የሰላም ሚኒስቴር በግጭቶች በመወጠሩ የ450 ሚሊዮን ብር የግዢ ሒደት መንጓተቱን ገለፀ

0
556

የኢፌዲሪ የሰላም ሚኒስቴር በክልሎች ፍላጎት መሰረት ለተለያዩ ሥራዎች እንዲውሉ ያቀዳቸው የ450 ሚሊዮን ብር የዕቃ ግዢ ሒደት መዘግየቱ ተገለፀ። ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ፣ ሚያዚያ 29 ባቀረቡበት ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቶች መፈጠራቸውን አስታውቀዋል።

የዘገየበት ምክንያት በግልፅ እንዲብራራ ከምክር ቤት አባላት በተጠየቀው መሰረት ሚኒስትሯ በዋናነት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያጋጠመ በመሆኑ እንዲሁም ሚኒስቴሩም በተለያዩ የአገር ውስጥ ጉዳዮች በመጠመዱ የግዢ ሒደቱ ችላ እንደተባለ አስታውቀዋል።

ከተመደበው 450 ሚሊዮን ብር ውስጥ በክልሎች ፍላጎት ተለይተው ግዢ እንዲፈፀምላቸው የታቀዱ ሌሎች መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ጨምሮ 12 ትራክተሮች፣ 180 የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮች፣ 6 ወፍጮዎች ይገኙበታል። ከክልሎች ፍላጎትም በመነሳት የሰላም ሚኒስቴር ከግዢ ኤጀንሲ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት ግዢው በሚኒስቴሩ በኩል እንዲፈፀም በመደረጉ የግዢው ሒደት በዋናነት ሚኒስቴሩን እንደሚመለከት ሙፈሪሃት አስታውቀው የሰላም ሚኒስቴር ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድና በአጭር ጊዜ ውስጥ ግዢው ተጠናቆ ለክልሎች እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል።

የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሰላም ሚኒስቴር በርካታ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሆነ ሙፈሪሃት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በሚቀጥሉት ስድስት አመታት ይተገበራል ተብሎ የጊዜ ገደብ የተያዘለት የቆላማ አካባቢ የኑሮ ማሻሻያና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ተቀርፆ በመጠናቀቅ ወደ ተግባር ለመግባት በዝግጅት ላይ ነው።

አርብቶ አደሩን ፈቃድና ድጋፍ ተመርኩዞ ሚመራ የመንደር ማሰባሰብ ስራም እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ ከዚህም ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ በሦስት ክልሎች ኻያ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት መገንባታቸው ታውቋል ። ተቋማቱም በጋምቤላ ክልል 15፣ በሶማሌ ክልል 2 እና በአፋር 3 ተገንብተዋል። ለዚህም ሙፈሪሃት ሲያብራሩ አርብቶ አደሮች በአንድ ቦታ ረግተው ባለመኖራቸው የሚያገኙት የማኅበራዊ ግልጋሎት ውስን ነው ሲሉ ጀምረው፥ አሁን የተቀረፀው ፕሮጀክት ግን መንደር በማሰባሰብ በአንድ አካባቢ ረግተው እንዲቀመጡ በማድረግ የጤና እና ትምህርት በዋናነት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ታስቧል ብለዋል።

ለአርብቶ አደሩ የገንዘብ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ከፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመሆን ወለድ አልባ ፋይናንስ አሠራር ሥልጠና ለ57 የክልል ባለድርሻ አካላት ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፥ 5564 አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 1 ሺሕ 359 አርሶ አደሮችን ማሰልጠን መቻሉን በሪፖርቱ ላይ ተመላክቷል። በዚህም መሰረት 19 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ለ1 ሺሕ 856 አርብቶ አደሮች ብድር ማሰራጨት ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here