ከሙስና ጋር በተያያዘ የዛሬማ ሜይ ዴይ ግድብ ሥራ አልጀመረም

0
994

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ወልቃይት ወረዳ የሚገኘው የዛሬማ ሜይ ዴይ ግድብ ሥራው ቢጠናቀቅም ተቆጣጣሪው ድርጅት በሙስና ወንጀል በመከሰሱ ሥራ መጀመር እንዳልቻለ ታወቀ። በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስኖ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፥ የግድቡ ሥራ ቢጠናቀቅም የተቆጣጣሪ ድርጅቱን በሙስና መከሰስ ተከትሎ ሕጋዊ ርክክብ ባለመደረጉ ወደ ሥራ አልተገባም ብለዋል። የግድቡን ግንባታ የአዋጭነት ጥናትና በአማካሪነት የሚሠራው ጣሊያናዊው ድርጅት ስቱዲዮ ጋሊ ኢንጅነሪንግ ሲሆን በሙስና ወንጀል በመከሰሰሱ ግድቡን ማስረከብ እንዳልቻለ ታውቋል።

እንደ ሚኒስትር ዲኤታው ገለፃ ዛሬማ ሜይ ዴይ ግድብ አንዳንድ ጥቃቅን ሥራዎች ካልሆኑ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በዋናነት ግን ወደ ሥራ ያልተገባው በድርጅቱ መከሰስ እንደሆነ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ማለዳ በመጀመሪያ ዕትሟ ሚኒስቴሩ የፕሮጀክቱን አስተባባሪ ዋቢ አድርጋ በሚያዚያ 2011 ግድቡ እንዲመረቅ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ለግድቡ ማስተንፈሻ ባለመሠራቱ ሊራዘም መቻሉን መዘገቧ ይታወሳል። በተያያዘም በግድቡ ላይ ለሚገነባው የውሃ ማስተንፈሻ ፕሮጀክት ተጨማሪ ከአንድ ዓመት እስከ ኹለት ዓመት እንደሚወስድም ይገመታል።

በክስ ላይ የሚገኘው እና የግድቡን ሥራ ሲከታተል የነበረው ድርጅት ስቱዲዮ ጋሊ የአዋጭነት እና የአማካሪነት ድርሻ እንዲኖረው የተደረገበት መንገድ ሕጋዊ አካሔዶችን የተከተለ እንዳልነበር ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ሥማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉት የሚኒስቴሩ ሥራ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፥ አማካሪ ድርጅቱ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ከመረከቡም በተጨማሪ የሠራቸው ሥራዎችም በሦስተኛ እና ገለልተኛ አካል አለመረጋገጡንም አስታውቀዋል።

ዛሬማ ሜይ ዴይ ግንባታውን ለማካሔድ በመጀመሪያ ደረጃ ተይዞለት ከነበረው የአራት ቢሊዮን ብር ከፍተኛ ሊባል በሚችል ሁኔታ 11 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ የገንዘብ መጠን በመጠቀም አጠቃላይ የግንባታ ወጪውን ወደ 15 ቢሊዮን ከፍ አድርጓል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በ2003 በጀት ዓመት ተጀመረው ግንባታው የሦስት ዓመታት የማጠናቀቂያ ጊዜ ተይዞለት ነበር። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ተጓቶ እስከ 2011 ዘልቋል።

የግድቦችን ጥራት በሚመለከትም ሚኒስትር ዲኤታው አብርሃ ሲናገሩ እስካሁን ይገነቡ የነበሩት ግድቦች በጥራት በኩል ችግሮች እንዳለባቸው እና ከዚህ በኋላ በሚገነቡት ላይ ግን በጥራት ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራበት አፅንዖት ሰጥተውበታል።

35 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪውብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ዛሬማ ሜይ ዴይ ግድብ በቀን 24 ሺሕ ቶን ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት አቅም ላለው የስኳር ፋብሪካ ዋነኛ ውሃ ምንጭ እንዲሆን ታልሞ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here