የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን በአምስት ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ባካሔደው የተጠርጣሪዎች ሰብኣዊ መብቶች አያያዝ ግምገማ፣ ተላላፊ በሽታ ያለባቸው ታራሚዎችን ከሌሎች ታራሚዎች ጋር ቀላቅሎ የመያዝ ችግሮች መኖራቸውን አስታወቀ። የሕክምና መስጫ ባለመኖሩ ተጠርጣሪዎች በራሳቸው ወጪ ለመታከም መገደዳቸውንም አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ተጠርጣሪዎች በምን ምክንያት እንደተያዙ አለመንገር፤ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኀይል መጠቀም፤ በፖሊስ መጥሪያ መያዝ፤ የተጠርጣሪዎች የመረጃ አያያዝ ክፍተት መኖሩን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ማርሴ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የፖሊስ ጣቢያዎችን ሕግና ደንብ አለማስተዋወቅ ችግሮች መኖራቸውን ያስታወቁት ማርሴ፥ ስለተጠርጣሪዎች ሁኔታ ለቤተሰብ መረጃ አለመስጠት ችግሮች መኖራቸውም ገልጸዋል።
ቃል በመቀበል ሒደት ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባ መኖር እንዲሁም ተጠርጣሪዎች የሚሰጡት ቃል በማስረጃነት እንደሚቀርብባቸው አለመንገር እና ተነቦላቸው ተስማምተው እንዲፈርሙ አለማድረግ የአብዛኞቹ የፖሊስ ጣቢያዎቹ መገለጫ መሆናቸው ታውቋል።
ተጠርጣሪዎችን በ48 ሰዓት ውሰጥ ፍርድ ቤት አለማቅረብ፤ የፍርድ ቤት ማዘዣ ሳይዙ/ሳያሳዩ ቤት መበርበር፣ የግል ሕይወት የመከበር መብት መጣስ፤ የፖሊስ ዋስትና አሰጣጥ ሒደት ግልጽ አለማድረግ በአጠቃላይ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት አለመከበር በስፋት መኖራቸውን ኮሚሽኑ ተገንዝቤያለሁ ብሏል ።
ከትግራይ እና ሐረሪ ጣቢያዎች በስተቀር በፖሊስ ጣቢያዎች ያሉ መጠለያዎች/የተጠርጣሪ ማቆያዎች ለዚሁ ዓላማ ታስበው ያልተሠሩና አየር የማያስገቡ በመሆኑ በቂ ብርሃን የሌላቸው ሲሆን በአጠቃላይ ጣቢያዎቹ ግን የምግብ እና የውኃ አቅርቦት፣ የመኝታ ቁሳቁስ የሌላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
መጸዳጃ የመጠቀሚያ ጊዜ ገደብ መጣል፤ ልዩ ትኩረት የሚሹ ተጠርጣሪዎች (ሴቶች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን) የተለየ አያያዝ አለመኖር፤ በተለይ ለሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ አለመኖር፤ ሴቶችና ወንዶችን በግቢ ለይቶ አለመያዝ ጥናቱ በተደረገባቸው ጣቢያዎች ያልተሻሻሉ ነገሮች ናቸው።
የኮሚሽኑ የግምገማ ሪፖርት፥ አሁንም ክትትሉ በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች የሚታዩ የሰብኣዊ መብት ጥሰት መንስዔዎች በመሆናቸው በትኩረት ሊሠራባቸው እንደሚገባ አመላክቷል።
በታራሚዎችም ሆነ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚደርሱ የሰብኣአዊ መብት ጥሰቶች በምንም ምክንያት ለመታገስ የማይገቡ መሆናቸውን ያሳሰበው ኮሚሽኑ፣ እነዚህ ችግሮች በቀጣይ መሻሻል እንደሚገባቸውና መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ ችግሩ አለባቸው ከተባሉ ክልሎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የምግብ፣ ንፁሕ የመጠጥ ውሃ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦትና ጥራት መጓደል እና ሌሎች በክትትሉ የተገኙ የታራሚዎች የሰብኣዊ መብት አያያዝ ችግሮች ላይ መክሮ የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድና ጅምሮችን አጠናክሮ ለመቀጠል ከስምምነት ላይ ደርሷል።
በተጫሪም ኮሚሽኑ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ እና በሐረሪ ክልሎች በሚገኙት ማረሚያ ቤቶች ባካሔደው የተጠርጣሪዎች ሰብኣዊ መብቶች አያያዝ ግምገማ፣ የአመክሮ እና የይቅርታ አሰጣጥ ስርዓት የአሠራር ክፍተትና ግልጽነት አለመኖርና አድሎአዊ አሰራር በሰፊው መስተዋሉን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011



