የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ቁጥር ከሚጠበቀው በታች ነው

0
751
  • ፀጥታ እና ደኅንነት ለማስከበር 2 ሺሕ ተጨማሪ አባላት ያስፈልጋሉ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአባላቱ ብዛት በቁጥር መሆን ካለበት ደረጃ በታች መሆኑን አስታወቀ። የፖሊስ ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉት የፖሊስ አባላት 19 ሺሕ እንደሆኑ አስታውቀው፤ ከከተማዋ ነዋሪ ቁጥር አንጻር የማይመጣጠን ነው ብለዋል። አያይዘውም አሁን ያለው ቁጥር የተቀመጠለትን ደረጃ ለመያዝ ወደ 21 ሺሕ ከፍ ማለት እንደሚኖርበት ጠቁመዋል።

የፖሊስ አባላት ቁጥር ዝቅ ያለበት ምክንያት ምን እንደሆነና ለምን ደረጃውን ማሟላት እንዳልተቻለም ኮሚሽነሩ ሲገልፁ፥ በዋናነት በጥራት ላይ ትኩረት ስለተሰጠ በገፍ ለማስመረቅ ባለመቻላችን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በቅርቡም የአባላትን ቁጥር ከፍ ለማድረግ 1 ሺሕ ሦስት መቶ አባላት ተመልምለው ሥልጠና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ያስታወቁ ሲሆን ከሰኔ 1/2011 ጀምሮ ሥልጠና እንደሚጀምሩም ከኮሚሽነሩ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከወንጀሎች ውስብስበነትና ብዛት አንጻር የሰው ኀይል እጥረት ማጋጠሙን ተከትሎ በዋናነት የማኅበረሰብ ዐቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ጠቁሟል። በዚህም ረገድ አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት 57 ፖሊስ ጣቢያዎች ለ121 ወረዳዎች በቂ ባለመሆናቸው 46 የማኅበረሰብ ዐቀፍ የፖሊስ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተገንብተው መጠናቀቃቸው እና ተጨማሪ 68 የሚሆኑት ደግሞ በጅምር ላይ እንደሆኑ ታውቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኮሚሽኑ የፖሊስን ኑሮና ሕይወት ለመቀየርም እንደሚሠራ ጌቱ አርጋው ገልጸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ፥ አባላት ቤት ባለቤት እንዲሆኑ እንደሚሠራ እና ቀለብ ማሻሻያም እንዳደረገ ታውቋል። የቤት ግንባታውን በሚመለከት በሚቀጥለው በጀት ዓመት በሰባት ግንባታ ቦታዎች ባለዐሥር እና ባለዐሥራ አምስት ፎቅ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሚገነባ ሲሆን፥ አሁን ላይ የዲዛይን ሥራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋክልቲ ተሰርቶ ተጠናቋል።
የግንባታ ወጪውንም መስተዳደሩ 4 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተጠቁሞ በሚመጡት ሦስት ዓመታትም ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ጊዜ ተይዞለታል። የአባላትን ኑሮ ለመቀየር በሚል ሌላው ነጥብ ደግሞ ቀለብ ማሻሻያው ቀድሞ ከነበረው 450 ብር ወደ 850 ብር ከፍ እንዲል መደረጉን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለአባላቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅን ለመገንባትም ዕቅድ እንደተያዘለት ተነግሯል። ይህም ከዚህ ቀደም ኮልፌ የፖሊስ አካዳሚ ብቻ የነበረው አዲስ አበባ ፖሊስ በቀጣይ ኮሌጅም እንደሚኖረው ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታዩትን ብዙ ወንጀሎች በሚመለከት ኮሚሽነሩ ሲገልፁ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 12 ሺሕ 326 ወንጀሎች መመዝገባቸውን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ በኹለተኛው ሩብ ዓመት ከተመዘገበው 4 ሺሕ 317 ወንጀሎች በሦስተኛው ሩብ ዓመት በ825 ቀንሶ 3 ሺሕ 492 መድረሱን አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here