መንግሥት አሁንም ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እጁን ያውጣ ተባለ

0
1101
  • ሚያዝያ 23/2011 የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኀላፊነቱን በይፋ ካስረከበ በኋላ አዲስ የሽግግር ኮሚቴም ተቋቋሟል

በውይይቱ በቀረቡ ሰነዶች ላይም ከሞላ ጎደል ሥምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ ቀጣይ ዝርዝር ውይይቶችንም አዲስ የተመረጠው የኡላማዎች ኮሚቴ የሚመራ ይሆናል ነው የተባለው።

በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አዳራሹ ሲገቡ “የቀድሞው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ኀላፊነቱን የለቀቀው ተገዶ ነው፤ መንግሥት ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት እጁን ያንሳ” በሚሉ ወገኖች የተቃውሞ ድምፅ አሰምተዋል።

ተቃውሞውን ሲያሰሙ ከነበሩ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው አሕመድ እንድሪስ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ሥራ አስፈፃሚው በጥቂት ሰዎች ጫናና በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሥልጣኑን እንዲለቅ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ አሁንም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ፤ ኮሚቴዎቹ በተደጋጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እየተገኙ ይወያዩ ነበር። መሆን የነበረበት በራሱ በእምነቱ አባቶችና ኡለማዎች በገለልተኝነት መታየት ነበረበት ሲል ተቃዋሚዎቹን ወክሎ ተናግሯል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሸምጋይነት ሰኔ 26/2010 የተቋቋመውና ዘጠኝ ኮሚቴ ያለው ቡድን አባል የሆኑና ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ በበኩላቸው፣ ኮሚቴው ሲቋቋም ገለልተኛ ከሆኑ ከምሁራን ኹለት፣ ከአገር ሽማግሌ አንድ፣ በድምሩ ሦስት አባላት ያለው ገለልተኛ አካል በኹለቱም ወገኖች ሥምምነትና ተጠቋሚዎቹ በሌሉበት እንዲሰየሙ መደረጉን ገልጸው፣ እነዚህ ሰዎች ከኹለቱም ወገን ተአማኒነት ያላቸው መሆኑ እየታወቀ ተቃውሞ ማሰማቱ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።

በዚህ የኡለማዎች ስብሰባ ላይ በመገኘትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ጠንካራ የሙስሊም ማኅበረሰብ ለአገር አንድነት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሃይማኖቱ የሚያስተምረውን አንድነትና ፍቅር ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል። የአስተሳሰብ ብዝኀነትን በማክበር ሕዝበ ሙስሊሙ ይቅር ተባብሎ ለጋራ አንድነት መሥራት እንደሚገባውም ነው የተናገሩት።

በእስካሁኑ ሒደት ያጠፉ፤ ያሳዘኑ ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእምነቱ እንደተቀመጠው ሁሉ ይቅር ተባብሎ የአንድነት ጉዞን መጀመር ይገባዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ሰብሳቢ የሆኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር ኢድሪስ ባደረጉት ንግግርም፣ ቀኑ ለሕዝበ ሙስሊሙ አንድነት ወሳኝ በመሆኑ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ኢድሪስ መሐመድ በበኩላቸው፣ ኮሚቴው የተቀመጠለትን ዓላማና ግብ ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አውስተዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብና መዋቅር ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታና ወደፊት እንዲደርስበት የታሰበውን ግብ ማሳካት በሚያስችል መልኩም ረቂቅ የመተዳደሪያ ደንብና መዋቅር መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።

እስልምና ጥልቅና ብዝኀ ሐሳብን የሚያስተናግድ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ሸሪዓው በሚፈቅደው አግባብ መፍታት ያስቸገረበት አጋጣሚ እንደነበርም አስታውሰዋል። በቀጣይም መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ኮሚቴው እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ቀጣዩን የረመዳን ፆም በይቅርታ እንዲጀምረው ጠይቀዋል።
ከ300 በላይ ኡላማዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ጉባዔ ላይ፣ 23 አባላት ያሉት ጊዜያዊ የኡላማዎች ምክር ቤት በመምረጥ ተጠናቋል። የመጅሊስ ምርጫን የተመለከቱ ሌሎች ጉዳዮችን ለማስፈፀም ኮሚቴው ከሥሩ በተዋቀረለት ቦርድ ታግዞ የሚያስፈፅም ይሆናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here