የኢንዱስትሪ ፓርኮች የወጪ ንግድ አርባ በመቶ ጭማሪ አሳየ

0
469

በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ከሚገኙት ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በ2011 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት የተመዘገበው የወጪ ንግድ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ታወቀ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት ዘጠኝ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ማለትም ሐዋሳ፣ ቦሌለሚ፣ ቂሊንጦ፣ መቀሌ፣ ድሬዳዋ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብረሃን፣ አዲስ አበባ እና ጂማ በዘጠኝ ወራት ብቻ 103 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገባት መቻላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መኮንን ኃይሉ እንዳስታወቁት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ከፍተኛ የሥራ መቀዛቀዝ ታይቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ማንሰራራት በመጀመሩ ከፍተኛ ትርፍ ሊገኝ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ለተገኘው ገቢ በዋናነት ጨርቃጨርቅ እና አልባሳት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙ የተጠቀሰ ሲሆን ጫማ ፣ የቆዳ ውጤቶችና ሌሎች ምርቶችም ወደ ውጭ ተልከዋል። እቃዎቹ መዳረሻቸውን አድርገው ከተላኩባቸው አገራት አውሮፓና አሜሪካ በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን እስያ፣ አረብ አገራት፣ እና አፍሪካም በቅደም ተከትል ተቀምጠዋል።

በአሁኑ ሰዓት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት በተጨማሪ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለ70 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥም 16 ሺሕ የሚሆነው በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ እንደሆነ ታውቋል።

ይሁን እንጂ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ክዋኔ ኦዲት በመንግሥት ወጪ እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ በተገመገመበት ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሠራተኞች ፍልሰት 97 በመቶ ደርሶ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህም ጉዳይ ላይ ዳይሬክተሯ ሌሊሴ ነሚ ሲመልሱ ሠራተኞችን ፍልሰት በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ ባለድርሻ አካል አለመሆኑን እና በቀጥታ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ሼዶች የተከራዩ ቀጣሪ ባለሀብቶች እንደሚመለከታቸው አስረድተዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር በጥር ወር 2011 ላይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽንን ከ2007 – 2010 የክዋኔ ኦዲት በገመገመበት ወቅት በጊዜው ሥራ ላይ በነበሩት አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች 11 ሚሊዮን ዶላር በወር ገቢ እንደሚገኝና ከአቅም በታች መሆኑንም አስታውቆ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በወቅቱ ሥራ ላይ በነበሩት አምስቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኘውን ገቢ አስመልክተው ሲናገሩ ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ የሚታመን ቢሆንም እንደጀማሪ ግን ሊበረታታ የሚገባው ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተውበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here