ማቱክ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ነው

0
511

የመካከለኛው ምሥራቅ “ስታር ባክስ” በመባል የሚሞካሸው የቡና አምራች እና አቅራቢማቱክ ኩባንያ በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ በመጪው ሰኔ ወር ላይ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የቡና ዘርፉን ለመቀላቀል እንዳሰበ ታወቀ።

በተለያዩ አገራት በቡና ንግድ ዘርፍ የተሠማራው ማቱክ ኩባንያ ቀጣይ ዕቅዱን ወደ ኢትዮጵያ በማድረግ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ዕሴት ጨምሮ እና አቀነባብሮ ወደ ውጭ በመላክ ሥራ ላይ እንደሚሠማራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መኮንን ኃይሉ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በውጭ ንግድ ዘርፍ ብዙም መግፋት ያልቻለችው የሚገኙትን ምርቶች በቀጥታ ምንም ዕሴት ሳይጨመርባቸው ስለምትልክ ነው ይላሉ። አያይዘውም “አሁን መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ የተሰናዳው ኩባንያ አቀነባብሮ እና ዕሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ስለሚልክ ከቡና የሚገኘውን ገቢ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል” ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል።

ዋና መነሻውን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረገውና በመካከለኛው ምሥራቅ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ማቱክ ኩባንያ በመካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ደግሞ በባሕረ ሰላጤው አገራት በርካታ ሱቆች እንዳሉት ይታወቃል። የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሚቀጥለው ወር በሚያደርጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ ያላትን የቡና ምርት እምቅ አቅም ከመገምገምም በተጨማሪ በቡና ዘርፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጨምረው እንደገለጹት፥ ማቱክ ኩባንያ የኢትዮጵያን ቡና ወደ ዓለም ዐቀፍ ገበያ ከማቅረብም ባሻገር በኩባንያው አማካኝነት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚገባው የኢትዮጵያ የቡና መጠን ጭማሪ ያሳያል ተበሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቡና ማምረት ላይ የተሠማሩት የቡና ገበሬዎችም ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሚፈጠርም ታውቋል።

ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ በቡና ንግድ ላይ ተሠማርቶ የሚገኘው ማቱክ በእነዚህ ዓመታት ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን የቡና ዓይነቶችን ከመላው ዓለም በመምረጥ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በዓለም ዐቀፍ ደረጃሲያቀርብ መቆየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በዝርዝሩም ውስጥ የኢትዮጵያ የቡና ጥራትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ ዕሴቶችን በመጨመር ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ ምሥራቃዊ የአውሮፓ ክፍለ አገራት ለመላክ ማሰቡ ተሰምቷል።

የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳሚራ ማቱክ በመጪው ሰኔ ወር ላይ ስለሚያደርጉት የኢትዮጵያ ጉዟቸው ሲናገሩ፥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በኢንቨስትመንት ዘርፍ ሥምምነት ላይ እንደሚደርሱና ይህም ከኢትዮጵያ ባለፈ ለምሥራቅ አፍሪካ የተቀነባበረ ቡናን ለዓለም ዐቀፍ ገበያ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here