ዮሐንስ ነሲቡ የተባለው ትውልደ ኢተዮጵያዊ ለአሜሪካ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጥ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወሰነው መሰረት ባለፈው አርብ፣ ሚያዚያ 25/ 2011 በአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ባልደረቦች ተይዞ አሜሪካ ገባ። በኹለቱ አገራት መካከል የወንጀል ተጠርጣሪን አሳለፎ የመስጠት ስምምነት ባይኖርም ወደፊት ሊኖር በሚችል ተመሳሳይ ትብብር እንዲሁም እያደገ በመጣው የኹለቱ አገሮች ትብብር አማካኝነት መንግሥት ውሳኔ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለአሜሪካ መንግሥት የፃፈው ደብዳቤ አስረድቷል።
ግለሰቡ በአሜሪካን አገር በቨርጂኒያ ግዛት ኹለት የኢትዮጵያ የዘር ሃረግ ያላቸውን ሔኖክ ዩሐንስን እና ቅድስት ሰሜነህ የተባሉ ኢትዮጵያ አሜሪካዊያንን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በአሜሪካው የምርመራ ቢሮ (ኤፍ ቢ አይ) ክትትል ሲደረግበት እንደቆየ ለማወቅ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ኹለት ዓመታት ሲኖር የነበረው ተጠርጣሪው በአሜሪካ የምርመራ ቢሮ ልዩ አውሮፕላን ተይዞ ዳላስ አየር ማረፊያ ገብቷል። የምርመራ ቢሮው እንዳስታወቀው ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ የትም ቢደበቅ ወይም ምንም ያህል ጊዜ ቢቆይ መንግሥት ያለሰለሰ ጥረት አድርጎ እንደሚመልሰው አስታውቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠርጣሪውን አሳልፎ ለመስጠት ላደረገው ትብብር ምስጋና ተችሮታል።
ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011



