ቤንች ማጂ ዞን መፍረስ በክልሉ አመራሮች ተቃውሞ ገጠመው

0
608

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የቤንች ማጂ የዞን መስተዳድር በሚያዝያ/2011 በይፋ መፍረሱን የዞኑ ምክር ቤት ማስታወቁን ተከትሎ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተቃውሞ እየገጠመው መሆኑ ታወቀ። ዞኑ ለኹለት የተከፈለው በግለሰቦች ይሁንታ ሳይሆን በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ነው ሲል የክልሉ ምክር ቤት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ዞኑ የምዕራብ ኦሞ እና የቤንች ሸኮ በሚሉ ኹለት ዞኖች በመከፈል እየተገባደደ ካለው ሳምንት መግቢያ አንስቶ በየፊናቸው ሥራቸውን መጀመራቸውም ታውቋል።

የዞኑ ምክር ቤት አንዳንድ አባላቶች የአስተዳድር መዋቅር ጥያቄዎቹ ከመንግሥት የሚቀርቡ የማኅበራዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት ያስችላል ሲሉ፣ ከፊሎቹ ደግሞ አስተዳደራዊ ወጪዎችን በማናር የልማት በጀቶችን ከመሻማት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም ሲሉ ይሞግታሉ።

ነባሩ ዞን የፈረሰው በክልሉ መንግሥት የተካሔደው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት ለዞኑ ምክር ቤት ጉባኤ ቀርቦ ውሳኔ በማግኙቱ መሆኑን የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ሰይፈ ዓለሙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት እና ከጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር የሚጎራበተው የቤንች ማጂ ዞን በደቡብ ክልል ነባር ከሚባሉት የዞን መዋቅሮች አንዱ ነበር።

ዞኑ በይፋ መፍረሱን በተመለከተ የነባሩ ቤንች ማጂ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወርቅነሽ ባዴት “የክልሉ ምክር ቤት ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት በሰጠው ውክልና መሰረት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ጥናት አጥንቶ ባገኘው የጥናት ውጤት መሰረት የቀድሞ ቤንች ማጂ ዞን አስቸኳይ ጉባኤ ተደርጎ በዚያ ጉባኤ ዞኑ ለኹለት መከፈሉን ምክር ቤቱ ይፋ አድርጓል” ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ መንግሥት ተዘጋጅቷል የተባለው የመዋቅር ማሻሻያ የዞኑ ምክር ቤት ውሳኔ ከመቅረቡ በፊት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉን እና የሕዝቡ ፍላጎት ለውሳኔው መነሻ መሆኑን ወርቅነሽ ጠቁመዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ክልል በዓይነትም በመጠንም እየጨመሩ የሚገኙት የአስተዳድር መዋቅር ጥያቄዎች ላይ አዎንታዊም አሉታዊም አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።

በደቡብ ክልል መስተዳድር ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ደያሞ ዳሌ በመዋቅር ጥያቄዎች ዙሪያ ጥቂቶች መሰረታዊ የሚባሉ አሳማኝ ምክንያቶች ቢኖራቸውም አብዛኞቹ ግን የመንግሥት መዋቅሮችን በማስፋት የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ካላችው ፍላጎት የሚመነጩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የሕዝቡን ፖለቲካዊና ንቃት እና ማኅበራዊ ፍላጎቶችን ተከትለው ለሚነሱ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የጠቆሙት ደያሞ አፈፃጸሙ በጥናት፣ በፖሊሲና በአዋጅ ሊደገፍ ይገባል ብለዋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ አካሒዶት በነበረው መደበኛ ጉባኤ ሦስት ዞኖች እና አርባ አራት ወረዳዎችን በአዲስ መልክ ለማዋቅር የሚያስችለውን ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here