የአተት በሽታ በአማራ ክልል ሦስት ዞኖች ተከሰተ

0
398

ከሚያዝያ 27/2011 ጀምሮ በአማራ ክልል በዋግህምራ ዞን አበርጌሌ ወረዳ፣ በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት ወረዳና በደቡብ ወሎ ዞን መሃል ሳይንት ወረዳ ከ130 በላይ ሰዎች በአተት በሽታ መያዛቸው ታውቋል። አራት ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል።

አበርጌሌ ወረዳ 56 ሰዎች በአተት መጠርጠራቸውንና ኹለቱ ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን እንዲሁም በጠለምት ወረዳ 63 ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው ኹለት ሰዎች ከበሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሽታ መከላከል ዳይሬክተር አሸናፊ አያሌው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። በበየዳ ወረዳ 3 ሰዎች እንዲሁም፣ በመሃል ሳይንት ወረዳ 8 ሰዎች በበሽታው መጠርጠራቸውን አስታውቀው ሕክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የአተት በሽታ ምልክቶች በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ታይቶ እንደነበር ያስታወቁት የኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር)፣ ይሁን እንጂ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ አተት አለመሆኑ መረጋገጡንና ምልክቱ ታይቶባቸዋል ተብለው የተጠረጠሩትም ታክመው መዳናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሁሉም ክልሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እንዲያከናውኑ የማንቂያና ማስጠንቀቂያ በደብዳቤ እንደተላለፈላቸውና በክረምቱ ወራትም የአተት በሽታ ሊከሰት ይችላል የሚሉ ግምቶች በመኖራቸው፣ በዞንና በክልል ደረጃ ፈጣን ምላሽ ሰጪ የሕክምና ቡድን ተልኮ እየተከታተለ እንደሚገኝ በየነ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከፌደራል አዲስ የፈጣን ምላሽ ሰጪ የሕክምና ቡድን ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው።

ለአማራ ክልል የአተት በሽታን ለማከም የሚያስችል የሕክምና ግብዓት አተት ወደ ተጠረጠረባቸው ወረዳዎች በፍጥነት ማቅረብ እንዲቻል በተለያዩ የመድኀኒት መጋዘኖች እንዲከማቹ እየተደረገ ሲሆን፣ ከፌደራል ሆስፒታሎች፣ ከኢትዮጵያ የመድኀኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም ከሕክምና ማስተማሪያ ሆስፒታሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች ተንቀሳቃሽ የኮሌራ ሕክምና መስጫ ማዕክል ለማቋቋም የሚያስችል ሥልጠና መሰጠቱም ታውቋል።

ንፁሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ማነስ፣ በአየር መዛባት ምክንያት የውሃ እጥረት፣ የጎርፍ ችግር መኖር፣ ከኅብረተሰቡ የአካባቢ፣ የግል፣ የውሃና የምግብ ንጽሕና አያያዝና አጠቃቀም ልማድ አለመዳበር ጋር ተያይዞ የተቅማጥ በሽታዎች ስርጭት በየጊዜው እንዲከሰት አስተዋጽዖ አድርጓል።

በተለይም በጎርፍ ምክንያት ምንጮች፣ ወንዞች፣ የውሃ ጉድጓዶች ስለሚበከሉ በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተቋሙ አስታውቋል።

በጸበል ቦታዎች የአተት በሽታ የመስፋፋት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ አደገኛ ጎርፎች ወደ ጸበሉ በሚገቡበት ወቅት፣ እንዲሁም በአካባቢው በርካታ ሰዎች ለመጠመቅ የሚመጡ በመሆናቸው፣ በበሽታው የተያዘው ሰው በቀላሉ በሽታውን ሊያሰራጨው ይችላል ብለዋል። በጸበል አካባቢዎችም ልዩ ትኩረት በመስጠት ቦታዎቹን በማጠርና ከሌሎች ወራጅ ውሃዎች በመከላከል የመጠበቅ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢንስትቲዩቱ ምክትል ዳይሬክትር በየነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ በተለያዩ በጥቃቅን በዓይን በማይታዩ ተዋህሲያን አማካይነት የሚከሰት በሽታ ሲሆን፣ ከንፅሕና መጓደል በተለይም፣ በተህዋሲያን በተበከሉ ምግቦች፣ የመጠጥ ውሃ እና በሌሎች መተላለፊያ መንገዶች ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here