ፓርቲው በ348 የምርጫ ወረዳዎች መዋቅር ዘረጋሁ አለ

0
730

የፊታችን ግንቦት 1 እና 2 መሥራች ጉባኤውን በኢትዮጵያ የስብሰባ ማዕከል የሚያካሂደው ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈርሰው ከወረዳ በሚጀምር ውህደት የሚመሰርቱት አዲሱ ፓርቲ ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 የገቢ ማሰባሰቢያ የራት ግብዣ አዘጋጅቷል።

ፓርቲ ሆኖ ለሚመሰረተው ድርጅት የምናወጣቸው ወጪዎች አሉ፤ ያሉት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ፣ ከመሥራች ጉባኤው ጋር ተያይዞ በየወረዳው ያሉ የተደራጁ አባላቶች ስለሚመጡ፣ ከዛ ጋር ተያይዞ ለምንሠራቸው ሥራዎች የሚረዳ የገቢ ማሰባሰቢያ ራት መዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። የእያንዳንዱ ትኬት ዋጋ 1500 ብር ሲሆን፣ ከ700 በላይ ትኬት ተሽጦ፣ 320 ሰዎች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል ብለዋል።

በሚቀጥለው ሳምንት ግንቦት 1 እና 2 መሥራች ጉባኤው ይካሄዳል። ፓርቲው ከሸፈናቸው የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ 1700 አባላቶች ተገኝተው በተመረጡበት የምርጫ ወረዳዎች በሙሉ አዲስ አበባ ይመጡና መሥራች ጉባኤው ይካሔዳል። የመሥራች ጉባኤው የፓርቲውን ረቂቅ መተዳደሪያ ደንቡ÷ ስያሜና አርማ ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፤ የፓርቲውን መሪዎችም ይመርጣል።

ሁሉም ፓርቲዎች የራሳቸውን ኅልውና አክስመው አዲስ ፓርቲ እንደሚመሠርቱ የነገሩን ናትናኤል፣ ግንቦት ሰባትም ሚያዝያ 29ኝ የሚከስምበትን ጉባኤ እንደሚያካሔድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ፓርቲው ለቀጣዩ ምርጫ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ውጤታማና በጥራትና ጥናት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብና ሥያሜ በሚጸድቅበት በዚህ ቀን የድርጅቱ ሊቀመንበርና መሪ እንደሚመረጥ ታውቋል። አዲሱ ፓርቲ በዋናነት የዜግነት ፖለቲካንና ማኅበራዊ ፍትሕን ማዕከል ያደረገ እንደሚሆን ናትናኤል ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነውን የብሔር ፓለቲካ ወይም ዘውገኝነትን በመተው በግለሰብ ላይ የተመሰረተ መብትንም የሚያስቀድም ይሆናል ብለዋል።

“በዜግነት ላይ የተመሰረተና አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ብቻ በእኩልነት የሚታይበት አገር ለመመሥረት እንታገላለን። የምንመሰርተው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለምም እሱን ማእከል ያደረገ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

አዲሱ ፓርቲ ከሌላው ጊዜ ለየት ባለ መልኩ ከታች ወደ ላይ የሚደራጅ መሆኑን የሚናገሩት ናትናኤል፣ የሚኖረው አደረጃጀት ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ 547 የምርጫ ወረዳዎች የነዋሪዎች መዋቅር እንደሚመሰረት ነግረውናል። እስካሁንም መዋቅሩ በመላ ኃገሪቱ በሚገኙ 348 ወረዳዎች መዘርጋቱን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡ ቀጣዩ አገር አቀፍ መርጫ ከመካሄዱ በፊት በሁሉም የምርጫ ወረዳዎች መዋቅር እንደሚዘረጋና 547 ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንደሚያቀርብ ታውቋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here