“የአማራ ተወላጆች በሌሎች ክልሎች ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ተነፍጓቸዋል”

0
277

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት የአማራ ተወላጆች በሌሎች ክልሎች ላይ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት መነፈጋቸውንና የክልሉ ሕገ መንግሥት ከክልሉ ውጭ ስለሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የሚለው ነገር የለም ሲሉ የክልሉን መንግሥት ወቅሰዋል። በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔሮች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መብት ሰጥቷል፤ ያሉት የምክር ቤቱ አባላት፣ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ለምን ሌሎች ክልሎች ዕድል አልሰጧቸውም ሲሉም ጠይቀዋል።

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ያለው የሕዝብ ብዛት ሲታይ የበርታ እና የአማራ ብሔሮች ቁጥር እንደሚበልጥ ተናግረው፣ ይሁን እንጅ የክልሉ ሕገ መንግሥት የክልሉ የባለቤትነት ጉዳይ ለበርታ፣ ሽናሻ እና ሌሎችም ሲሰጥ አማራዎችን የባለቤትነት መብት ነፍጓል በማለት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል። የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥትም ስለ ኦሮሞ ሕዝብ እንጅ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለሚገኙ ሌሎች ብሔሮች አይገልጽም የሚሉትም በማሳያነት ቀርበዋል።

የፌደራል ስርዓቱ ለፌደራል መንግሥት እና ለክልል መንግሥት የሰጠው ሥልጣን ቢኖርም፣ ከመጠን በላይ የሥልጣን ባለቤቶች ክልሎች መሆናቸው ለችግሮች መፈጠር ምክንያት መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ማንሳታቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አሰማኸኝ አስረስ፣ መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በትክክል መወጣት ባለመቻሉ የክልሉን ሕዝብ የአገልጋይነት ስሜቱ እየተዳከመ ስለመሆኑ ከተወያዮቹ መቅረቡን ጠቅሰዋል። ሕዝቡ የመንግሥት አገልግሎት እያገኘ ያለው በሙስና እና በሌሎች ትስስሮች መሆኑን ማንሳታቸውንም አክለዋል።

የስደትና ሞት መበራከት አሳሳቢ መሆኑን ያቀረቡት አባላቱ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የክልሉ የመንግሥት አካላት ውስንነት እንደሚስተዋልባቸው ተናግረዋል። የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ያላቸውን እና የሌላቸውን አካላት በትክክል መለየት እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት። የተረጋጋ ሰላም እንዳይኖር የሚሠሩ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውም ተጠቅሷል። የፓርላመንታዊ ስርዓቱ በአገሪቱ እየተፈጠረ ላለው አለመረጋጋት ምክንያት በመሆኑ ሊጤን እንደሚገባውም ጠይቀዋል።

በሌላ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች የአስተዳደር እና የዲሞክራሲ መብታቸው እንዲከበር የተነሳው ጥያቄ ተገቢ በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚያቀርብ ማብራሪያ ተሰጥቷል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወርቅ ሰሙ ማሞ “ሁሉም ዜጋ ባለበት እንደ ሰው የመኖር፣ የመንቀሳቀስና ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲኖር መሥራትን ሁላችንም በኢትዮጵያ ካሰፈንን ችግሩን መቅረፍ እንችላለን” ብለዋል ።

ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ለአገራችን ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ ደግሞ ሰፊ ትኩረት የሚጠይቅ በመሆኑ በቀጣይ ሕዝቡ ተወያይቶ መልስ ቢሰጥበት የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ ተሰጥቶበታል።

ለሕግ አውጭውም ሆነ ለሕግ ተርጓሚው እንቅፋት እየፈጠረ ያለው በአብዛኛው አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ነው፤ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራው ነው፤ የአማራ ክልል የሰላምና ደኅንነት ስጋት መንስኤው በአብዛኛው የክልሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ነን የሚል ማብራሪያም ተሰጥቷል። በየደረጃው ያለን አስፈጻሚ አካላት ችግራችን ተነጋግረን ባለመፍታታችን ሕዝቡ ማግኘት ያለበትን ጥቅም እያገኘ አይደለም፤ በክልሉ እየታየ ካለው ወቅታዊ ለውጥ ጋር አብሮ ለመጓዝ ችግር ፈች ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል።

ሕገ ወጥነት እየተስፋፋ፣ ስርዓት አልበኝነት እየነገሰ፣ ችግሮች ሲከሰቱ አስፈጻሚ አካላት አለመፍታታቸውም ክፍተት መሆኑ በጉባኤው መገለጹን የተናገሩት አሰማኸኝ፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ሥራቸውን በቅንጅት እየሠሩ ባለመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተጋረጡበት መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት ይህን ጉዳይ ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የፌደራል መንግስቱ በመላ ሀገሪቱ ከዜጎች ሞት እና መፈናቀል ጋር ተያይዞ የሚታዩ አሉታዊ ገጽታዎችን መፍታት እንዳለበትም ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here