በጌዴኦ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የጤና እክል ተጋልጠዋል ተባለ

0
567
  • የአንድ ሕፃን ልጅ ሕይወት ሲያልፍ፣ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ 22 ሺሕ 895 ሕፃናት ተፈናቃዮች መኖራቸው ታውቋል

በጌዴኦ ዞን ከገደብ ወረዳ 20 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጎቴቲ የምትባል የተፈናቃዮች ጣቢያ ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች ለከፍተኛ የጤና እክል እየተጋለጡ ነው። የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰጠው መግለጫ የቆዳ ላይ እከክ (Scabies) ተስፋፍቶ መታየቱን ገልጸዋል።

ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ሕፃናት ላይ የጤና እክሎች፣ የምግብ እጥረት በተለይም ሁሉም ሕፃናት ሊባል በሚችል ደረጃ የዓይን በሽታ (Conjunctivitis) ተጠቂዎች የሐኪሞቹ ቡድን አስታውቋል።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድ ሕፃን ከምግብ እጥረት ጋር በሚያያዙ የጤና ችግሮች ምክንያት ሕይወቱ ማለፉንም ጨምረው ተናግረዋል።

በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ በርካታ ነፍሰ ጡሮች በመኖራቸው፣ የተቻለውን ያህል አይረን እና ፎሊክ አሲድ ለማቅረብ ሙከራ ላይ እንደሆነ የተናገረው ቡድኑ የቲቢ በሽተኞችንም ለመለየት ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል። የችግሩ መጠን እና የቡድኑ አቅም ያለመመጣጠን፣ ከቡድኑ ጊዚያዊነት ጋር ተደማምሮ ለከፋ የጤና ችግር መስፋፋት ምክንያት እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ በጌዴኦ ዞን ተፈናቃዮች ድጋፍ የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች፣ የተለያዩ መድኀኒቶች እና ሌሎች ግብዓቶችን ወደ ሥፍራው ከመላክ በተጨማሪ በጤና ባለሙያዎች የሚደረጉ የተለያዩ የሕክምና ድጋፍና ክትትል ሥራዎች መቀጠላቸውን አስታውቋል።

በዞኑ በሚገኙ የተፈናቃዮች መጠለያ አካባቢዎች የአካባቢ ጤና አጠባበቅን (የውሃ አቅርቦት እጦት) በተመለከተ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲሻሻሉ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ዶክተር በየነ ሞገስ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቁጥራቸው 22 ሺሕ 895 የሚሆኑ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የገጠሟቸውን የጤና እክሎች በምርመራ በመለየት ተገቢውን ምርመራና ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረግን ነው ያሉት (ዶ/ር) ሞገስ፣ እንዲሁም በተፈናቃዮቹ የተለያዩ መጠለያዎች በተደረጉ ምርመራዎች የተለያዩ የጤና እክል ያጋጠማቸው 29 ሺሕ 823 ሰዎች ተለይተው ኽክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አክለዋል።

ከአሁን ቀደም ወደ ሥፍራው ካቀኑት ባለሙያዎች በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት 11 የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችም ለተለያዩ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር የተጋለጡ ሰዎች የድጋፍና ክትትል ሥራ እንዲያከናውኑ የተሠማሩ መሆኑንም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከአሁን በፊት 15 ሐኪሞች፣ 36 ነርሶች፣ 5 የአካባቢ ጤና ባለሙያዎች እና 5 የኢፒዲሞሎጂ ባለሙያዎች እንዲሁም ከ121 በላይ የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው ማቅናታቸውንና የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ቅኝቶችና ዳሰሳዎችን ከማድረግ በተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን በመግለጫው ተጠቅሷል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በበኩሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ከባድ የምግብ እጥረት ችግር እንደሚስተዋል ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ ባለፉት ሳምንታት ከ200 የሚበልጡ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናትን ማከሙንም ገልጿል። በአካባቢው የድርጅቱ አስተባባሪ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) እንደገለጹት አንዳንድ ወላጆች እንደውም ችግሩ ልጆቹ ላይ ያስከተለው ጉዳት ከተባባሰ በኋላ ዘግይተው ነው ወደ ሕክምና ጣቢያቸው የሚመጡት። በዚህ ምክንያትም አንዳንዶቹን ማትረፍ እንዳልተቻለም አመልክተዋል።

ተፈናቃዮቹን በሳምንት ቢያንስ አንድ ጊዜ እንደሚጎበኙ የነገሩን በዲላ ሐኪም ቤት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ (ዶ/ር) ተስፋነው በቀለ በጎ ፈቃደኛ ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸውን እና ዜጎችን በማስተባበር እነዚህን ወገኖች ለመርዳት እየሞከሩ መሆኑን ነግረውናል። እሳቸውም በአካባቢው ያለውን የጤና ስጋት ያረጋግጣሉ።

ከመፈናቀል ጋር በተገናኘ የሚከተለው ማንኛውም ችግር ጤና ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ እንደማይቀር ያመለከቱት የደቡብ ክልል የጤና ቢሮ ተወካይ የሆኑት አባተ አዶሳ ለተፈናቃዮቹ በተቻለ አቅም መቅረብ የሚገባቸውን ነገሮች እያቀረብን ነው ይላሉ። ሆኖም በበጎ ፈቃደኝነት ተፈናቃዮቹን በተደጋጋሚ በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ዶ/ርተስፋነው የክረምቱ ወራት ሲጠናከር በተፈናቃዮቹ መንደር አሳሳቢ የጤና ችግር እንዳይከሰት ስጋት አላቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here