ባለኹለት አፍ መንግሥት

0
692

አንድ ዓመት ያስቆጠረው የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባሕርይ ከታዋቂው ገጣሚና ጸሐፊ ከበደ ሚካኤል “ኹለት አፍ ያለው ወፍ” ከሚለው ያመሳሰሉት ጌታቸው መላኩ፥ ንጽጽራቸውን ባነሷቸው ነጥቦች አስደግፈዋል። መንግስትም ባለኹለት አፍ ባሕሪይውን ተረድቶ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት መፍትሔዎች ማምጣት አለበት ሲሉም ይመክራሉ።

የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት የከርሞው ባሕርይና ተግባር የተሰኘውን የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤልን ምናባዊ ግጥም አስታወሰኝ። የታደሉት በልጅነታቸው ተረትና ምሳሌን እንብበው አጣጥመዋል፤ የኔ ታላላቆች ማለቴ ነው። እኔም እንጥፍታፊውም ቢሆን ደርሶኝ አንብንቤዋለሁ፤ በምናብም ተደስቼበታለው። ይህ ግጥም ኹለት አፍ ያለው ወፍ እንዴት በኹለቱ አፎች አለመስማማት፤ በተለይ የአንደኛው እኔ ብቻ፣ የኔ ብቻ ባይነትና እንዲሁም የሌላኛው እልህ ለሞት እንዳበቃው የሚያሳይ እጅግ ምስጢሩ የረቀቀ ግጥም ነው። የዛሬን አያድርገውና እኔም በቃሌ “ሸምጥጬው” ነበር። ምን ያደርጋል ዕድሜና “ከመጠን ያለፈ ትጋት” ይህንን ሁሉ የክፉ ቀን መጽናኛ ሀብት አሳጣኝ፤ አስረሳኝ። ብሶቴን ልተወውና ወደ ጉዳዬ ልመለስ። ግጥሙ ሲጀምር፡
እየለቃቀሙ የሚበሉለት፣
አንድ ወፍ ነበረ፣ ኹለት አፍ ያሉት።
እያለ ይቀጥላል።

በከበደ ሚካኤል ግጥም ውስጥ ከወፉ አንዱ አንገት ፈጣንና ለእኔ ባይ ስለሆነ ወፉ ባረፈበት ቦታ የተገኘውን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ ሁሉ ለሌላኛው አፍ ሳያስቀር ጥርግ አድርጎ ይበላዋል። ሌላኛው አፍም ምንም ሳይናገር ወፉ በበረረበት ቦታ ሁሉ ያንን ፈጣን አፍ እየተመከተ በሚያሳየው ራስ ወዳድናትና አልጠግብ ባይነት እያዘነ አይለየው ነገር አካል፣ አይደግፈው ነገር ጉዳት ሆኖበት ጊዜውን ይገፋ ነበር። ከበደ ሚካኤል እንደሚነግሩን ወፉ አንድ ቀን መርዛም ዛፍ ላይ ያርፋል። ወፉ ያረፈበት ዛፍ ፍሬ መርዛማ፥ ቢበሉት ወዲው የሚገል መሆኑን የተገነዘበው ዘግይቶ ነበር። በመሆኑም ፈጣኑና ለኔ ባዩ ወፍ ከመብላት ሲታቀብ ዘገምተኛው ወፍ ግን የዛፉን ፍሬ ለመብላት ለቀም ያደርገዋል። አላወቀውም ነበር። የዚህን ጊዜ ፈጣኑና ለእኔ ባዩ አፍ ፍሬው ገዳይ እንደሆነና ሞቱ ለኹለቱም እንደማይቀርላቸው እየተርበተበተ በመግለጽ ፍሬውን እንዳይበላው ይማጸነዋል።
ደካማው አፍ ግን ጥሩ ጥሩ ፍሬ በምፈልገው ጊዜ ካላገኘው አሁን የምግደረደርበት ምክንያት የለም የሚል መልስ ይሰጣል። በልቡ ግን ፈጣኑ አፍ ያደረሰበትን ጎጂ ስሜት ለመበቀል ያገኘውን አጋጣሚ ዳግም የማይገኝ መሆኑን በማመን ፍሬውን ይበላዋል። በዚህም ምክንያት ፈጣኑ አፍ ቢርበተበትም ወፉ ከዚያ ዛፍ ላይ ሳይነሳ በመርዛማው ፍሬ አማካይነት ሕይወቱ አለፈ።

የዐቢይ መንግሥትና ደካማው አፍ
“በለውጥ ላይ ነን፤ ለውጥ ይዞት የሚመጣ የማይቀር አለመረጋጋት እያጋጠመን ነው፤ ነገር ግን ሁሉንም በትዕግስትና በሕዝባችን ድጋፍ እንወጣዋለን” የሚለው የዐቢይ መንግሥት በእኔ ግንዛቤ በተለይ የደካማ አፍነቱን ሚና ተያይዞታል። ለምሳሌ የበዛ “የሕዝብ ግንኙነት” ሥራ ላይ መጠመዱ አንድ ጉዳይ ነው። የሕዝብ ግንኙነቱ ሥራ በራሱ ክፋት ባይኖርበትም ባለብን ግለሰቦችን በመካብ ወደ ማይወጡት አውቃለሁ ባይነትና መታበይ እንዳያደርሳቸው ያሰጋል። በዋናነት ግን እንደ ደካማው አፍ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ላይ መጠመዱ የሚያስከትለው ችግር ከባድ ነው። ምክንያቱም እጅግ የበዛ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በሒደት ራስን ብቻ መስማትና ሌላው የሚለው የፀረ ሰላም ወሬ ነው በሚል የከረመ የቀድሞው ኢሕአዴግ አባባል መልሶ እንዳይመጣ ያሰጋኛል።

ሌላው የመንግሥቱ የደካማ አፍነቱ መገለጫ “የበዛ” የሚመስል ትዕግስት ለጉዳዮች ሁሉ ማሳየቱ ነው። ከዚህ በፊት በአንድ አጋጣሚ በጻፍኩት መጣጥፍ እንደገለጽኩት ከአንድ ዓመት በፊት ለውጡ ተቀጣጥሎ ዕውን ሲመስልና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ሲለቁ ማንኛውም ወደ ሥልጣን የሚመጣ አካል በሦስት ክፍል የሚወጣው አሳሳቢ የቤት ሥራ እንደሚኖርበት ገልጬ ነበር። በመጀመሪያ በየቦታው የተከሰቱትንና እየተከሰቱ የነበሩትን ግጭትና መፈናቀሎች በማንኛውም መንገድ ማስቆም ነው። በኹለተኛ ደረጃ የሚኖረው ኀላፊነት ለመፈናቀሉ ምክንያት የሆኑትን ግለሰቦችና ተቋማት በሕግም በሞራልም መጠየቅ ነው። በሦስተኛ ደረጃ የሚኖረው ሥራ ዘላቂ የሆነ ለውጥን ለማረጋገጥ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከርና ራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

መንግሥት የመጀመሪውን የቤት ሥራ በከፊል ቢያልፍም ኹለተኛውና ሦስተኛው ላይ ግን የደከመው ይመስላል። ለዚህም ምክንያቱ እኔ ጋር ካልደረሰ በሚመስል የበዛ ትዕግስቱ ይመስለኛል ወይም ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ግን ያደናግር የሚለውን አገራዊ ብሒል ያስታውሳል።

ሌላው የደካማው አፍ መገለጫ በዐቢይ መንግሥት ላይ ሲንፀባረቅ የሚታየው የስትራቴጂካዊ ዕይታና ትኩረት ማነስ ነው። በእርግጥ ስትራቴጂ በአገሪቱ ትርጉማቸው ከተዛቡባቸው ቃላት መካከል አንዱ ነው። ለወትሮው አውሮፓን ከዓለም ጦርነት ውድቀት በኋላ ከውድቀት መንጥቆ ያወጣው በሁሉም መልክ የታየ የአመራርና የአስተዳደር ጥበብ እንዲሁም ጃፓንን፣ ቀጥሎ ደቡብ ኮሪያን አሁን ደግሞ ቻይናን ከድኅነትና ከብሔራዊ ውርደት አውጥቶ ከፍተኛ ደረጃ ያደረሰ ምትሀታዊ አስተሳሰብ መጠሪያ ቃል ሲሆን በእኛ አገር ሚንስትር እንኳን ለመሾም አሻግሮ ለማሰብ ልተቻለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። የብሔር ስብጥርን፣ የፖለቲካ መስመር “ትክክለኛነትን” ለማረጋገጥ ሲባል ብቻ የሚሠራው ሥራ የዐቢይ መንግሥት የደካማውን አፍ ባሕርያት አላብሶታል። መንግሥትና አመራሩ የረጅም ርቀት ዕይታቸውን ከሚከልሉ አማካሪ ግለሰቦችና ዝባዝንኬ ጉዳዮች ካልተጠበቀ የማይቀርለት የመዳከም ጉዳይ ነው።

የበዛ ትኩረት ማጣት የዐቢይ መንግሥትን ከደካማው አፍ ጋር የሚያመሳስለው ሌላኛው ባሕርይ እንደሆነ ይሰማኛል። መንግሥትነት ለዕድሜ ልክ አይደለም። ትኩረት ያጣ መንግሥት በጊዜው ዘላቂ ሥራ ማከናወን አይችልም። በመሆኑም የምርጫ ጊዜ ሲደርስበት ሥራዬን አልጨረስኩም በሚል ሰበብ ሥልጣን የሙጥኝ ማለት የለመደብን አዙሪት ከሆነ ውሎ አድሯል። የዐቢይ መንግሥት በርካቶች ተስፋ እንዳደረጉበት ለዴሞክራሲያዊት አገር ግንባታ የሚበጀው ሥራ ላይ አተኩሮ ታሪክ ሰርቶ ቢያልፍ ምኞቴ ነው። ለዚህ ግን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል። በመሆኑም ሁላችንም እንደምናውቀው ፖለቲካው ችግር ውስጥ ነው፣ ምጣኔ ሀብቱም እንዲሁ፣ በርካታ ማኅበራዊ ጉዳዮችም ትልቅ ትኩረት እንደሚሹም ይታወቃል። አህጉራዊ በተለይም ክፍለ አህጉራዊ የሰላምና የደኅንነት ጉዳዮችም አሳሳቢ ናቸው። የዓለም ዐቀፋዊ ግንኙነቱ ትኩረት የሚሻ ነው። በአጠቃላይ አገሪቱ በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ተፅእኖ ውስጥ እንዳለች የሚታወቅ ነው። በመሆኑም በእንግሊዝኛው እንደሚባለው (grasp all, lose all) እንዳይሆን መንግሥት ትኩረት አጥቶ ደካማውን የወፉን አፍ መስሏል።

የዐቢይ መንግሥትና ለእኔ ባዩ አፍ
የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት “የፈጣኑና” ለእኔ ባዩ የወፍ አፍ ባሕርይ አመላካች ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ነው። በግለሰብ ደረጃ፣ እንዲሁም በፓርቲ፣ ከዚያም አልፎ በጎጥ እስኪከፈል ድረስ የመንግሥት የውስጥ ሽኩቻ የበለጠ ገኖ ወጥቷል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሥልጣን ሞኖፖሊ አስግቶናል የሚሉ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኢሕአዴግ መስራች ድርጅቶች አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ጨምሮ መኖራቸው የሚገልፁት በርካቶች ናቸው። በግለሰብ ደረጃ ሕወሓት እኛ የተወከልንበትን የአስተዳደር ክልል ጥያቄ የያዘበትና ለመመለስ የሚሠራበት መንገድ አግባብነት ስለጎደለው ከፓርቲው አባልነት ወጥተናል የሚሉ ግለሰቦችን ከከፍተኛ አመራር አካላት እያየን ይገኛል። አስቡት እነዚህ ግለሰቦች በአንድ ወቅት የኢሕአዴግ በተለይም የሕወሓት አሰራር ከምድር በታች ምሉዕ ነው ብለው ሲከራከሩ የነበሩ ጥቅመኞች እንደነበሩ የማይካድ ጉዳይ ነው። መነሳት የነበረባቸው በይቅርታ ነበር። ወደ ጉዳዬ ልመለስና የኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲዎች ለሕግ የበላይነት መዳከም በተለያየ መልኩ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውንም የሚገልጹ በርካቶች እየሆኑ መጥተዋል። ማፈናቀሉ፣ ሙሰኝነቱ ወዘተ የሚገርመው ጊዜ ሲልፍ እንሱ ቢረሱት ሌላው የሚረሳው የሚመስላቸው ደካሞች መኖራቸው ነው።

ጉዳዮችን በፍጥነት እንጂ በትኩረት የሚተነትን መጥፋቱ የዐቢይ መንግሥት ለእኔ ባዩ ወፍ ባሕርይ ሌላው መገለጫ ሆኖ ወጥቷል። ለእኔ ብቻ ባዩ ወፍ ፍጥነቱን እንጂ የሚሰራው ሥራ ሌላኛው አፍ ላይ ምን ዓይነትና መጠን ያለው ተፅዕኖ እንደሚደርስ ያሰበው አይመስልም። በመንግሥት ውስጥም ለጉዳዮች ጥልቀት ያለውና ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ ተግባራትን ማከናወን የተሳናቸው በእሳት ማጥፋት የተጠመዱ አመራሮችን እየታዘብን እንገኛለን። ነገር ግን እነዚህ አመራሮችና ጽሕፈት ቤታቸው የሚያቅዱትና የሚተገብሩት መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ሰሞኑን የተለያዩ ሕጎችን የሚከለሱባቸውና፣ የፖሊሲ አቅጣጫን የሚነድፉባቸው ተግባራት የጥራትና የትኩረት እንዲሁም አደገኛ የግንዛቤ ክፍተት እየተስተዋለባቸው ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉንም ጉዳይ ሁሉም ቦታ መከሰት በተለይ በመጀመሪያው የሥልጣን ወራት የታዘብነውና የተገነዘብነው ጉዳይ ነው። ከኤርፖርት ምረቃ እስከ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ፤ ከስቴዲየም ምረቃ እስከ ተፈናቃዮች መንደር ዐቢይ ያደረጉት እንቅስቃሴ ብዙዎች ለሳቸውም በማዘንም፣ በማብጠልጠልም የተገነዘቡት ጉዳይ ነው። በተለይ አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ወስደው ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በደርዘን ከሚያማክሯቸው ባለሙዎች ጋር መቼ ተገናኝተው የጠራ መረጃና ሐሳብ ያገኛሉ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። አንዳንዶች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአመራር መጻሕፍት ሰለባ እንደሆኑ በመጠቆም ያነበቡትን ወይም የሰሙትን (መስማት ብቻ አደገኛ እንደሆነ ልብ ይሏል!) የተለያዩ ባሕርያት በተግባር ለመተርጎም አጉል ሙከራ እያደረጉ እንደሆነም የሚዘባበቱም አልጠፉም። ያም ሆነ ይህ የዐቢይ መንግሥት የፈጣኑንና ለእኔ ብቻ ባዩን የወፍ አንገት መሰል ባሕርይ እያሳዩ እንደሆነ መስተዋሉን ብዙዎች የተስማሙበት ይመስላል።

ከላይ ካነሳነው የወፉ አንገት ባሕርይ ጋር የሚዛመደው ሌላው ተግባር ደግሞ የዐቢይ መንግሥት ምሁር መሰል አሰራር ከግርድፍ መረዳት ጋር በማጣመር የሚተገብርበት አሠራር መስተዋሉ ነው። ጉዳዮች ምሁራዊ ትንታኔ ያስፈልጋቸዋል ሲባል ፅንሰ ሐሳበዊ መረዳቶችን ከነባራዊ ዓውድ ጋር አዛምዶ መተንተን፣ አንድምታዎችን መለየትና አቅጣጫን ማመላከት ነው። የዐቢይ መንግሥት ግን ዕድሜ ከመጣው ጋር ለሚያሸረግዱ በተለይ የሕዝብ (ልብ በሉ የመንግሥት አላልኩም) ብዙኀን መገናኛዎች በየቦታው የሚደረጉትን ስብሰባዎችና ውይይትቶች በተለመደ የቸከ አዘጋገባቸው ሲያስተጋቡ እንሰማለን። እዚህ ላይ የአቅም ክፍተቱ እንዳለ ሆኖ ሙያዊ ኀላፊነታቸውን በተቻለ መጠን ለመወጣት የሚጥሩትን ባለሙያዎችና ብዙኀን መገናኛ ድርጅቶች ጥረት ከግምት ማስገባት ያሻል። ለውጡን ተከትለው አንድ ወዳጄ እንዳለው (U turn) ያደረጉትንም ከቁጥር ማስገባቴ ልብ ይባልልኝ።

የባለኹለት አፍ ወፉ መጨረሻ
የከበደ ሚካኤልን ግጥም የመጨረሻ ስንኞች እንደሚያትተው ወፉ በአንድ ፍሬው መራራና አደገኛ፥ ቢበሉት የሚገድል ዛፍ ላይ ያርፋል። ወፉ ያረፈበት ዛፍን ፍሬ ገዳይነት ያወቀው ዛፉ ላይ ካረፈ በኋላ ነበር። በመሆኑም ደካማው አፍ መልካም ፍራፍሬዎችን ከተከለከልኩ በሚል ሒሳብ ፍሬውን ለመብላት ይወስናል። “ለእኔ ባዩ” አፍ ቢመክረውና ቢለምነው እምቢኝ ብሎ ያንን መራራና ገዳይ ፍሬ በልቶ ወፉ ከነኹለት አፉ መሞቱን ግጥሙ በሚያምር ፍሰት ይደመድማል። የግጥሙ ዘመን ተሸጋሪነት እንደለ ሆኖ አሁን ላለንበት ጥልፍልፍ ችግር የሚለገሰው ምክር እጅግ ውድ መሆኑን ሳስብ ገርመኛል። የዐቢይስ መንግሥት ይህንን የመንግሥታቸውን ባለኹለት አፍ ባሕርይ ተረድተው ከችግር ቀድመው መፍትሔ ይፈልጉለት ይሆን? ይህ ምኞቴም ጸሎቴም ነው። ምክንያቱም አገሪቱ ሌላ ዙር መጠላለፍ በተለይ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከተከሰተ ችግሩን መላሽ እንዳያጣ ያሳስበኛልና ነው።

ጌታቸው መላኩ የሚዲያና ተግባቦት አማካሪ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው getachewmelaku@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here