ውስብስቡ የአፋር-ሶማሌ ግንኙነትና የሦስቱ ቀበሌዎች ዕጣ ፈንታ

0
980

የምሥራቃዊ ኢትዮጵያ ኹለቱ ክልሎች አፋርና ሶማሌ ውጥረት ውስጥ የገቡ ይመስላሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ከአራት ዓመታት በፊት በታኅሣሥ 2007 ላይ ሦስት በሶማሌ ክልል ይተዳደሩ የነበሩ ቀበሌዎችን ወደ አፋር ክልል እንዲዛወሩ መፍቀዳቸው እና ከአፋሩ አቻቸው ኢስማኤል አሊሴሮ ጋር መፈራረማቸው ነው። አሁን ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበትና ፌደራላዊ ስርዓትን ተግባራዊ ካደረገበት ሰዓት ጀምሮ ለአለመግባባቱ መንስኤ የሆኑት ሦስቱ ቀበሌዎች በሶማሌ ክልል ውስጥ ይተዳደሩ ነበር።

ይሁን እንጂ ሦስቱ ቀበሌዎች ማለትም አዳኢቱ፣ ገርብ ኢሳ እና እንዱፎ የ2008 በጀት ዓመት በጀታቸውን ከሶማሌ ክልል ሳይሆን ከአፋር ክልል ተበጅቶላቸው፣ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን ሰንደቅ አላማ በይፋ እያውለበለቡ በአፋር ክልል ሥር መተዳደር ጀመሩ።

ሦስቱ ቀበሌዎች ወደ አፋር ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር ሥር እንዲሆኑ በኹለቱ ክልሎች የተፈረመው የጋራ ስምምነት ላይ ለረጅም ዘመን ሰላምና ልማት ርቋቸው የነበሩ ሕዝቦችን ወደ ሰላምና ልማት ተሳታፊነት በማሸጋገር የቀጠናውን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚል ዓላማን ያነገበ ነበር። በዚሁ የመግባቢያ ሰነድ ላይ የአዳኢቱ ከተማን በሚመለከት በሚሌ ወረዳ ሥር የሚተዳደር ሲሆን የሚኖረውን የአስተዳደራዊ ወሰን የአፋር ክልል መንግሥት ከሱማሌ ክልል መንግሥት እና ከፌደራል መንግሥት ከተወጣጡ የጋራ ኮሚቴ ጋር በመሆን ማካለል ሥራ እንደሚሠራ በግልፅ ተደንግጓል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በሦስቱም ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ፍቃዳቸው አልተጠየቀም፣ ሕዝበ ውሳኔ አልተካሔደም፣ የፌደራሉ ባለድርሻ አካል ፌደሬሽን ምክር ቤት እንኳን ጉዳዮን እንዲያየው አልተጠየቀም። መሐል አገርን ከጅቡቲ በሚያገናኘው ዋና መስመር ላይ የሚገኙት ሦስቱ ቀበሌዎች ከጅምሩም በአፋር ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር ዙሪያቸውን ተከበው መሃል ላይ መገኘታቸው የጉዳዩን ውስብስበነት ይበልጥ እንዲጨምር አድርጓል። በዚህም ምክንያት ከየትኛውም የሶማሌ ክልል አስተዳደር ወደ ሦስቱም ቀበሌዎች ለመሔድ የአፋር ክልልን ማቋረጥ ግድ ይላል።

የሦስቱ ቀበሌዎች የማንነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በሥያሜያቸው ላይም ያለመግባባቶች ተከስተዋል። ከቀበሌዎቹ አንዱ የሆነው “ገርብ ኢሳ” በሶማሌ ክልል ዘንድ የሚታወቅበት መጠሪያ ሲሆን፥ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ደግሞ ገዳማይቱ በሚል እንደሚጠራ የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። ገዳማይቱ የሚለውን ሥያሜ ነዋሪዎቹ እንደማይቀበሉትና በዚህም ቅሬታ እንዳለባቸው ይነገራል። ከዚህም በተጨማሪ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ሦስቱንም ቦታዎች በወረዳ ደረጃ እንዳዋቀራቸው እና እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የቻሉ ወረዳዎች መሆናቸውን አውጆ ሲተዳደሩ ኖረዋል። ነገር ግን በ2007 የክልላዊ አስተዳደር ለውጥ ከተደረገባቸው በኋላ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ሦስት ራሳቸውን የቻሉ ቀበሌዎች በመሆን ዝቅ ወዳለ አስተዳደራዊ መዋቅር ተሸጋግረዋል።

ከአራት ዓመታት የአፋር ክልል አስተዳደራዊ ቆይታ በኋላ ታዲያ እነዚህ ሦስት ቀበሌዎች የማንነት ጥያቄ አንስተዋል። በአካባቢውም አለመረጋጋት እና ብጥብጥ የዕለት ተዕለት ተግባር ሆኗል። በቅርቡም የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማን በአደባባይ አቃጥለው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በሦስቱም ቀበሌ በስፋት የሚኖሩት “የኢሳ” ጎሳ አባላት ሲሆኑ የአሁኑ በሦስቱም አካባቢዎች የተነሳው የወሰን አከላለል ጥያቄ ባለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ የተከሰተውን በአፋርና በኢሳ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት እንዳያባብሰው ተፈርቷል። በተለይ ደግሞ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ከዓመታት በፊት ወደ አፋር ክልላዊ መንግሥት እንዲዛወሩ የተደረጉትን ሦስት ቦታዎች ስምምነቱን ሽሯል። ይህንም ተከትሎ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ በሚያዚያ 26/2011 ለጀርመን ድምፅ በሰጠው መረጃ ኹለቱን ክልሎች ወደ ለየለት ግጭት የሚመራ ውሳኔ እንደሆነ ጠቁሞ ውሳኔው በደምብ ሊጤንበት የሚገባ እንደሆነ አሳስቧል።

የሦስቱን ቀበሌዎች አከላለል ውዝግብ በተመለካተ በሰላምና ደኅንነት የግጭት አፈታት ዙሪያ በርካት ጥናቶችን በሶማሌ ክልል ያካሔዱት ኤልሻዳይ መስፍን የጉዳዩን ውስብስበነት “ከመጀመሪያውም አከላለሉ ችግር እንዲፈጥር ተደርጎ ነው የተካለለው” ሲሉ ይጀምራሉ። በአፋር ክልላዊ መንግሥት አስተዳደር መሃል ላይ በሶማሌ ክልል የሚተዳደሩ ቦታዎች መኖር አስተዳደራዊ አለመረጋጋትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ባለሙያዋ ይናገራሉ። ግልፅ እና ሕገ መንግሥታዊ አካሔድን ባልተከተለ መንገድ ሦስቱም ቦታዎች እንዲዘዋወሩ መደረጉ በጊዜው የነበረው አስተዳደር ሕገ መንግሥቱን በይፋ የጣሰበት መንገድ ለመሆኑ ያስረግጣሉ። አካባቢውን በሚገባ የሚያውቁት ኤልሻዳይ በተጠቀሱት ሦስት ቦታዎች የሚገኙት ነዋሪዎች የሥነ ልቦና ውቅራቸው ከአፋር ይልቅ ወደ ሶማሌ እንደሚያደላ ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ ዓይነተኛ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ በሦስቱ ከተሞች የሚገኙት የኢሳ ጎሳዎች መሆናቸው እና የኢሳ ጎሳም በሶማሌ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ጎሳዎች ከኦጋዴን ጎሳ ቀጥሎ በቁጥር ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው። እንደ ኤልሻዳይ አስተያየት ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ቅርበት ያለውን ሕዝብ ፈቃዱ እና ምርጫው ሳይጠየቅ በአንድ አዳር በሌላ ክልል አስተዳደር ሥር እንዲሆን ማድረግ “የለየለት ሕገ ወጥነት” ነው ይላሉ።

ኤልሻዳይ ቀጥለውም በአካባቢው ስለሚስተዋለው ከግጦሽ መሬት ጋር በተገናኘ ስለሚከሰተው ግጭት ሙያዊ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል። አካባቢው አርብቶ አደሮች በስፋት ስለሚኖሩበት እና የአከላለል ሁኔታውም ግልፅ ባለመሆኑ ግጭቱ እንዲባባስ ያደርጋል ይላሉ። አያይዘውም የግጦሽ መሬት ችግር እንኳን እንደዚህ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የተካለለ እና የነዋሪዎች ቅሬታ በሚስተዋልበት ቦታ ቀርቶ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እውቅናን ባገኙ የአገራት ድንበሮች ላይም ግጭቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። በዚህም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበሮች በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን የግጦሽ መሬትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶችን ለአብነት ጠቅሰው፥ በዚህ ረገድ ባለፉት ኻያ ዓመታት አንፃራዊም ቢሆን ሰላም የነበረው የኢትዮጵያ ድንበር ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምትጋራው ድንበር እንደሆነ አስታውሰዋል።

በመጨረሻም ስለ ሦስቱ ከተሞች ዕጣ ፋንታ ይሆናል የሚሉትን የመፍትሔ ሐሳብ ሲያስቀምጡ፥ “አንድ ጊዜ የተበላሸ ውሳኔ ተወስኗል” ሲሉ ይጀምራሉ። ሕዝበ ውሳኔን እንደ መጀመሪያ አማራጭ የሚያስቀምጡት ኤልሻዳይ በየትኛው ክልል የመስተዳደር ምርጫውን ለነዋሪዎች ቢተው መልካም ነው ይላሉ። ለዚህ ደግሞ የቅማንት የማንነት ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ ተካሒዶ የመጣውን መፍትሔ በማውሳት ሕዝበ ውሳኔውም ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልታከለበት ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here