የኤርትራውያን እምባ

0
1011

ርእሶም ኪዳነ (ለደኅንነቱ ሲባል ሥሙ የተቀየረ) ተወልዶ ያደገው በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ነው። ርእሶም የተወለደው ኤርትራ ተገንጥላ ሉዓላዊነቷን ካወጀች ኹለት ዓመታት በኋላ ነበር። ርእሶም ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ኤርትራ የነበረችበት ሁኔታ በብዙ ዓለም አገራት የተወደሰ ነበር።

በርግጥ በወቅቱ ኤርትራ ፈጣን ኢኮኖሚ ካስመዘገቡ አገራት ተርታ ትመደብ የነበረ ሲሆን፥ መሠረተ ልማቷም ከብዙዎቹ አፍሪካ አገራት የተሻለ፣ ምጣኔ ሀብቷም የተረጋጋ ከሚባሉ አገራት ተርታ ይመደብ ነበር። ሕዝቦቿም ጠንካራና በመላው ኢትዮጵያ በምርታማነታቸው የሚታወቁ ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ከአንድ ትውልድ በኋላ በርእሶም የወጣትነት ዘመን ላይ ያለው የኤርትራውያን ሁኔታ ከዚህ ፈፅሞ የተለየ ነው። እንደ ርእሶም ያሉ ወጣቶች በግዴታ ወታደር እንዲሆኑ በመደረጋቸው ትምህርታቸው ከ12ኛ ክፍል ለማቋረጥ ተገደዋል። “እንኳንስ ለመማር ቀርቶ አገራችን ላይ በነጻነት ለመቀንሳቀስ አልቻልንም” ይላል ርእሶም የችግሩን ክብደት ሲያስረዳ።

11ኛ ክፍል ሲደርስ የኤርትራ ጦር ማሠልጠኛን የተቀላቀለው ርእሶም ተምሮ ራሱን የመለወጥ ፍላጎት ቢኖረውም በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው መንግሥት ለውትድርና የተቀመጠው ገደብ ተግባር ላይ ባለማዋሉ ርእሶም እንደ ሌሎች አገራት ወጣቶች በሚፈልገው ሙያ ተምሮ ሥራ መያዝ አልቻለም።

“አገሬን ወታደር ሁኜ ማገልገሌ ደስተኛ ቢያደርገኝም ገደብ ባለመኖሩ በሕይወቴ ተስፋ እንድቆርጥ አድርጎኛል” ይላል ርእሶም። “በጎረቤት አገራት የሚኖሩ የእኔ ዕድሜ እኩያዎች ዩንቨርስቲ ተመርቀው ሥራ ሲይዙ እኔ ግን የሳምንት እንኳን ወጪዬን የማይሸፍን ገንዘብ በየወሩ እየተቀበለኩ ሕይወቴን እንድመራ ተገድጃለሁ” ሲል ያማርራል የ25 ዓመቱ ወጣት ርእሶም።

በኑሮ ክብደት ቢማርርም በባለፈው ዓመት መጨረሻ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ሰላም ለማውረድ መሥማማታቸውን ተከትሎ ርእሶም ተስፋ ሰንቆ ነበር። “ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ኤርትራን ከረገጡ አንስቶ የወረደው ሰላም ለአገሬና ሕዝቦቿ ለውጥ ያመጣል ብዬ አስቤ የነበረ ቢሆንም ከምግብ ዕቃዎች መርከስ ባለፈ ሕይወታችን ላይ የታየ ለውጥ የለም” ይላል ርእሶም። “አሁንም በኤርትራ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቱ ቀጥሏል፤ ወንድሞቻችን አሁንም በእስር ቤት እየማቀቁ ነው።”

ርእሶም ብቻውን አይደለም
እንደ ርእሶም ያሉ በአገራቸው ባለው ወቅታዊ ሁኔታና አመራር ተስፋ የቆረጡ ወጣቶች ቁጥራቸው ቀላል አይደሉም። የሥራ ዕድል ያለመኖሩ፣ የዜጎች የመንቀሳቀስና የመናገር መብት መገደቡ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስመራ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ ጥቂት ዕድለኛ ተማሪዎችን ከማስተማር በስተቀር ሥራ ማቆማቸው እና የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዙ የኤርትራ ወጣቶች በአገራቸው የኑሮ ሁኔታ ተስፋ እንዲቆርጡ ምክንያት ሆኗል።

በዚህም የተነሳ፣ በሕይወታቸው ኹለት ምርጫ እንዲኖራቸው ግድ ሆኗል። አንዱ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰዶ በምዕራብ አገራት ጥገኝነት መጠየቅ ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ ወታደርነት ሆኗል። ለዚህም እንደ ማሳያነት የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ከተከፈተ አንስቶ እየጨመረ የመጣው የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ ነው።

ድንበሩን መከፈት ተከትሎ በያዝነው ዓመት በመስከረም እና ጥቅምት ወራት ብቻ በየቀኑ ከ391 በላይ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ይህ የኤርትራ ስደተኞችም በኢትዮጵያ ብቻ ቁጥራቸው ከ200 ሺሕ የላቀ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። አሁን ላይ የኤርትራ ወጣቶችና በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ይበቃል ያሉ ይመስላል።

አዲስ ማለዳ በአስመራ ባደረገችው ምልከታ ብዙ ኤርትራውያን ከመንግሥት ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ተቃውሟቸውን ከመግለጽ ባሻገር በቅርቡ ሥራ ለጀመሩት ኤሪሳትና አሴና ሳተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያዎች መረጃ በማቀበልና አንዳንዶችም አስተያየታቸው መስጠት ጀምረዋል። በተለያዩ መኖሪያ ቤቶችም አዲስ ማለዳ ተገኝታ ባደረገችው ቅኝት ለአዳዲሶቹ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካች ሲኖራቸውን የተለያዩ ሙዚቃዊ ሂሶችና ድራማዎችን ኤርትራውያን ተቃውሟቸውን ለመግለጽ እየተጠቁሙባቸው መሆኑ መገንዘብ ተችሏል።

ኤርትራ እንዴት ሰነበተች?
ባለፉት 20 ዓመታት በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የታዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ኤርትራ ውስጥ ገና አልታዩም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከሦስት እስከ አምስት ሚሊዮን ሕዝቦች ይኖሩባታል ተብላ የሚታመነው ኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ሉዓላዊነቷን ካወጀች በኋላ መጀመሪያ ዓመታት ውስጥ ዴሞክራሲ ይኖራል ተብሎ በሕዝብ ዘንድ እምነት የነበረ ቢሆንም፥ ዛሬ በአምባገነንነታቸው የሚታወቁት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገሪቷን በበላይነት ላለፉት 27 ዓመታት ሲመሩ ቆይተዋል።

እንደ አገር ከተመሠረተች ምርጫ አካሔዳ የማታውቀው ኤርትራ ፓርላማዋ ሥራ ካቆመ 17 ዓመታት አልፎታል። የከተማ አስተዳደሮች፣ ከንቲባዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች የኤርትራ ጦርና የፓርቲው አባል ናቸው። አገሪቷ ሕግ አውጪም ሆነ ነጻ የሕግ ተርጓሚ የላትም። የግል የሚዲያ ተቋማት በኤርትራ ከተዘጉ ኹለት ዐሠርት ዓመታት ሊሆናቸው ነው። ኢትዮጵያ ከ40 በላይ ደረጃ ባሻሻለችበት የ2019 የፕሬስ ነጻነት ጠቋሚ ሪፖርት ኤርትራ ከዓለም አገራት ከመጨረሻ 3ኛ ደረጃን ይዛለች።

ከዛሬ 18 ዓመታት አንስቶ የታሰሩ ከ15 በላይ ኤርትራውያን ጋዜጠኞች አሁንም አልተፈቱም። መንግሥት ሳንሱር ሳያደርግ መጽሐፍ ማሳተም በኤርትራ በጥብቅ የተከለከለ ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የቀድሞ የአገሪቷ ፋይናንስ ሚኒስቴር ብርሃነ አብርሃ ጉዳይ ነው። ሚኒስቴር ብርሃነ የኢሳያስን አመራር በመተቸት መጽሐፍ ባወጡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ታስረው እስከ አሁን ያሉበት አይታወቅም። ከዚያም ባለቤታቸው አልማዝ ሀብተማርያም ከወራት በኋላ ታስረው፣ እርሳቸውም የት እንደገቡ አይታወቅም።

በርግጥ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ለኤርትራ አዲስ ነገር አይደለም። ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመከሰስ መብት፣ በእስር ቤት ውስጥ በአግባቡ መያዝ ኤርትራውያን ከተነፈጉ ኹለት ዐሥርት ዓመታት ሆኗቸዋል። ሌላው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ማሳያ ደግሞ የኤርትራ ዜጎች ቤት የመገንባት መብታቸውን መነፈጋቸው ነው። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአስመራ ነዋሪዎች እንደገለጹት ከጎረቤት አገራት ሲሚንቶ መገበያየትና ከዚያም ቤት መገንባት በኤርትራ ውስጥ እንደ ሕልም ይቆጠራል።
በርግጥ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበሮች ከተከፈቱ በኋላ አንዳንዶች በድፍረት ሲሚንቶ በመገበያየት ቤት ለመገንባት ቢሞክሩም መንግሥት ሕግ አስከባሪዎች እንዲያቆሟቸው አድርጓል። ሌላው ብዙዎች ለስደት የዳረገው አሳሳቢ ጉዳይ ገደብ የለሹ ብሔራዊ የውትድርና ስርዓት ነው።

ብሔራዊ ውትድርና
ኤርትራ ሉዓላዊነቷን ባወጀት ኹለት ዓመታት ውስጥ የወጣው የብሔራዊ አገልግሎት አዋጅ እንደሚያሳየው ሁሉም ዕድሜአቸው ከ18 እስከ 40 የሆኑ ኤርትውያን ብሔራዊ አገልግሎት በግዴታ መስጠት አለባቸው። ይሁን እንጂ፣ ሠልጣኞች በውትድርና ለመቆየት ፈቃደኛ ካልሆኑ በስተቀር አገልግሎቱ 18 ወራት መብለጥ የለበትም ይላል አዋጁ።

የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት እስከሚከሰት ድረስ የኤርትራ መንግሥት አዋጁን ተግባራዊ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላ ሕጉን አክብሮ አያውቅም። አንዳንዶች ከ18 ዓመታት በላይ በውትድርና በግዴታ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን ከውትድርና ባለፈ በግንባታና ትላልቅ እርሻዎች ላይ በአነስተኛ ክፍያ እንዲሠሩ ተገደዋል።

የ38 ዓመቱ ሮቤል በላይ በዚህ ችግር ውስጥ እንዲያልፍ ከተገደዱ ኤርትራውያን መካከል አንዱ ነው። ሮቤል ከ6 ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ከመሰደዱ በፊት ወርሐዊ ደሞዙ 1850 ናቕፋ ነበር። ከደሞዙ ለቤት፣ ለትራንስፖርት እና ምግብ ወጪዎች መንግሥት 1600 ናቕፋ የሚቆርጥበት ሲሆን፥ እጁ ላይ የሚደርሰው 250 ናቕፋ (500 ብር) ነበር። ይህ እንኳንስ አራት ልጆቹን ለማሳደግ ቀርቶ ለሮቤል ለራሱ የሚባል አይደለም። የሌሎች የኤርትራውያን ወጣቶችም ሕይወት ከዚህ የተለየ አይደለም።
‘ሂውማን ራይትስ ዋች’ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ባወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በውትድርና ግዳጅ ላይ የተሠማሩ ኤርትራውያን ለአካላዊ ጥቃት እና ብዝበዛ የተጋለጡ ናቸው። በተጨማሪ ከብሔራዊ ውትድርና ለማቋረጥ የሚሞክሩ ወጣቶች ላይ የኤርትራ መንግሥት እስከ ኹለት ዓመታት የሚደርስ እስራትና 1500 ናቕፋ (3000 ብር) ቅጣት ይጥላል፡ በተጨማሪ ብሔራዊ ውትድርና ያገለገሉ ኤርትራውያን ንግድ መክፈት፣ መንቀሳቀሷ ወረቀት የማግኘትና ሲም ካርድ የመግዛት መብት አይኖራቸውም።

በተጨማሪም ሕፃናት ብሔራዊ ውትድርና በመፍራት በትምህርታቸው አውቀው ክፍሎችን በመደጋገም ወጥመድ ውስጥ ላለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። መጣቶች በትምህርት ላይ ያላቸው ተስፋ ከከሰመ ሰንበትበት ብሏል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚያነሱት ቢማሩ ባይማሩም የብሔራዊ ውትድርና እንዲያገለግሉ መገደዳቸው ነው። በሌላ በኩል የሃይማኖት ነጻነት ኤርትራ ውስጥ ሲጣስ ተስተውሏል።

የእምነት ነጻነት ጉዳይ
በኤርትራ ከእስልምና፣ ኦርቶዶክስ፣ ሮማን ካቶሊክ እና ኢቫንጋሊካን እምነቶች በስተቀር ሌሎች እምነቶች በመንግሥት ተቀባይነት አላገኙም። ከ50 በላይ የይሖዋ ምስክርነት እምነት ተከታዮች ማይ ሰርዋ በተባለ እስር ቤት እንደሚገኙ ‘ሂውማን ራይትስ ዋች’ ያወጣው ሪፖርት ያሳያል። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም ሃይማኖታቸው በነጻነት እንዳያከናውኑ ተከልክለዋል። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የተቃወሙ የሃይማኖት መሪዎች በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርገዋል። ከ2007 አንስቶ ከፓትሪያክነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉ በኋላ በቤት ውስጥ እስር ላይ የሚገኙት አቡነ አንቶኒዮስ ለዚህ ማሳያ ናቸው።
ፓትርያርኩ ከ12 ዓመታት በኋላ አፈትልኮ ከኹለት ወራት በፊት በወጣ ቪዲዮ ላይ ያልተገባ እስር ላይ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፤ በፓትሪያርኩ ላይ የተፈፀመውን በመቃወም የዓለም ዐቀፍ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ማኅበር እሳቸውን የተኩትን አቡነ ዲስኮሮስ ሳይቀበላቸው ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።

ቁሞ ቀሩ የኤርትራ ምጣኔ ሀብት
የኤርትራ የምጣኔ ሀብት ዕድገት መጠን ለማወቅ አዳጋች ነው። ለለፉት ዐሥር ዓመታት የኤርትራ መንግሥት ምንም ዓይነት ጥናት ባለመደረጉ እንዲሁም እንደ አይ.ኤም.ኤፍ. ያሉ ተቋማት ምጣኔ ሀብቱን እንዲመዝኑ ፈቃድ አለመሰጠቱ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይነሳል።

ይሁን እንጂ፣ የዛሬ ዓመት የወጣ የአፍሪካ ልማት ሪፖርት እንደሚያሳየው የኤርትራ ኢኮኖሚ በ2018፣ 4 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። አገሪቷ ላሳየችው የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ምክንያት የማዕድን ዘርፍ ማደግ ሲሆን፣ ሐዋላም ቀላል የማይባል ሚናን ተጫውቷል። የኤርትራ ኢኮኖሚ መጠን ባለፈው ዓመት መጨረሻ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ደርሶ ነበር።

ባንኩ በምድረ ኤርትራ ዕድገት አለ ቢባልም በመሬት ላይ የሚታየው ከዚህ በፍፁም የተለየ ነው። ባለፉት በ27 ዓመታት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች አናሳ የነበረ ሲሆን በቴክኖሎጂ አንፃር አገሪቷ ወደ ኋላ እንድትቀር ምክንያት ሆኗል። በሌላ በኩል በኤርትራ የሚገኙ የንግድ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ከፍተኛ የብር መጠን አከማችተዋል በማለት መዘጋታቸው ለአገሪቷ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሌላ ምክንያት ሆኗል። በወር ከ5000 ናቅፋ በላይ ዜጎች ከባንክ እንዳያወጡ መከልከላቸው ችግሩን የበለጠ አብሶታል።

ኤርትራ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት አናሳ ነው። የዛሬ 2 ዓመት የወጣ የኦኢሲ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሰባት የማይበልጡ አገራት ጋር ግንኙነት ያላት ኤርትራ በዓመት 336 ሚሊየን ዶላር የሚጠጉ ዕቃዎችን የምታስገባ ሲሆን ወደ 371 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎችን ትልካለች።

ከሕጋዊ መንገድ ባሻገር፣ የኤርትራ ኮንትሮባንድ ንግድ በጥንካሬው ይታወቃል። በተለይም ከሱዳን የሚገቡ ዕቃዎች ብዙኀኑ የኤርትራ ሕዝብ ፍላጎቱን ለማሳካት ሲጠቀምባቸው ይታያል። በተለይም በሕጋዊ መልኩ ዕቃ ለማስመጣት አዳጋች በመሆኑ ብዙዎቹ ነጋዴዎች ኮንትሮባንድን ይመርጣሉ።

በርግጥ በቅርቡ ለኹለት ዐሥር ዓመታት ቆሞ የቀረው የኤርትራ ምጣኔ ሀብት ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ሥምምነት ተከትሎ ነቃ ያለ ይመስላል። ሥምምነቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ መነሳቱ ደግሞ የበለጠ መነቃቃትን ፈጥሯል። ነገር ግን ከሰላም ሥምምነቱ ማግስት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷ የምጣኔ ሀብቱን መነቃቃት ቀጣይነት አጠራጣሪ አደርጎታል።

አራቱም የሑመራ-ኡማነጀር፣ የዛላንበሳ፣ ራማ-ክሳድ ዒቓ እና ቡሬ-ደባይ ሲማ ድንበሮች በኤርትራ በኩል ተዘግተዋል። ድንበሮቹ ለመዘጋታቸው ይፋዊ ምክንያት ባይሰጥም የቪዛና ቀረጥ ጉዳዮች መልክ ለማስያዝ የተደረገ እርምጃ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁን እንጂ፣ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እርምጃውን በመቃወም ድንበሮች መከፈት ይገባቸዋል ሲሉ አስተያየታቸው ከሦስት ሳምንት በፊት በሰጡት መግለጫ ወቅት ሰንዝረው ነበር።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ጋር በኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የተጠናከረ ግንኙነት ማዳበር የሚያስችሉ ሰነዶች በኤርትራ መንግሥት ከወራቶች በፊት ቢልክም ምላሽ እንዳላገኘ ምንጮች ይገልጻሉ። በተለይም በኢትዮጵያ በኩል የኹለቱን አገሮች ግንኙነት ሕጋዊና ተቋማዊ መልክ ለማስያዝ ቢሞከርም ከኤርትራ በኩል ምላሽ በአፋጣኝ አለመሰጠቱ ጉዳዩን አክብዶታል።

ዋዜማ ሬድዮ የዛሬ ወር ባወጣው ዘገባ መሠረት ኢትዮጵያ ባቀረበችው ሰነድ ላይ አሰብን የመጠቀም ፍላጎት ብታሳይም ከኤርትራ ባለሥልጣናት በኩል ኢትዮጵያ ምፅዋን እንድትጠቀም መገፋፋት እንዳለ ያሳያል።

ይሁን እንጂ፣ ሚያዝያ 17፣ 2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው መግለጫ በሰጡበት ወቅት ድንበሩ ለምን ተዘጋ ለሚለው መልስ ባይሰጡም፣ የኹለቱን አገራት ግንኙነት ተቋማዊ ቅርፅ ለማስያዝ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት
ከ1880ዎቹ በፊት ኤርትራ የአሁኑ ኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል እንደነበረች የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። በኹለቱ አገራት መካከል ልዩነት መፈጠር የጀመረው ጣልያን ኤርትራን በቅኝ ግዛት ከያዘች በኋላ ነበር። ከዚያም የኹለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ በተደረጉ ሥምምነትቶች በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ለማጣመር ተችሎ ነበር። ነገር ግን፣ በ1962 ንጉሠ ነገሥቱ ፈዴሬሽኑን በማፍረስ ኤርትራ በመውረር የኢትዮጵያ ክፍል በማድረጋቸው ነጻ አውጪ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ የኤርትራ ብሔርተኝነት እንዲጠነክር ምክንያት ሆኗል። በኋላም የኤርትራ ሕዝቦች ነጻነት ግንባር (የአሁን ሥሙ የሕዝቦች ንቅናቄ ለዴሞክራሲና ለፍትሕ) ጠንካራ ሽምቅ ታዋጊ በመሆን ለ30 ዓመታት ታግሎ የደርግን መንግሥት ከኤርትራ በማስወጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ወታደራዊውን መንግሥት ከቤተ መንግሥት እስከ ማስወጣት ደርሰው ነበር። ከዚያም ኤርትራ ነጻነቷን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በግንቦት 24፣ 1991 ማወጅ ችላ ነበር።

ኤርትራ ሉዓላዊነቷን ካወጀች በኋላ የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የነበረው የፖለቲካና ምጣኔ ሀብታዊ ግንኙነት ጥሩ የነበረ ሲሆን፥ በተለይም ኤርትራውያን በአዲስ አበባ በሌሎች ከተሞች ንግድ ላይ የነበራቸው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አልነበረም። በወቅቱም፣ የኤርትራ ነጋዴዎች በዓመት እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ምርቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር ይገበያዩ ነበር። ይህ ጥሩ ግንኙነት ከስድስት ዓመታት በላይ ሊዘልቅ ግን አልቻለም።

በ1998 ኹለቱ አገራት እስከ ዛሬ በአፍሪካ ታሪክ ትልቅ ደም መፋሰስ የታየበት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። ለኹለት ዓመታት በቆየው ጦርነት ከመቶ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሲያጡ ከ20 ሺሕ በላይ ኤርትራውያን ሞተዋል። በተጨማሪም ወደ 100 ሺሕ የሚጠጉ የኹለቱ አገራት ዜጎች ደግሞ ከመኖሪያቸው በጦርነቱ የተነሳ ሊፈናቀሉ ችለዋል።
ጦርነቱን የጀመረው ማን እንደሆነ እስካሁን እልባት ያልተገኘለት ጥያቄ ቢሆንም፥ በአገሬ ሀብት ኤርትራ ያልተገባ ጥቅም ልታገኝ ሞክራለች በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት መክሰሱና የኤርትራ መንግሥት ብርን በድንገት አቁሞ ናቕፋ በሥራ ላይ ማዋሉ ለጦርነቱ መነሳት እንደ ምክንያት ይነሳል። ከዚህ ባሻገር የኹለቱ አገራት መሪዎች ያልተገባና ጤነኛ ያልሆነ ግንኙነት ለጦርነቱ መከሰት ሌላው ምክንያት ነው።

ይሁን እንጂ፣ ብዙኀኑ የፖለቲካ ልኂቃን በዚህ ሐሳብ ቢሥማሙም የኹለቱም አገራት መንግሥታት የጦርነቱ መነሳት የባድመ ከተማን ይገባኛል ጥያቄ ጨምሮ የድንበር ጉዳይ ሲሉ እርስ በርሳቸው ሲካሰሱ ከርመው ነበር። ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ለ20 ዓመታት ከአነስተኛ ግጭቶች በስተቀር ‘ያለ ጦርነት፣ ያለ ሰላም’ የኹለቱ አገር ግንኙነት ሊቀጥል ችሏል። ይህ በእንዲህ እያለ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ ኤርትራ በኹለቱ አገራት ሰላም እንዲመጣ ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታዎችን (ማለትም የአልጀርስ ሥምምነት ይከበርልኝ ጥያቄ) የኢትዮጵያ መንግሥት እፈፅማለሁ በማለታቸው የኹለቱ አገራት ግንኙነት እንዲታደስ ምክንያት ሆኗል።

ታኅሣሥ 3፣ 1993 በቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ እና የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተፈረመው የአልጀርስ ሥምምነት ግቦች በኹለቱ አገራት መካከል የባላንጣነት መንፈስን ማቆም፣ በ1992 የተፈረመው የሰላም ሥምምነት እንዲፈፀም ማድረግ፣ በእስር ላይ ያሉ የጦር ምርኮኞችና ሌሎች ግለሰቦች ወደ የአገራቸው እንዲመለሱ ማስቻልና ኹለቱ አገራት በየግዛቶቻቸው ላሉ ዜጎች ሰብኣዊ ክብር እንድያደርጉ ድልድይ መሆን ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ ሥምምነቱን ብትቀበልም ለለፉት 10 ወራት ከሰላሙ ሥምምነት ባሻገር ሲፈፀም የታየ የድንበር ማካለል ምንም ዓይነት ሥራ የለም። ይህም አዲስ ማለዳ በአስመራ ተገኝታ ባደረገችው ቅኝት በኤርትራውያን ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል።

በተለይም በቅርቡ መተላለፍ የጀመሩት የኤሪሳትና አሴና የሳተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያዎች መከፈት ተከትሎ እየበዛ በመጣው ተቃውሞ ላይ ከሚገለጹ አጀንዳዎች መካከል የሥምምነቱ ተግባራዊ አለመደረግና የድንበር አለመካለሉ ናቸው። በተለይም፣ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ ከብሔርተኝነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት እንኳን ያለነው የሔዱትም ቢሆኑ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ እየሰፋች እያደገች እየተጠናከረች ትመጣለች ማለታቸው በጣቢያዎቹ የመነጋገሪያ ርዕስ ከመሆንም አልፎ ከፍተኛ ጥሬጣሬን በኤርትራ ሕዝብ ዘንድ ፈጥሯል።

አዲስ ማለዳ በአስመራ ተገኝታ ባደረግችው ቅኝት ምናልባትም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ይህን የተናገሩት ኤርትራን የኢትዮጵያ አካል ለማድረግ ፍላጎት አላት የሚል ፍራቻ አስነስቷል። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በየነ ሃጎስ የተባሉ (ሥማቸው የተቀየረ) ግለሰብ እንደገለጹት በተደጋጋሚ በአስመራ ውስጥ በተቃዋሚዎች በድብቅ ለሚሰራጩ መልዕክቶች እንደ አንድ አጀንዳ የሚነሳው የኹለቱ አገራት መሪዎች ድብቅ የሆነ ሥምምነት እንዳለና ይህም ውሕደት እስከ መፍጠር የሚደርስ እንደሆነ ያትታል።

ባለፈው ወር በተዘጋጀ የአዲስ ወግ ውይይት ላይ ተመሣሣይ ጥያቄ መነሳቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር ) ምላሽ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል። በንግግራቸውም አቅላይነት የተጠናወተው የፖለቲካ ሁኔታ ነው ያለው በማለት ኤርትራና ኢትዮጵያ ያላቸው ግንኙነት መሪዎች ግንኙነት ይመስላል ተብሎ የሚውራው ስህተት እንደሆነ ቁጣን ባዘለ ንግግራቸው ገልጸዋል።

እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በኤርትራዊያን ዘንድ አልጀርስ ሥምምነት አፈፃፀሙ ላይ ጥርጣሬ የሰፈነ ይመስላል። በየነ እንደሚሉት ከሆነ ድንበሩን ማካለል ለኤርትራ የሞትና ሽረት ጉዳይ ነው። በተለይም የኢትዮጵያም መንግሥት ሆነ የኤርትራ በድንበሩ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን እስካሁን አለማማከራቸው የኮሚሽኑ ውሳኔ መቼ ድረስ ይፈፀም የሚለው ገደብ አለመኖሩ የበለጠ እንዲጠራጠሩ ምክንያት እንደሆነ በየነ ይገልጻሉ።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ለመመሥረት መወሰኗን ተከትሎ በምፅዋ ሜሪታይም ማሠልጠኛ ወታደሮቿ እንዲሠለጥኑ የኤርትራ መንግሥት ተሥማምቷል የሚል መረጃ በመላው ኤርትራ በመሠራጨቱ ሌላ ጥርጣሬን ፈጥሯል።
የጅቡቲ ፕሬዘዳንት ከፈረንሳይ መጽሔት ጁቶን አፍሪክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል በምፅዋ ለመገንባት ተሥማምታለች ማለታቸው ጥርጣሬው የበለጠ ከፍ እንዲል አድርጎታል። ፈረንሳይ 113 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማገዝና የባሕር ኃይል አገሪቷ እንድትገነባ ለማድረግ ቃል መግባቷ ይታወሳል።

ኢትዮጵያም ከ1991 ጀምሮ ባሕር ኀይሏን በድጋሚ አሠልጥኖም ወደ ሥራ ለማስገባት ለኤርትራ ጥያቄ አቅርባ አዎንታዊ ምላሽ አግኝታለች መባሉን የኤርትራው መረጃ ሚኒስቴር የማነ ገብረመስቀል በቲውተር ገጻቸው ይህ መረጃ ከእውነት የራቀ ነው መሆኑን አስተባብለዋል።

ይኣክል (ይበቃል)
ካለፈው የፈርንጆች ዓመት መጨረሻ አንስቶ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ኤርትራውያን በአንድነት ይኣክል የሚል እንቅስቃሴ ጀምረዋል። በኤርትራ የሚኖሩ ወጣቶችም ቢሆን ተቃውሞውን በመደገፍ በግድግዳዎች ላይ “ኢሳያስ ውረድ፤ አገራችንን እንጠብቅ” የሚል መፈክር በመጻፍ ተቃውሟቸውን አልፎ አልፎ ቢሆንም ሲገልጹ ይታያል።

በሌላ በኩል፣ በአስመራ በሌሊት ላይ መፈክሮች የያዙ ወረቀቶች በከተማው በምሽት ወቅት አንዳንዴ እንደሚበተኑ ምንጮች ገልጸዋል። ለብዙ ዓመታት ፕሬዝደንት ኢሳያስን ይተካሉ ተብሎ በኤርትራውያን ዘንድ የሚታመንባቸው የአገሪቷ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር ስብሃት ኤፍሬም ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ተቃውሞ መጠናከሩን ማሳያ መሆን ይችላል።

በካናዳ፣ ቤልጄየም፤ ሲውዘርላንድና ሌሎች የአውሮፓ አገራት ያሉ ኤርትራውያን የየራሳቸውን መሪ በመምረጥ መቃወም ከጀመሩ መንፈቅ ዓመት ሆኗቸዋል። እስከዛሬ ከነበሩት ተቃውሞዎች ይህንን ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር የኢሳያስ መንግሥት ደጋፊ የነበሩ ኤርትራዊያን ተሳታፊ መመሆናቸውን ነው።

በተለይም የኢሳያስ አፈወርቂ ልጅ የሆነው አብረሃም ቀጣ ፕሬዚደንት ሊሆን ይችላል የሚል መረጃ በመላው ዓለም መሰራጨቱ የዲያስፖራ ማኅበረሰቡ ሕዝባዊ ዴሞክራሲና ፍትህን (PFDJ) በጥርጣሬ ዓይን እንዲመለከተው ምክንያት ሆኗል ሲሉ የፓለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።

በሌላ በኩል የመጀመሪያው የኤርትራ አምባሳደር በኢትዮጵያ የነበሩት ሓይለ መንቆሪዮስ በኤርትራ ዴሞክራሲ ለመገንባትና የሽግግር መንግሥት የሚቋቋምበት መንገድ ላይ ለመምከር ውይይት ተደርጎ ነበር። በአፍሪካ ኅብረት የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ተወካይ በነበሩት ሓይለ በተዘጋጀው ውይይት ላይ 70 ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና ያላቸው ባለሙያዎች፣ ዲፕሎማቶችና በተለያዩ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ ኤርትራውያኖች ተሳትፈው ነበር።

በኤርትራ ያለው አምባገነን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ በማድረግ ዴሞክራሲ ማስፈን አንዱ የውይይቱ አጀንዳ ነው። ይኣክል የተባለው የተቃውሞ አንቅስቃሴ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል። በውይይቱም ተሰብሳቢዎች በዋነኝነት የኤርትራ ባለሙያዎችንና ወጣቶችን ማሰባሰብና ለሕዝቡ የመረጃ ምንጮች በማስፋት ዓላማቸውን ለማሳካት ግብ አስቀምጠዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here