በነገሌ ቦረና የልኳንዳ ቤቶች በአድማ ዋጋ በመጨመር ክስ ተመሰረተባቸው

0
925

በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን ዋና ከተማ ነገሌ ቦረና የፋሲካ በዓልን ተከትሎ የሥጋ ዋጋ ጭማሪ አድርጋችኋል በሚል የነገሌ ቦረና አስተዳደር ንግድ ጽሕፈት ቤት 14 የሥጋ ቤት ባለቤቶች ላይ አድማ በማድረግ ክስ መስርቷል። ከነዚህ መካከልም አራት ተጠርጣሪዎችም ያለፍርድ ቤት ማዘዣ እና ግልጽ በሆነ ማዳላት ታስረናል፤ ለመታሰራችንም ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ቀድመን አሳውቀናል ብለዋል።

የነገሌ ቦረና የፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አብዱልከሪም ሁሴን፣ በበዓሉ ቀን ነጋዴዎች አድማ በማድረጋቸውና ሕዝቡም በመቃወም ድንጋይ ይዞ በመውጣቱ፥ ከተማውን ለማረጋጋትና ጉዳዩን ለማጣራት ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ልናሥራቸው ችለናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። “ያሰርነው አራት ሰዎችን ሲሆን ቀሪዎቹ ተሰውረው ስለነበር ማግኘት ባለመቻላችን ነው ያልያዝናቸው” ሲሉ ገልፀዋል። የሥጋ ቤት ነጋዴዎቹም በፊት የበሬ ዋጋ ጭማሪ አሳየቷል በሚል የዋጋ ጭማሪ ጥያቄ ለከተማዋ ንግድ ቢሮ ቢያስገቡም መፍትሔ ባለማግኘታቸው ዋጋውን ለመጨመር ተገደናል ብለዋል።

መስፍን ታምሩ በነገሌ ቦረና የሽብሬ ሆቴልና ሥጋ ቤት ባለቤት ናቸው። በትንሣኤ ዋዜማ ቅዳሜ፣ ሚያዚያ 19/2011 ለውስጥ ተገልጋዮች 210 ብር እና ለውጭ ተጠቃሚዎች 180 ብር ሽጡ ተብለው ዋጋ እንተለጠፈላቸውና ዋጋ እንደተቆረጠባቸውም ገልፀዋል። “በፊት 19 ሺሕ ብር ይሸጥ የነበረው በሬ አሁን ላይ 40 ሺሕ ብር ገብቶብናል እያልን ይሄ ተመን መውጣቱ አሳዝኖናል” ሲሉ ተናግረዋል በከተማዋ የሚገኙ ኮርማዎቹ ለሥጋ ቤት የሚሆኑ ባለመሆናቸው ከአርሲ ነጌሌ እንደሚገዙ ተናግረዋል።

የነገሌ ቦረና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ነጌሳ ባነታ በከተማዋ በሳምንት ኹለት ቀን ቅዳሜና ማክሰኞ የገበያ ቀን በመሆኑ በየሳምንቱ የገበያ ጥናት እንደሚያካሔዱ እና የተባለውን የዋጋ ንረት እንዳልታዘቡ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ነጋዴዎቹ ደብዳቤውን ያስገቡት በ14-08-2011 ሲሆን እኛ ወዲያው ኮሚቴ አዋቅረን ጥናት አድርገን ነጋዴዎቹን አወያይተን ውሳኔ ወስነናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መንግስት ያወጣው የዋጋ ተመን ስለማያዋጣን አንሰራም፣ የአንድ በሬ ዋጋ 40ሺ ብር ሆኖ ሳለ በ210 ብር አያዋጣንም፣ ይህንን ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት ሊያናግሩን ይገባ በማለት ቅሬታቸውን ገልፀዋል ለእርድ የሚዘጋጁ የማይወልዱ ላሞች (መሲና) ቀድሞ ከ9ሺ እስከ 10ሺ ይሸጡ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ 18ሺ ብር መግባታቸውንም አክለዋል።

ነጋዴዎቹም ቀርቦ የሚያነጋግራቸው አካል እንደሌለም ተናግረው ሠራተኞች በቢሮ ውስጥ ባለመገኘታቸው እና በመጨረሻም ከንቲባው ቅሬታቸውን ቢሰሙም የሰጡት መልስ ግን የጠበቁትን አለመሆኑንን ተናገረዋል። ‹‹በከንቲባው ተወካይ ሁቃ ኡራጎ በኩል ደብዳቤአችን ወደ ከተማዋ ንግድ ጽ/ቤት ተመርቶልን፣ የገበያ ጥናት የሚያካሂድ ኮሚቴ አዋቅረን አጥንተን ምላሽ እንሰጣለን ቢሉንም፣ ለውይይት ይጠሩናል ብለን ጠብቀን ነበር ምንም አይነት ውይይት ሳናደርግ ጥያቄአችንን ውድቅ ተደርጓልም ብለዋል።

ሌላኛው ነጋዴ አቅራቢ ለማ ኤርጃቦ ወደ ሥጋ ንግድ ከገቡ 2 ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ እርሳቸው እንደሚሉት ከባድ ሁኔታ ውስጥ ነኝ ያለሁት ቤት ኪራይ 10 ሺሕ ብር እከፍላለሁ፣ 14 ሰራተኛ አለኝ አሁን ያለሥራ እንድንቀመጥ ሆነናል ብለዋል።

“ቀደም ብለን ለኅብረተሰቡ ዋጋውን (ተመኑን) አሳውቀናል፤ የሕዝብ አገልጋይ እስከሆኑ ድረስ ሕዝቡን በፆም ፍቺ ቀን አድማ ማድረግ አልነበረባቸውም፤ ደብዳቤው የሚለው የምንሸጥበት ዋጋ አያዋጣንም የሚል ሲሆን አድማ አድርገው ሕዝቡን ከሚያጉላሉ እየሠሩ ቅሬታቸውን ማቅረብ ነበረባቸው ያሉት ነጌሳ ከዚህ በኋላ ያለው ሒደት በሕግ አግባብ እንዲታይ አድርገናል፣ ሕዝቡ ያነሳው ቅሬታ ትክክል ነው ፆም ፍቺ ላይ ሕዝቡ ተበድሏል በማለት ሲሉ ገልጸዋል።

“ከኅብረተሰቡ ጋር ትልቅ ቅራኔ ውስጥ ገብተናል” ያሉት መስፍን የአገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን እንደያዙትና ጥፋተኛ ሆነን ከተገኘን ሕዝቡን ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here