መሬት ያልረገጠው የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ

0
636
  • በየዓመቱ 92 ሺሕ ሔክታር ደን ይመነጠራል

በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የመሬት ፖሊሲ እንዲያዘጋጅ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሥር የተቋቋመው ብሔራዊ የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት በመንግሥት ትኩረት ማጣት ኅልውናው ጥያቄ ውስጥ መግባቱን አስታወቀ።

በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ወረዳዎች በሦስት ዓመታት ውስጥ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ፣ የአፈር ምርምር፣ በየአምስት ዓመቱ የሚታደስ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድና ዲዛይን እንዲያዘጋጅ የተቋቋመው ጽሕፈት ቤት የሚጠበቅበትን ሥራ ሳያከናውን ከዕድሜው ከፊሉን አገባዷል። ከ14 ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተውጣጥቶ የተቋቋመውን መሪ ኮሚቴ (steering committee) በመምራት ሁሉም ወገኖች በመሬት ጉዳይ ያላቸው የጥቅም ግጭት (conflict of interest) አደራድሮ ሥምምነት ላይ በማድረስ፣ የተመደበለት የሦስት ዓመት ዕድሜ አጠናቅቆ ወደ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ እንዲያቀብል ዕቅድ ተይዞ እንደነበር የኮንስትክሽን ሥራዎች ውልና የሕግ ክትትል ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ቡልቻ በሬቻ ገልጸዋል።

በወቅቱ ዓለማየሁ ተገኑ በሚመሩት በካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ትብብር ሚኒስቴር በተጻፉ ደብዳቤዎች የተቋቋመው ፕሮጅክቱ እስከ ሰኔ 2010 በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ሰባት የሚሆኑ ሠራተኞችን ይዞ እየተደራጀ ነበር።

ይሁን እንጅ “የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በሌሎች ጉዳዮች ስለተወጠረ ልንደግፈው አንችልም’’ በሚል በወቅቱ የካቢኔ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት ደሚቱ ሃምቢሳ በተፈረመ ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ግቢ ወጥቶ በቅርቡ ከሚኒስቴርነት ደረጃ ከወረደው የአካባቢ፣ የደን፣ እና የአየር ለውጥ ኮሚሽን ውስጥ አርፏል።

በአሁኑ ወቅት አራት ባልደረቦቹን ይዞ ‘እየተንቀሳቀሰ’ ያለ ሲሆን ሠራተኞቹም ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመለትን ዓላማ ምን ላይ እንዳደረሰውና እንዴት እንደሚያሳካው ግንዛቤው ያላቸው አይመስልም። የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተስፋዬ ጋሻው “ጽሕፈት ቤቱ አሁን ባለበት ሁኔታ ከእሱ በላይ የሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ማዘዝ መቻሉ ያጠራጥራል” ይላሉ ።
“አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የጽሕፈት ቤቱን አስፈላነት ሳይረዱ ነው በአንድ ደብዳቤ ከጽሕፈት ቤቱ እንዲወጣ የተወሰነው፤ አሁን በኮሚሽኑ ውስጥ እንደ አንድ ዲፓርትመንት ብቻ ነው የሚቆጠረው። የራሱ በጀትና የሰው ኃይልም የለውም። የነደፈውን መዋቅርም መሬት ላይ ማውረድ አልቻለም” ቡልቻ እንደተናገሩት።

የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ድህነትና የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገት ማነቆነት ዋነኛ ምንጭ ስለመሆኑ በ2009 በቀረበ ዓለም ዐቀፍ ጥናት መጠቆሙን ተከትሎ ነበር የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጽ/ቤቱ በአስቸኳይ እንዲቋቋም ያዘዙት።

የግብርና ምኒስትር ከረጅም ጊዜያት በፊት የመሬት ፖሊሲ የማዘጋጀት ሥራ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ለራሱ ያደላል በሚል ተወስዶ ለአካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥና ደን ሚኒስቴር መሰጠቱ ይታወሳል። ነገር ግን ይህኛውም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደንን የማሥፋፋት የራሱን ፍላጎት ከማስፈፀም ባለፈ ሁሉን ዐቀፍ ሥራ የሚሠራበት መንገድ ባለመኖሩ ለመሬት አጠቃቀም ፖሊሲው እውን መሆን የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ በመታመኑ ነበር ገለልተኛ ጽሕፈት ቤት ማቋቋም ያስፈለገው። ይሁን እንጅ የጽሕፈት ቤቱ መቋቋም በራሱ መፍትሔ መሆን ተስኖታል።

“በእኛ ሥር እያለ ቢያንስ የፖሊሲ ማዘጋጀት ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየሔደ ነበር’’ ሲሉ በግብርና ሚኒስቴር የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ካሳሁን ግርማ ይሞግታሉ።

ፖሊሲው በአፈር ይዘትና በኅብረተሰቡ አብላጫ ፍላጎት ላይ በመመሥረት በብዙ አገራት ባልተለመደ መልኩ ጠቅላላ የአገሪቱን መሬት በ22 የተለያዩ የአጠቃቀም ክፍሎች ለመክፈል ነበር ዕቅዱ። ከነዚህም ውስጥ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ውሃማ አካላት፣ የእንስሳት እርባታ ተጠቃሾች ናቸው። ፖሊሲው በተለይም የከተሞች፣ የኢንዱስትሪ፣ እና የግብርና አላግባብ መስፋፋት ይገታል ተብሎ ነበር። አብዛኛዎቹ የዓለም አገራት ቢበዛ ከ9 እስከ 14 በሚሆኑ የአጠቃቀም ክፍሎች ነው የሚከፍሉት።

በሚንስቴር ዴኤታ ማዕረግ በጽሕፈት ቤቱ የጠቅላይ ሚንስትሩ ተጠሪ የሆኑት ገብረሕይወት ገብረሚካኤል ከተሞች፣ ኢንዱስትሪና፣ መሠረተ ልማቶች ለም ባልሆነ አፈር ላይ ብቻ መመሥረት አለባቸው ሲሉ ያስረዳሉ። “ተራራማና ዳገታማ ቦታዎች በሙሉ ለደን ተከልለው ለም የሆነ አፈር በሙሉ ለግብርና ማስፋፊያ የተተወ መሆን አለበት” በማለት የፖሊሲውን አስፈላጊነት ያብራራሉ። አንዳንድ ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነም ፕላን ኮሚሽን ለጉዳዩ ቀጥተኛ ተከታታይ መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በከፍተኛ የጤፍ ምርቱ ይታወቅ የነበረው የቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) እና አዳማ አካባቢ መሬት ለኢንዱስትሪ በመሰጠቱ የዓደኣ ጤፍ ምርት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ይታወቃል። የመሬት ፖሊሲ ያለመኖሩ ጉዳይ በዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች ውስጥ ያንበሳውን ድርሻ እንደወሰደ ይታመናል።

የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የታረሰ መሬት በሔክታር ከ13 ሚሊዬን ወደ 15 ሚሊዬን ያደገ ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ በየዓመቱ 92 ሺሕ ሔክታር ደን ይመነጠራል። በዚህም የተነሳ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር የተመድን የደን መለኪያ ከ5 ሜትር ወደ 2 ሜትር በማውረድ የአገሪቱ የደን ሽፋን ከሦስት በመቶ ወደ 15 በመቶ አድጓል ማለቱ ይታወሳል።

“ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በመጭው በጀት ዓመት ከኮሚሽኑ ወጥቶና እንደገና ገለልተኛ ሆኖ ይቋቋማል ብለን እንጠብቃለን። እስከዚያው ግን የመሬት አጠቃቀም ዲዛይን ሥራውን በአዘነ በቀለ (ዶ/ር) ለሚመራ የግል አማካሪ ሰጥተናል። እስከ ሰኔ 2011 ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን” ብለዋል ሚንስቴር ዴኤታው።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here