የበጎነት እና የመልካም እናትነት ተምሳሌት የሆኑት የ84 ዓመቷ ዕድሜ ባለፀጋ አበበች ጎበና ዛሬ አቅማቸው የደከመ፣ ጤናቸውም የጎደለ ይመስላል። ሺዎችን በፍቅር ያሳደገው ልባቸው ታውኳል፣ ዘመናትን ወደ ኋላ ተጉዘው የተደረጉ ጥቃቅን ነገሮችን እንኳን የማይስቱት ደጓ እናት አበበች፥ ከዕድሜያቸው ጋር ተያይዞ የመዘንጋት ችግር አጋጥሟቸዋል። እንደዛም ሆኖ ግን ለእርጅና እጅ የሰጡ አይመስሉም አሁንም በቤት ውስጥ የሚያድጉትን ልጆች በዓይኖቻቸው ሳያዩ አይውሉም፣ ጩኸታቸውን ሳይሰሙ አያድሩም፣ እርጅና የማያደበዝዘው ሩኅሩኅነታቸው አሁንም እንዳለ ነው።
እኒህ እናት ሰብኣዊ ፍቅርን ያህል ዕዳ ተሸክመው የተወለዱ፣ ይህንኑ ረቂቅ ፍቅር ወደ ገሀድ እውነታነት ለውጠው የተስፋ ቢስነት ጽልመት በነገሰበት ቦታ ብርሃን፣ ረሃብ በሰፈነበት የዕለት እንጀራ፣ አይዞህ ባይ በሌለበት ብርታት፣ ልብ በሐዘን በተሰበረበትና ጉንጭ በእንባ በራሰበት እያበሱ የሚኖሩ ትልቅ እናት ናቸው።
ዛሬ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ በየጎዳናው ላይ ወድቀው የሚገኙ እንቦቀቅላዎች የሕይወት ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ነው። በዚች ምድር ላይ ብዙ ጨካኝና መጠፎ ሰዎች እንደሚፈጠሩበትም ሁሉ ብዙ ደጋግና የዋህ ሰዎችም ይወለዱበታል።
አበበችም ወላጅ አልባ ሕፃናትን በአንድ ቤት ሰብስበው የማሳደግ ሐሳባቸውን ሲተገብሩት ከባለቤቶቻቸው ጋር ፍቅር በሞላበት እና በመግበባት እንዲሁም ችግር ያልቃኘው፤ ስቃይ ያልጎበኘው ሕይወት ነበር የሚኖሩት። ይሁንና ወላጅ አልባ ልጆችን ሰብስበው በማሳደጋቸው “ሴትየዋ ጤናም የላትም እንዴ” እሰከማለት የደረሱ እንዲሁም ጤንነታቸውን የተጠራጠረ ዘመድ አዝማድ እርቋቸው ቤተሰቦቻቸውን ትዳራቸውን ያጡት እኚህ አዛውንት እናት በውስጣቸው የሚንቀለቀለው የሰው ልጆች ፍቅር በሰው ልጅ በራሱ እንዲጠሉና እንዲናቁ አድርጓቸዋል።
አበበች ግን ተስፋን ሰንቀው የጀመሩት የ1972 ጉዞ እጅግ ፈታኝ ቢሆንም ውጤቱ ግን መልካም ሆነላቸው። በኹለት ትናንሽ ሴት ልጆች የተጀመረውም ጉዞ ለብዙ ሺሕ ሕጻናት መንገድ ከፋች ሆነ።
አበበችም ለሚያሰድጓቸው ልጆች እናትም አባትም ናቸው። ለልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ሲያለቅሱ አልቅሰው ፣ ሲስቁም ስቀው አልፎም ሲራቡ ተርበው ያሳደጓቸው ልጆች “እዳዬ” እያሉ ይጠሯቸዋል።
የአበበች ጎበና የሕፃናት ክብካቤና ልማት ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ይትባረክ ተካልኝ ስለማሕበሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው በአሁኑ ጊዜ የእዳዬ ቤት ወለጅ አልባ የሆኑ ሕፃናትን ከመንከባከብ ባለፈ የማኅበረሰቡ ችግር ላይ የሚያጠነጥን ትልቅ ማሕበሩ ሆኗል። ይህ የሆነበት ምክንያትም የማኅበረሰቡ ችግሮች ሲቃለሉ እንዲሁም የሴቶችን ጉዳት ስንቀንስ ነው የሕፃናቱ ጉዳት ሊቀነስ የሚችለው። ማኅበሩም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጀ ላይ የሚገኙ ሴቶችን በተለያዩ መንገዶች አቅማቸውን አጎልብተው ለተለያዩ ማኅበራዊ ጠንቆች ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ይህም ገጠር ለሚገኙ ሴቶች ላሞችን ገዝቶ በመስጠትና ግንዛቤን በመፍጠር፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን በመንደር ቁጠባና ብድር በማደራጀት እና በማሰልጠን እንዲሁም ለበርካታ ሴቶች የመቋቋምያ ገንዘብ በመስጠት የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ ዕድል በመክፈት ክፍተኛ የሆነ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
ይትባረክም ስለ አበበች ያለውን ስሜት እንዲገልፅ በተጠየቀበት ወቅት ስለ እዳዬ መናገር አልችልም ምክንያቱም መደጋገም ከመሆኑም ባሻገር ተብሎ የማያልቅ ተሰምቶ የማጠገብ ንግግር ስለሚሆን በአንድ ቃል ልግለፅልሽ ብሎ “ዕድሜዬን ብቀይራት እና የእሷን ዕድሜ ቢሰጠኝ ደስ ይለኛል” በማለት ፈገግ ባለ ገፅታ፣ የብዙ ዓመት ፍቅሩን በአንድ ዓረፍተ ነገር ቋጫት።
ማኅበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከ3 ሺሕ በላይ ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናትን በእንክብካቤ በማሳደግ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል። እስከአሁንም 139 ሕፃናትን በጉዲፈቻ እንዲያድጉ ያሰረከብን ሲሆን መንግሥት ባወጣው ሕግ ምክንያት የውጪ አገር ጉዲፈቻን ከልክለናል። እንዲሁም 10 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናትን ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው ሙሉ ዕርዳታ እያደረግን የሚያድጉበት ሁኔታ የተመቻቸ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም በማኅበሩ ያሉ 34 ታዳጊዎች እንክብካቤ እያገኙ ነው ብለዋል።
እንዲሁም ከተለያዩ አገራት እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ ከማግኘቱም ባለፈ ማኅበሩ ውስጥ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎችንም ይሰራሉ። የሕፃናት ሕክምና ማዕከል፣ ትምህርት ቤት፣ የሹራብ ሥራና ማተሚያ፣ የእንጀራ ምርትና ባልትና ውጤቶች የሚገኙበት ሲሆን በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ ሁለገብ የልማት ማዕከል አለ። በማዕከሉም የወተት ተዋህፆ፣ የዘይት እና የጤፍ ምርቶችን እንዲሁም የዶሮና የከብት ምርቶች ይገኛሉ።
ማኅበሩ በባሕላዊና ዘመናዊ የምግብ ዝግጅቶች መስተንግዶ በማሰልጠን በየ6 ወሩ የሚያስመርቅ ሲሆን የ29ኛው ዙር ሰልጣኞችን ሐሙስ፣ ግንቦት 8 አስመርቋል።
በ1972ዓ.ም በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ከፍተኛ የድርቅና የረሃብ አደጋ ተከስቶ የነበረ ሲሆን በዚሁ ጊዜ አበበች ጎበና የግሸን ማርያምን ክብረ በዓል ለማክበር ወደ ስፍራው ሔደው ነበር። በአካባቢውና በምግብና ውሃ እጦት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ተጎድተው ለብዙ ችግር ተጋልጠው በመዘየታቸው ልባቸው ክፉኛ በሐዘን ተሰበረ። ሕይወታቸውን ከአደጋው ለማዳንና አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ወስነው ኹለት ሕፃናትን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ቤታቸው ተመለሱ። ይህ እንዳለ ሆኖ ያለ ተንከባካቢ የቀሩ ሕፃናትን በመሰብሰብ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕፃናቱን ቁጥር ወደ 21 አሳድገዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ችግሮችን ያስተናገዱት እናትም ሕጻናቱን ተንከባክበው ለማሳደግ ጥቃቅን ንግድን ከማካሔድ ባሻገር የተለያዩ ጌጣጌጣቸውን እና ንብረታቸውን ሸጠዋል። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታም ዶሮ ለማርባት ባዘጋጁት ትንሽ ጎጆ የተጀመረው የሕፃናት ክብካቤና ድጋፍ እጅግ ሰፍቶና አድጎ የበርካታ ሺሕ ሕፃናትን ሕይወት ታድጎና እየተዳገ ይገኛል።
ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011



