ከ16 ሺሕ በላይ ተፈናቃይ ነፍሰ ጡሮች መኖራቸው ተገለፀ

0
1049

• የዓይንና የእከክ በሽታ በሁሉም ክልሎች እየተዛመተ ነው

በአምስት ክልሎች በሚገኙ 65 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ መጠለያ ጣቢያዎች እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ 16 ሺሕ 361 ነፍሰ ጡሮች ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ እና 734 የሚሆኑ እናቶችም መውለዳቸውን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በተጨማሪም እነዚሁ በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ከቀያቸው ከተፈናቀሉ ዜጎች ውስጥ 11 ሺሕ 926 የሚሆኑ ፈቃደኛ ሴቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በአሁኑ ወቅት በሶማሌ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 91 የመጠለያ ጣቢያዎች ተመድበው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 744 የጤና ባለሙያዎች መኖራቸውን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) ተናገረዋል። በየጊዜው በተለያዩ ክልሎች እያገረሹ ያሉት ግጭቶች የተፈናቃዩን ቁጥር እየጨመሩ ከመሆኑም ባለፈ፣ ተገቢው እርዳታና ድጋፍ ለተፈናቃዮቹ እንዳይሰራጭ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በሚያዚያ 26 ዕትሟ፣ በጌዲዖ ዞን ጎቴቲ መጠለያ ጣቢያ በቆዳ ላይ እከክ፣ የዓይን ሕመም (ʻኮንጃክቲቫይተስʼ) እና የምግብ እጥረት በተለይ እስከ አምስት ዓመት ባሉ ሕፃናት ላይ የሚስተዋሉ የጤና እክሎች በአካባቢው እየተስፋፉ መሆኑንና ዘግባ ነበር። እነዚህ የዓይን እና የእከክ በሽታዎች በሶማሌ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ክልሎች በሚገኙ ጣቢያዎች መስፋፋታቸውን አክለው ገልጸዋል።

ተቋሙ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ብሎ ካስቀመጣቸው ስጋቶች መካከል፣ የአተት በሽታ ምልክቶች በታዩባቸው የአማራ ክልል ወረዳዎች የመንገድ ችግር መኖሩን ተናግሯል። በፀጥታ ችግር ምክንያት በአንዳንድ የተፈናቃይ ወገኖች መጠለያ ጣቢያዎች አገልግሎት መቋረጡና በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና አዳዲስ ተፈናቃዮች መኖራቸው ተጠቃሾች ናቸው።
ተፈናቃይ በጨመረ ቁጥርም የውሃ እጥረት እና በአንድ ቦታ ላይ የሚቆዩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለሚመጣ ችግሮች መባባሳቸው እንደማይቀር ኢኒስቲትዩቱ አሳስቧል። በአሁኑ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ በተለይ የብሔር ማንነትን መሰረት ባደረጉ ግጭቶች የተፈናቃዮች ቁጥር 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን የሰላም ሚኒሰቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮችን በ9 ወር ውስጥ መመለሱን አስታውቆ የፌደራል መንግሥቱ 1 ነጥብ 7 ኩንታል የእርዳታ እህል ማሰራጨቱንም ገልጧል። ከዚህ ውስጥ 692 ሺሕ የሚሆነው ከለጋሾች የተገኘ ሲሆን የተቀረው በመንግሥት የተሸፈነ ነው።

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በማኅበራዊ ገጹ ላይ በጎ ፈቃደኞችን አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቆ ከ176 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ባለሙያዎች ተመዝግበዋል። እነሱንም ለመመደብ ከክልሎች ጋር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል። የጤና ሙያ ማኅበራት አባሎቻቸው በበጎ ፈቃደኝነት እንዲያገለግሉና እንዲያበረታቱም ጠይቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here