ቁጥጥር እና ሚዛን

0
652

የተቋማት መልሶ ማዋቀር ወይም ማሻሻያ (institutional reform) ጉዳይ ሲነሳ የሚታሰበው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ብቻ አይደለም። ቁጥጥር እና ሚዛን (check and balance) መፍጠርም አንዱ ዓላማ ነው። በርግጥ ተቋማዊ ቁጥጥር እና ሚዛንም የመልካም አስተዳደር ዘላቂ ዋስትና ነው።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሦስቱ የመንግሥት ቅርንጫፎች (ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስከባሪው እና አስፈፃሚው) መካከል ቁጥጥርና ሚዛን አልነበረም። በዚህም ምክንያት ሕግ አስፈፃሚው ሕግ አውጪውን እና ሕግ ተርጓሚውን አካል የፈለገውን እንዲፈፅሙ ያደርጋቸዋል። ለዚህ ዋነኛው መንሥኤ የአውራ ፓርቲ መኖር ሲሆን፥ የአስፈፃሚው አካል ለዴሞክራሲያዊ የተቋማት ነጻነት እና ገለልተኝነት ፈቃደኛ አለመሆን ተጠያቂ ነው።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሁኔታ የትኛው ሕግ አውጪ፣ የቱ ተርጓሚ እና የቱ አስፈፃሚ እንደሆነ እስኪቸግር ድረስ ሁሉም የአስፈፃሚውን አካል ፍላጎት ነው የሚያንፀባርቀው። ይህንን ተገን አድርገው በሥልጣናቸውን የሚባልጉ፣ ዜጎችን የሚያሰቃዩ እና የሚዘርፉ የመንግሥት አካላት ተጠያቂ ካለመሆናቸውም ባሻገር በእጃቸው፣ ሁሉ በደጃቸው ስለሆነ ነው።

ይህንን ለማስተካከል አስፈፃሚው አካል በሕግ ተርጓሚው ጉዳይ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት ማስቆም ያስፈልጋል። በተለይም የዴሞክራሲ ተቋማት የሆኑት ፍርድ ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን፣ እምባ ጠባቂ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲሁም የፀጥታ አካላት የመሳሰሉት ከሕግ አስፈፃሚው ጋር እጅና ጓንት ሆነው መሥራታቸው ለዴሞክራሲ ግንባታ አግባብ አይደለም። በወዳጅነትም ይሁን በበላይነት የሚደረግ የአስፈፃሚው አካል ተፅዕኖ በእነዚህ ተቋማት ላይ ካረፈ ዴሞክራሲ ፈተና ውስጥ ይገባል።

እስካሁን በነበረው አሠራር አስፈፃሚው አካል ፈርጣማ በመሆኑ ያሻውን የሚያደርግበት ነው። በቀደሙት ዓመታት አስፈፃሚው አካል ያሻውን ሕግ እያስወጣ እና እንዳሻው እያስተረጎመ አምባገነናዊ ሥራ በይስሙላ ዴሞክራሲ ሥም ሲተገበር ቆይቷል። አሁንም የማሻሻያ ሙከራው በተመሳሳይ ሞዴል ቀጥሏል። ለምሳሌ ቀድሞ አስፈፃሚው አካል ያልወደዳቸውን አካላት ረዥም እጁን በመጠቀም ባሰረበት መንገድ አዲሱ አመራር እንዲፈቱ አድርጓል። እርምጃው የእርምት በመሆኑ ቢደነቅም ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ብቻ ነው። ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሲባል የአስፈፃሚው አካል እጅ ማጠር አለበት። የመንግሥት እና የገዢው ፓርቲ መቀላቀል መቀረፍም ይኖርበታል። ተቋማቱ መልሰው ሲዋቀሩ በሰዎች እና የሎጎ ለውጥ ሳይሆን በነጻነት እና በገለልተኝነት የሚሠሩበት መንገድ መመቻቸት አለበት። እርስ በርስ ቁጥጥር ማድረግ ችለው ሚዛን መፍጠርም አለባቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here