ሕገ ወጦች የክልሉን የማዕድን ዘረፍ አደጋ ላይ ጥለውታል

0
1149
  • ከ10 ሺሕ በላይ ማዕድን አውጭዎች በ 7 ዓመት ውስጥ 16 ሚሊዮን 944 ሺሕ ዶላር ብቻ አስገኝተዋል

በአማራ ብሔራዊ ክልል 10 ሺሕ 299 የባሕላዊ ማዕድን እና 81 የከበሩ ማዕድናት አውጪ ፍቃድ ያላቸው ማኅበራት ቢኖሩም በሕገ ወጥ ማዕድን አውጪዎች ሰርጎ ገብነት ዘርፉ እጅግ መዳከሙን የክልሉ የመንግሥት የማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ገለፀ፡፡ ሕጋዊዎቹ አምራቾች በተለያዩ ማዕድናት ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው ቢገኙም በደከሙበት ልክ ጥቅም ያለማኘት፤ አምራቾች በቀላሉ ሊገበያዩባቸው የሚችሉ የገበያ ማዕከላት በአቅራቢያው አለመኖራቸውንና መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት ለችግሮቹ መንስኤ ናቸው ተብሏል፡፡

በክልሉ በዓለም የጌጣጌጥ ገበያ ሠንጠረዥ ተፈላጊነቱ እያደገ በመጣው የኦፓል ማዕድን አምራች አካባቢዎች ባለፉት ሰባት ዓመታት ለዓለም ገበያ ከቀረበው የኦፓል ምርት ከ17 ሚሊዮን አሜሪካን ዶላር በታች አሰገኝተዋል፡፡

ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለጌጣጌጥ፣ ለግንባታ፣ አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ የተለያዩ ማዕድናት በክልሉ ይገኛሉ፡፡ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎች ሊያገለግሉ የሚችሉ እንደ አሸዋ፣ ኖራ ሴራሚክ ፣ የድንጋይ ከሰል እና ነዳጅ የኀይል አማራጮችም እንዳሉ ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ከላከው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የወርቅ ማዕድን በ13 ወረዳዎች፣ ኦፓል በ16 ወረዳዎች መኖራቸውን በጥናት መረጋገጡን ከአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይታየው ተስፋሁን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ኦፓል በአብዛኛው በአራት የክልሉ ዞኖች የሚገኝ ሲሆን በተለይም በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ ከፍተኛ ክምችት ይገኛል፡፡ በወረዳው 27 ቀበሌዎች ማዕድኑ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ ነገር ግን የኦፓል ክምችቱ የወረዳውን ነዋሪዎችም ይሁን ለአገሪቱ የውጭ ንግድ እያስገኘ ያለው ጥቅም ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡

በኦፓል ማዕድን ብቻ ከተሠማሩ የአማራ ክልል ማኅበራት እና ግለሰቦች ባለፉት 7 ዓመታት ወደ ውጭ አገር ከተላከ ምርት የተገኘው ጠቅላላ ገቢም 16 ሚሊዮን 944 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ክልሉ ምንም እንኳን እምቅ የማዕድን ሀብት ቢኖረውም የሚፈለገውን ያክል ጥቅም እያኘ እንዳልሆነ ማሳያ ነው ይላል ኤጀንሲው፡፡ ልክ እንደ ኦፓል ሁሉ በሌሎች የክልሉ የማዕድን ሀብቶች ላይ የተሰማሩ ማዕድን አውጭዎችም ከዘርፉ የሚያገኙትና የሚያስገኙት አገራዊ ጠቀሜታ አጠያያቂ ነው፡፡

ይታየው እንዳሉት ከእነዚህ በአነስተኛ እና በከፍተኛ ማዕድን ማምረት ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች እስከ ሕዳር 15/2011 በነበረው ጊዜ ውስጥ 3 ሚሊዮን 409 ሺሕ 434 ብር ብቻ ነው ገቢ የተገኘው፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here