የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንን ለመምራት ኀላፊነት የተሰጣቸው ግለሰቦች የሹመት ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ አይደለም ተባለ። ግንቦት 8/2011 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ቃለ መሓላ እንዲፈፅሙ የተደረጉት ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳስ ዘ ካቶሊካውያን በሰብሳቢነት እና የትነበርሽ ንጉሴ ደግሞ በምክትል ሰብሳቢነት ሲሆኑ፤ ኹለቱም ተሿሚዎች ቃለ መሓላ ከመፈፀማቸው አስቀድመው ሥራ መጀመራቸው ቅደም ተከተሉን የጣሰ ነው የሚል ቅሬታን አስነስቷል።
የኹለቱን ተሿሚዎች ለሕዝብ እንደራሴዎች ያቀረቡት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪው መስፍን ቸርነት፤ የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡ ሰብሳቢውና ምክትል ሰብሳቢው ሥራ ሙሉ በሙሉ አልጀመሩም፤ ይህ ደግሞ የሆነው በምክር ቤቱ ፊት ቆመው ቃለ መሓላ ባለመፈፀማቸው ነው ሲሉ አስተባብለዋል። የኮሚሽኑን ኀላፊዎች በተለመከተ የተሰጣቸውን ኀላፊነት የሚመጥን አስተሳሰብ እንዳላቸው እና ለሕዝቡ ምን ያህል ቅርብ እንደሆኑም ጥያቄ ተነስቶባቸው ምላሽ ከመንግሥት ተጠሪው ተሰጥቶባቸዋል። ከዚህ ቀደም ስለ ብቃታቸው በሰፊው የተዘረዘረ መሆኑን የጠቀሱት መስፍን፤ ከሕግና ከሞራል ጋር በተያያዘ እንከን የማይገኝላቸው ናቸው ብለዋል። አያይዘውም ወደ ሕዝቡ ያላቸው ቅርበትም ወረዳ ድረስ ወርደው አይሥሩ እንጂ በመገናኛ ብዙኀን ስለሰፊው ሕዝብ የሚሟገቱ ናቸው ብለዋል።
በመጨረሻም ሹመቱ በአራት ተቃውሞ እና በዐሥር ድምፀ ታዕቅቦ በአብላጫ ደምፅ ጸድቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011