውን በሴቶች መሙላታቸው እና ነባር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን እንዲታጠፉ በማድረግ በርካታዎቹን በአንድ የሚያቅፍ አንድ ሚኒስቴር ማቋቋማቸው ነው። የበርካታ ሥልጣኖች ባለቤት የሆነው ይህ አዲሱ ሚኒስቴር ሰላም ሚኒስቴር የደኅንነትንና ፌደራል ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች ቀደምት ጉልህ ሚና ይጫወቱ የነበሩ ሰፊ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤትንም አካቷል። ለዚህ ደግሞ የቀድሞውን የአርብቶ አደርና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።

በበርካቶች ዘንድ እጅግ ከአቅም በላይ ሥልጣን አካብቷል በሚል የሚተቸው የሰላም ሚኒስቴር፣ የባለሙያ እጥረትም ዋና ተግዳሮቱ እንደሚሆን ከጅምሩ የታሰበበት እንዳልነበረ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ። ለዚህ ደግሞ አጠናካሪው እውነታ በቅርቡ ሰላም ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም ጋር በጋራ የሚሠራበትንና በባለሙያዎች በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየቱ ነው። ከባለሙያ እጥረቱም ባለፈ አሁን ባለበት ደረጃ ሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ሥራ እየሠራ እንዳልሆነ ፌበን መኮንን ጨምረው ይናገራሉ። አያይዘውም በሚኒስቴሩ ውስጥ ግልጽ የሆነ ተቋማዊ መዋቅር አለመኖሩንም ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የሰላም ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ባቀረበበት ወቅት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በአንድ ወር ውስጥ አብዛኛውን ተፈናቃይ ወደ ቀየው እንመልሳለን ቢሉም፥ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተለየ ነው።
አንድ ዓመት ያስቆጠረው “የለውጥ አመራር” ተከትለውት ተግባራዊ የሆኑ የለውጥ መገለጫ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች አሁንም ከትችት አላመለጡም። በለውጡ መባቻ ማንም አሳዳጅ ተሳዳጅ ሳይኖር ዜጎች በነፃነት መኖር እንደሚችሉ እና የሰብኣዊ መብት ቀበኞችንም ለሕግ እንደሚቀርቡ በጠቅላይ ሚኒስቴሩ መገለጹ ይታወሳል። ይሁንና በዚህ ረገድ ምን ተሠራ በማለት ይጠይቃሉ።

ለውጡ እና ዐቃቤ ሕግ
ለውጡን ተከትሎ በርካቶች በልዩ ትኩረት የሚከታተሉት የቀድሞውን ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ደግሞ የሙስናውን ዘርፍ ኀላፊነት በማካተት በአዲስ መልክ የተዋቀረው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ነው። በተለይ ደግሞ በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ግለሰቦች መቼ ይሆን ክስ የሚመሠርትባቸው በሚል ጉጉት ባዘለ ስሜት ይጠባበቁታል። ዐቃቤ ሕግ የለውጡ ኃይል የገባውን ቃል በማስፈፀም ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለበት የሚናገሩት ፌበን፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈፅሟል ለተባለው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙትን ግለሰቦች እስካሁንም ወደ ሕግ አለማቅረቡ በራሱ ለውጥ ታይቷል ለማለት እንደማያስደፍር ይናገራሉ፤

ፌበን በእርግጥ ከአገሪቱ በርካታ ችግሮች አንፃር ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ ይፈፀም ማለት ከባድ ቢሆንም፥ ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚደረገው ጥረት ግን እጅግ ዘገምተኛ ነው ይላሉ። ወንጀለኞች በጊዜ ወደ ሕግ ከአለመቅረባቸው ጋር ተያይዞ በስፋት የሚስተዋለው አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑንም ጨምረው ይናገራሉ። ወንጀለኛ ተብለው የተጠረጠሩትን በቀጥታ በሥራው ላይ ተሳታፊና መሪ የነበሩ (practitioners) ናቸው የሚሉት ፌበን እነዚህ ባለሙያዎች በፅንሰ ሐሳብ በኩል ሳይሆን በድርጊት የኖሩ በመሆናቸው አሁንም ዐቃቤ ሕግ በተግባር ተንቀሳቅሶ ወደ ሕግ ከማቅረብ በስተቀር ሌላ አማራጭ ወይም ድርድር ወይም በንግግር መፍታት የሚባለው ሐሳብ ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ። ʻለውጥʼ አለ ከተባለ ለውጡ በሥፋት ሊታይ እንደሚገባ የሚናገሩት ፌበን ዐቃቤ ሕግ ግን ከዚህ የተለየ አካሔድን እየተከተለ መሆኑን አስቀምጠዋል።

ይህን በሚመለከት የፌደራል ዐቃቤ ሕግ የሦስተኛ ሩብ ዓመት መጀመሪያው ላይ በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ የወጣባቸው ግለሰቦች በሩብ ዓመቱ ወደ ሕግ እንደሚያቀርቡ ቢገልጽም፥ አሁንም ተጠርጣሪዎች ወደ ሕግ እንዳልቀረቡ የሚታወቅ ነው።

በእርግጥ ለውጥ ታይቷል?
በመከላከያ ሚኒስቴር በከፍተኛ አማካሪነት ረጅም ዓመታት የሠሩትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሰላምና ደኅንነት ላይ የሚሠሩት ሙሉቀን ሀብቱ “ለውጥ ለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም” ብለዋል። ሲሉ የሚጀምሩት ሙሉቀን በአገር ውስጥ መጣ ከሚባለው ለውጥ ይልቅ በኢትዮ ኤርትራ በኩል የታየው የሰላም ሥምምነት በትንሽም ቢሆን የለውጡን ኅያውነት ሊያመላክት ይችል እንደሆነ እንጂ በአገር ውስጥ ለውጥ መጥቷል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ያብራራሉ። ቅድሚያ የሚሰጠው ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች አቅማቸውን የሚያጎለብቱበት እና ለችግሮች ምላሽ የሚሰጡበትን ሁኔታ መፍጠር ነው እንጂ አርማ መቀየር ወይም ቢሮዎችን ማስዋብ “አብለጭልጮ ከመታየት ያለፈ ፋይዳ የለውም” ይላሉ።

አንፃራዊ ሰላም ከሚስተዋልባት አዲስ አበባ ወጥቶ ወደ አራቱም አቅጣጫ መጓዝ እጅግ እየከበደ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት ለውጥ እንዳለ አድርጎ ማውራት እውነታን መካድ እንደሆነ ሙሉቀን ያብራራሉ። ስለዲፕሎማሲው ዘርፍ ሙሉቀን ሲናገሩ ለኻያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት እንዲቀጥል መደረጉ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ያህል የቀጠናው ተለዋዋጭመልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያሻው እንደሆነና፥ በስሜታዊነት ተመርቶ የሚገባበት ቀላል ጨዋታ አለመሆኑን ያስገነዝባሉ።

በቅርቡ ኤርትራ እስካሁን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኟትን ድንበሮች መዝጋቷ ተለዋዋጭ ለሆነው የቀጠናው በተለይም ደግሞ በኢትዮ ኤርትራ መካከል ያለው ፖለቲካ አንድ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ቃል የገቡትን አልፈፀሙም፤ የታሰበው ለውጥ እየታየ አይደለም በሚል ቀድሞ ʻዐቢይማኒያʼ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ሁሉ እየሆነ ባለው እና ከተገመተው በተቃራኒው እየሆነ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያላቸው ድጋፍ ማሽቆልቆሉን እና አዲሱ አመራር መልካም አስተዳደርና አለመረጋጋትን ያሰፍናል ብለው እንደማያምኑም በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ በስፋት በመጻፍ የሚታወቁት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አሕመድ ሱሌማን በጽሑፋቸው ላይ አስነብበውናል።

መንግሥት በአገር ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ አለመረጋጋቶችን ወዲያውኑ አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኖችን በማቋቋም መጠመዳቸውን በጽሑፋቸው የሚያትቱት ምሁሩ፣ በተለይ ደግሞ አዲስ የተዋቀረውን የሰላም ሚኒስቴር ሥልጣን ከማጎልበት ባለፈ ውስብስብ መልክ ላለው የአገሪቱ ቀውስ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ሐሳባቸውን ያስቀምጣሉ። ይህንን ሐሳብ የሚጋሩት ደግሞ በፍሬድሪክ ኧርበርት ስቲፍቱንግ የሰላም እና ደኅንነት ፖሊሲ ጥናት ባለሙያዋ ፌበን መኮንን ናቸው። “ለኮሚሽኖች እና ለሚኒስቴር ከልክ ያለፈ ሥልጣን መስጠት ኢትዮጵያን ወደ መረጋጋት አይመራትም” ሲሉ ይሞግታሉ።

የሕግ ስርዓቱ በአሁኑ ሰዓት ከመላላቱ የተነሳ የደቦ ፍርድ እጅግ አሳሳቢ ነው። ለውጥ ወደ ጥሩም ወደ መጥፎም ሊመራ እንደሚችል የሚናገሩት ፌበን ከዚህ ቀደም ታይተው የማይታወቁ ወንጀሎችን መስማትና ማየት በየዕለቱ እየተለማመድነው ነው ይላሉ። “ለውጥ” የሚባለው ነገር ወደ መልካም ካልሆነ በጭራሽ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም እንዲያውም ዜጎች ከቀን ወደ ቀን በስጋት ውስጥ መኖራቸው እየጨመረ ሔዷል በማለት ፌበን አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here