ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ኅልውና እና ለዜጎች ደኅንነት!

0
358

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ፈታኝ ወቅት ላይ ነው የሚገኙት። በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ መብላት እና ነግዶ ማደር አስቸጋሪ ተግዳሮቶች ተጋርጠውባቸዋል። ከዓመት በፊት የተጀመረው የለውጥ ሒደት ሲበሰር ዜጎች የተደሰቱት ሁሉም ጥያቄዎቻቸው በአንድ ጊዜ መልስ ያገኛሉ በሚል የተሳሳተ አረዳድ ሳይሆን፥ ቢያንስ ሰላም ወጥቶ የመግባት እና ሠርቶ የመብላት ነጻነቶቻችን ይረጋገጡልናል በሚል ነው። ይሁን እንጂ ከዓመት በኋላ መንግሥታዊ ኃይሎች ያደርሱት የነበረው ግፍ እና በደል ዛሬ መንግሥታዊ ባልሆኑ ኀይሎች እየተፈፀመ ነው። ዛሬም የዜጎች የደኅንነት ሥጋት እና የነጻነት ማጣት ስሜት አለ። ዛሬም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ ለመገንባት እንዳይችሉ ከፍተኛ ፈተናዎች እንደተጋረጡባቸው ነው። ዛሬም አገረ-መንግሥቱ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት ነው። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የዜጎች አስተዋፅዖ አስፈላጊ ቢሆንም፥ ዋናው ኀላፊነት ግን የመንግሥት መሆኑ በፍፁም መዘንጋት የለበትም።

ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሸጋገር ያለባት የሕልውናዋ ጉዳይ ስለሆነ እንደሆነ ተደጋግሞ ይነገራል። ይሁን እንጂ በቁርጠኝነት መንገድ የሚጠርግላት አመራር አላገኘችም። ከዚህ በፊት በርካታ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ዕድሎች ከሽፈዋል፤ ይህንኛው ዕድልም እንደባከኑት ዕድሎች እንዳይባክን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም የሚከተሉት እርምጃዎች ወሳኝ ናቸው፦

የኀይል የበላይነት፦ በማንኛውም የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የኀይል የበላይነት መኖር የሚኖርበት በመንግሥት እጅ ነው። አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ግን የተደራጁም፣ ያልተደራጁም ታጣቂ ኀይሎች ነዋሪዎችን ከቀያቸው እያፈናቀሉ፣ የነጋዴዎችን እና ተጓጓዦችን መንገድ እየዘጉ ሰላማዊ ኑሮን እያስተጓጎሉ ይገኛሉ። በሌላ በኩል እነዚሁ የታጠቁ ኀይሎች የመንግሥት ታጣቂዎች ለገዢው ፓርቲ ወገንተኛ ናቸው የሚል ክስ ይመሠርታሉ። ሁለቱም ትክክል ስላልሆኑ አፋጣኝ ምላሽ ይሻሉ።

በመንግሥት እና በገዢው ቡድን መካከል ያለው መቀላቀል መቆም አለበት፤ ይህ እንደለውጡ ሒደት ተቆጥሮ በፍጥነት እና በተግባር መከናወን አለበት። የመከላከያ ሠራዊቱ እና የየክልሉ የፀጥታ አካላት በትብብር እና የሥልጣን ክፍፍላቸውን ባከበረ መልኩ መከነናወን አለበት። የትኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ቡድን የመንግሥትን የኀይል የበላይነት ማስከበር አለበት፤ የፀጥታ አካላቱም ይህንን በማረጋገጥ ለዜጎች ደኅንነት ዋስትና እንዳለ ማረጋገጥ አለባቸው።

የሕግ የበላይነት፦ ነጻነት ማልት ስርዓት አልበኝነት ማለት አይደለም። ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው። ምንም እንኳን ወቅቱ የፖለቲካ ሽግግር ቢሆንም ከሕግ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መኖር የለባቸውም። በአገራችን የሚስተዋለው የተለያዩ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ተግባራት ከሕግ ውጪ ከሆኑ በፍትሐዊ የክስ ሒደት ሊጠየቁ ይገባል። ከዚህ በፊት የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት ያደረጉ እስሮች እና ክሶች በመኖራቸው እና የዳኝነት ሒደቱም ለአስፈፃሚው አካል ታዛዥ በመሆኑ ምክንያት የፍትሕ ስርዓቱ ታማኝነት ማጉደሉ ይታወቃል። በዚህም ምክንያ የፍትሕ ስርዓቱ ተአማኒነት ሊያጣ ይችላል። ሆኖም ግልጽነት ላይ የተመሠረተ እና ፍትሓዊ መሠረት ያለው የሕግ ሒደትን ግን የሚቃወሙ ዜጎች የሉም። ስለሆነም፣ ለሰላም መደፍረስ እና ለዜጎች ደኅንነት አደጋ የሆነ ድርጊት ላይ የተጠመዱ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች ሕጋዊ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረግ ለዜጎች ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል።

የሥልጣን ክፍፍል፦ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የፌዴራል ስርዓት እየተከተለች ቢሆንም በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልሎች መካክል የሥልጣን እና ኀላፊነት ክፍፍል አይስተዋልም፤ ቢስተዋልም አይከበርም። ከዚህ ቀደም የነበረው ስርዓት በተግባር እጅግ የተማከለ በመሆኑ ምክንያት የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ከሚገባው በላይ የተለጠጠ ነበር። ስለሆነም ክልሎች የፌዴራል መንግሥቱን ትዕዛዝ ከማስፈፀም በቀር ሥልጣን አልነበራቸውም። አሁን ደግሞ በተቃራኒው ክልሎች የተለጠጠ ሥልጣን ወስደው የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን አልባ አስመስለውታል። በየክልሉ ለሚፈፀሙ የደኅንነት ሥጋት የሚፈጥሩ ግጭቶች የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ እንዳያበጅ የክልል መንግሥታቱ እምቢተኝነት አስቸግሯል። የተዘጉ መንገዶችን ለማስከፈት እና የሚፈለጉ ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ ሳይቀር የክልል መንግሥታት ባለመተባበራቸው የፌዴራል መንግሥቱን ጥርስ አልባ አድርጎታል። ክልሎችም ይሁኑ የፌዴራል መንግሥቱ የየራሳቸው ሥልጣን እና ኀላፊነት አለባቸው። በኹለቱ መካከል በመከባበር ላይ የተመሠረተ የወል እና የተናጠል አመራር ካልተዘረጋ በስተቀር ይህ አደገኛ አካሔድ ለዜጎች ደኅንነት ፈተና ሆኖ ከመቀጠሉም ባሻገር፣ የአገሪቱን ኅልውና አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም።

በርግጥ አምና እና ካቻምና ኢትዮጵያ ከነበረችበት የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ነች ማለት ይቻላል። ሚያዝያ ወር ላይ በወጣው የ“መፍረስ አደጋ ያንዣበበባቸው አገራት ጠቋሚ” (“Fragile States Index”) መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2017 ወዲህ 5 ነጥብ 2 አሻሽላለች። ይሁን እንጂ ዛሬም የመፍረስ አደጋ ካንዣበበባቸው አገራት ተርታ ነው የምትመደበው፤ ከ178 የዓለም አገራት አንፃር 23ኛ የመፍረስ አደጋ ያንዣበበባት አገር ተብላ ተመድባለች። ከኢትዮጵያ የተሻለ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አገራት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያ እንደአገር ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና ካተረፈች በኋላ የተመሠረቱ አገሮች ናቸው እና አይመጥናትም። ስለሆነም፣ መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ በመስጠት የአገሪቱን ኅልውና እና የዜጎችን ደኅንነት ባስቸኳይ ያረጋግጥ።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here