በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የትጥቅ ትግላቸውን ለማቆም በመሥማማት ከኤርትራ የተመለሱ የኦነግና የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሠራዊት አባላት በካምፕ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ወደ ተለያዩ የግል ሥራዎች ሊገቡ መሆኑ ታወቀ። የኦነግ ሠራዊት ከነበሩት አባላት ውስጥ የተወሰኑት የኦሮሚያ ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው የገቡ ሲሆን፥ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሠራዊት ግን ሙሉ ለሙሉ በመንግሥት መዋቅር የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ለማወቅ ተችሏል።
የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ቶሌራ አዳባ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሳተፍ ያልፈለጉ አባላት በግብርና ሥራ እንዲሁም በሌሎች የሥራ ዘርፎች ተሠማርተው ለመሥራት የመቋቋሚያ ገንዘቡ እስኪሰጣቸው እየጠበቁ መሆኑን አስታውቀዋል። የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ የነበሩት ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው፣ የቀድሞ አባሎቻቸው ሥራ ፈጥረውና ራሳቸውን አደራጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው ልዑካን ቡድን በጥቅምት ወር፣ 2011 በጀርመን እና ፈረንሳይ ቆይታ ባደረገበት ወቅት ነበር የጀርመን መንግሥት 35 ሺሕ የሚሆኑ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወስነው ወደ አገር ቤት የተመለሱ ታጣቂዎችን ለማቋቋም ድጋፍ ለመድረግ ቃል የገባው።
የጀርመን መንግሥትም የልማትና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ቃል በተባው መሠረት ታጣቂዎቹን መልሶ ለማቋቋም ገንዘብ መልቀቁን ለማወቅ ተችሏል።
ከኤርትራ ተመልሰው ወደ ካምፕ የገቡት የአርበኞች ግንቦት ሰባት የቀድሞ ሠራዊት አባላት 300 ገደማ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ከመቶ በላይ የሠራዊቱ አባላት በሥልጠና ላይ ይገኛሉ። ሥልጠናቸውን በማጠናቀቅ ወደ የቤታቸው የተመለሱት የፌደራል መንግሥቱ ዘጠኝ ሺሕ ብር እየሰጠ መልሶ ማቋቋም መርሐ ግብሩ ሲጀመር በያሉበት ሆነው የሚሳተፉበት አማራጭ ይሰጣቸዋል።
አርበኞች ግንቦት ሰባት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ በትግል ወቅት ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑት ለትምህርት እና ሌሎች መርጃ መሣሪያዎች የሚውል ገንዘብ በመስጠት ለመደገፍ መወሰኑንና፣ ቀሪውን ደግሞ ለሠራዊቱ የልብስና መሰል ግዢዎች የሚሆን ገንዘብ እንደሚለግስላቸው አዲስ ማለዳ ከቀድሞ አመራሮቹ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። የአርበኞች ግንቦት 7 ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከመመሥረቱ በፊት ሲከስም፥ የቀድሞ የሠራዊት አባላቱን የማቋቋም ሥራ እንዲሠራ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑ ይታወሳል።
የንቅናቄውን የቀድሞ ሠራዊት አባላት መልሶ የማቋቋም ሥራው ከሚገባው በላይ በመዘግየቱ ምሬቱን ገልጾ የነበረው የቀድሞው የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሥራ አስፈፃሚ፥ መልሶ የማቋቋሙን ሒደት ላይ መንግሥት የሰጠውን አነስተኛ ትኩረት ለተመሳሳይ ድርጅቶች ሠራዊት ከተሰጠው ትኩረት ጋር በማነፃፀር በካምፕ ውስጥ ባሉት የሠራዊቱ አባላት መሐል የሚታየው ምሬትና መከፋት ተገቢ መሆኑን ተናግሮም ነበር። ይህንንም ጉዳይ አመራሩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር በፍጥነት መፍትሔ እንዲገኝለት ጥረት እንዲያደርግ አበክሮ አሳስቦም ነበር።
በመጨረሻም የቀድሞው የአርበኞች ግንቦት 7 ምክትል ሊቀ-መንበር አንዳርጋቸው ጽጌ ይህንን ኃላፊነት ወስደው ምልስ ታጋዮችን የማቋቋሙን ሥራ እንዲሠሩ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011