ብዙኀን መ ገናኛዎች የውስጥ ችግራቸውን ይቅረፉ መንግሥት የራሱን ኀላፊነት ይወጣ

0
476

ለ26ኛ ጊዜ የተከነረው የዓለም ዐቀፉ የፕሬስ ቀን “ጋዜጠኝነትና ምርጫ፡ በዘመነ የመረጃ ብክለት” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ረቡዕ፣ ሚያዚያ 23/2011 ጀምሮ እስከ ትላንት ድረስ ለሦስት ቀናት ተከብሮ ውሏል።

በርግጥ በተደጋጋሚ የፕሬስ ነፃነትን በመድፈቅ ግንባር ቀደም ከሆኑ አገራት ተርታ ትመደብ የነበረችው ኢትዮጵያ ውስጥ ቀኑ መከበሩ በአገሪቱ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ምኅደሩን ለማስፋትና የፕሬስ ነፃነት ለማክበር ያደረገችውን ጥረትና የወሰደቻቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች ዕውቅና ለመስጠት ያለመ መሆኑን መገመት አያዳግትም።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ሲኦል ከሚባሉት አገሮች መካከል ትመደብ ነበር። ደፈር ብለው መንግሥትን ይተቹ የነበሩ ጋዜጠኞች ዕጣ ፈንታቸው ስደት አሊያም እስርና እንግልት ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሳደድም ሆነ በማሰር በግንባር ቀደምትነት ከሚጠሩ አገራት መካከል ትመደብ እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የታሰሩት ጋዜጠኞች ተፈትተዋል። በጋዜጠኞችም ላይ ይህ ነው የሚባል ወከባና እንግልት አልደረሰባቸውም ማለት ይቻላል። አንድም ጋዜጠኛ በጻፈው ዘገባ ምክንያት አልታሰረም። አዲስ ማለዳ ለዚህ መልካም ጅማሮ ዕውቅና ትሰጣለች።

በአገሪቱ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት እንዲሁም “ሽብርተኛ” ተብለው የተፈረጁ መገናኛ ብዙኀን ወደ አገር ቤት ተመልሰው ቢሮ ከፍተው ሥራቸውን እንዲያከናወኑ በር ከፍቷል። ሌሎች አዳዲስ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማትም በተለይ በቴሌቪዥን ዘርፍ በብዛት ተከፍተዋል። የኅትመት ዘርፉን ከተቀላቀሉትና የዚህን ለውጥ ትሩፋት ከተቀዳጁት መካከል ደግሞ አዲስ ማለዳ ትገኛለች።

እነኝህ ሁሉ ለውጦች ባሉበት ሁኔታ ግን አሁንም ቢሆን ፕሬስ ከውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ነፃ ነው ማለት አይቻልም። በተጨማሪም በአገራችን ያሉት የፕሬስ ውጤቶች የሚጠበቅባቸውን ያክል ለኅብረተሰቡ በሚዛናዊነት፣ ከወገንተኝነት በፀዳና ሙያዊ ሥነ ምግባሩን በጠበቀ መልኩ መረጃን ማቅረብ ላይ ክፍተት ይታይባቸዋል። የምርመራ ጋዜጠኘነትን በተመለከተ አፍን ደፍሮ መናገር የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል ብላ አዲስ ማለዳ አታምንም።

የፕሬስ ውስጣዊ ችግሮችን በተመለከተ በዋናነት የሚነሱት ሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ አለመሥራት ናቸው። ይህም የሆነበት ምክንያት በሙያና ሥነ ምግባር የታነጹ ጋዜጠኞች ይልቅ በልምድ የሚሠራበት መስክ መሆኑ፣ በግልጽ ወገንተኝነትን በሥራ ላይ ማሳየት፣ ጠንካራ የሙያ ማኅበራት አለመኖር ሙያው በተፈለገው መንገድ እንዳያድግ ብሎም እንደዲቀጭጭ አድርጓል። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኀን ምክር ቤት አለመኖር ወይም በሚፈለገው ልክ ጠንካራ አለመሆኑ መገናኛ ብዙኀን ራስን በራስ የመቆጣጠሪያ ስርዓት ተግባራዊ እንዳያደርጉ እንቅፋት ሆኗል። ሙያውን ለፖለቲካ ዓላማ ማዋል በሰፊው መታየቱ ለሙያው መቀጨጭ ከላይ ከተጠቀሱት በይበልጥ አስተዋጽዖ አድርጓል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ውጫዊ ምክንያቶችን በተመለከተ አገሪቱ ከነበረችበት አፋኝ ሁኔታ በመጠኑ ከፈት መደረጉ መረጃ በሚሰጡ ተቋማት (በተለየ በመንግሥት) አሁንም ድረስ ከፍርሐት ቆፈን አለመውጣት፣ መረጃን አደራጅቶና በተፈለገው መልክ አለማስቀመጥና በተፈለገው መጠንና ፍጥነት አለመስጠት፣ አንዳንድ የመንግሥት ቢሮዎች ጨርሶውኑ መረጃ ለመስጠት ክፍት ያለመሆን ሊቀረፉ ያልቻሉ የቀድሞ ውርሶቸ እንደሆኑ አዲስ ማለዳ በተግባር ያየችው ለመሆኑ ምስክርነቷን ትሰጠለች። ከዚህም በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ኀይሎች ለጋዜጠኞች ደኅንነት አስጊ የደቦ ጥቃት እና ዛቻ እያደረሱ ቢሆንም መንግሥት ለሙያተኞቹ በቂ ጥበቃ ማድረግ ላይ አላተኮረም።

ሌላው መገናኛ ብዙኀን ያላቸው ውስን ተደራሽነት ሳይጠቀስ መታለፍ የለበትም። መገናኛ ብዙኀን ውሱን በሆኑ ቋንቋዎች ብቻ መጠቀማቸው ለውስንነታቸው ዓይነተኛ ሰበብ ሆኗል። ከውስን ተደራሽነት ጋር ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ በተለይ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሥርጭት በአዲስ አበባ ብቻ ተገድቦ ነው ያለው፤ በዚህም መገናኛ ብዙኀን ሚናቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ መሰናክል ሆኗል።

በውጫዊ ጫናዎች ላይ በተለይ አሳሪ ሕጎች ተጠቃሽ ናቸው። በርግጥ መንግሥት አሳሪ የሆኑትን ከፕሬስ ጋር የተገናኙ ሕጎችን ወደ ማሻሻል ሒደት መግባቱ አዎንታዊ እርምጃ ነው በማለት አዲስ ማለዳ ታደንቃለች። ይሁንና የሚሻሻሉ ሕጎች የሚመለከታቸውን ሁሉ በማሳተፍና በጥንቃቄ መታየት እንዳለባቸው ጨምራ ታሳስባለች።

መንግሥት እየወሰደ ካለው አዎንታዊ እርምጃዎች መካከል የሚመደበው የፕሬስና ተግባቦት ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ሒደት ላይ መሆኑ ይበረታታል። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የሚዲያ ፖሊሲ እንደሌላት ልብ ይሏል! ፖሊሲው አሁን እየታየ ካለው የፕሬስ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ዘርፉ ወደ ኢንዱስትሪነት እንዲያድግ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብላ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

በመሆኑም አዲስ ማለዳ የዘንድውን የዓለም ዐቀፍ የፕሬስ ቀን ስናከብር በፕሬስ ላይ የተሰማሩት የሙያ አጋሮቿ ሙያችንን ለማሳደግ፣ የሙያ ሥነ ምግባራችንን ለመተግበር እንዲሁም ገለልተኝነታችንን (ውግንና የሌለን ስለመሆናችን) በሥራችን ለማስመስከር፥ በጎ ተመክሮዎችን ለመለዋወጥ ጠንካራ የሙያ ማኅበር ወሳኝ መሆኑን አምነን ለጠንካራ ማኅበር እውናዊነት ለመሥራት አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታቀርባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here