የፀጥታ ኀይሎች የአረናን ጽሕፈት ቤት በረበሩ

0
461

ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) እና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የተባሉ ኹለት አዳዲስ ፓርቲዎች ከአረና በወጡ አባሎች ተቋቁመዋል

የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል፣ ፖሊስና ሚሊሻዎች በመቀሌ የሚገኘውን የዓረና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝና ያለፓርቲው አመራሮች እውቅና መበርበራቸውን የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አንዶም ገብረ ሥላሴ ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በጽሕፈት ቤቱ ጎን የሚገኙ ቤቶችም የህገወጥ ብርበራው ሰለባ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።

ሕወሓት በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ መሆኑን ያስታወቁት አንዶም፥ በፍርሃት ስሜት ሕዝቡን ወደ ባሰ አፈና እየከተተውና ፓርቲዎችም በተጠናከረ መንገድ ከሕዝቡ ጋር የሚያደርጉትን ግንኙነት ለማደናቀፍና በአመራሮቹ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ለማድረስ ተግቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕወሓት በዓረና ላይ እየፈጸመ ያለው ጥቃት እየተጠናከረ መጥቷል የሚሉት አንዶም፣ በሰላማዊ መንገድ የሚደረጉ ትግሎችን ወደ ጎን በማለት ወጣቱን የማዋከብና የማፈን ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ ይወነጅላሉ። በቀጣይም ይህንን ያደረጉትን የጸጥታ አካላትም ሆነ የክልሉን መንግሥት በሕግ የሚጠይቁ መሆኑንና እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በተያያዘ፣ የፓርቲው ኹለት ከፍተኛ አመራሮች ከድርጅቱ በመልቀቅ አዲስ ፓርቲ ያቋቋሙበት ምክንያት አዲስ ማለዳ ላቀረበችላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አንዶም፥ ከፍተኛ አመራሮች የሚለው ስህተት መሆኑን ገልጸው፤ የለቀቁትም በፈቃዳቸው እንጂ በቅራኔ ምክንያት አለመሆኑን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ወደ ፓለቲካ ትግሉ የመቀላቀል ሒደት ላይ እንዳለ የገለጸው ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) የሚል ሥያሜ የያዘ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት በቀድሞ የዓረና አመራሮችና አባላት እንዲሁም ሌሎች የትግራይ ተወላጆች የተመሰረተ መሆኑን ለጀርመን ድምፅ ገልፀዋል።

ትግራይ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆንዋ የሚገልፀው የፖለቲካ ድርጅቱ ከዚህ በመነሳት ሁሉን ዐቀፍ ለውጥ የሚፈጥር የድርጅት ስትራቴጂ በመያዝ ለመንቀሳቀስ ወደ ፖለቲካ ትግሉ መግባቱን አብራርቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነው ሳምንት ራሱን ያስተዋወቀው ሌላ የፖለቲካ ድርጅት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ የሚል ሥያሜ አለው። ሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ይዞ የሚንቀሳቀስ ብሔርተኛ ፓርቲ እንደሚሆን የገለፀው ሳልሳይ ወያነ ትግራይ፣ በትግራይ ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት እታገላለሁ ብሏል።

ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ባወጣው የመጀመርያው መግለጫ የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት አድርጎታል የሚለው ትግልና የተጎናፀፈው ድል ይጠቅሳል። በ1930ዎቹ አጋማሽ በትግራይ የነበረው ‘ቀዳማይ ወያነ’ በሚል የሚታወቀው አርሶአደሮች በአፄው ስርዓት ላይ ያደረጉት ተቃውሞ እንዲሁም ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በትግራይ በሕወሓት፣ ግገሓትና ሌሎች ያልተደራጁ እንቅስቃሴዎች ተጋድሎ ተቀጥያ መሆኑ ይገልፃል። ሳልሳይ ወያነ የፖለቲካ ድርጅት በሒደት የተፈጠሩ የፖለቲካ ችግሮች በመጥቀስ ለፖለቲካዊ ችግር ፓለቲካዊ መፍትሔ የግድ ያስፈልጋል ይላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here