ሶደሬ ሪዞርት ሆቴል ወደ ሰንሰለት ሆቴሎች ገበያ ሊገባ ነው

0
1327

ከተመሰረተ 70 ዓመታትን ያሰቆጠረው ሶደሬ ሪዞርት ሆቴል ወደ ዓለም ዐቀፍ የሆቴል ሰንሰለቶች ሥራ ለመግባት ዝግጅቶች መጀመሩን እና በአዲስ አባባ እና በሰሜን አሜሪካን አገር አዳዲስ ሆቴሎችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታወቀ። በ2009 ሙሉ ለሙሉ ከመንግሥት ይዞታ ወደ ግል የታለፈው ይህ ሪዞረት ሆቴል በቢሾፍቱ ባቦጋየ ሐይቅ ዳር የሪዞርት ግንባታ የጀመረ ሲሆን በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት ፊት ለፊት በ250 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል ግንባታም 95 በመቶ መድረሱም ተገለጿል።

አዲሱ ገበያ እና ቦሌ አትላስ አካባቢ እየተገነቡ ያሉት ሆቴሎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆኑ የሪዞርቱ ዋና ሥራ አስከያጅ አብዮት ተመስገን ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል። ጨምረውም ቢሾፍቱ ከተማ ባቦጋያ ሐይቅ ላይ የሚገነባው ሆቴል ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ታስቦ እየተገነባ እንደሆነ ተናግረዋል። በተለይም የቤተሰብ መዝናኛዎች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

በ427 ሄክታር መሬት ላይ ከአዳማ ከተማ 27 ኪሎ ሜትር ላይ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ 124 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሶደሬ ከተማ ላይ የተገነባው የመጀመሪያው ሶደሬ ሪዞርት ሆቴል በ2009 ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታ የተላለፈ ሲሆን የሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት ዲንቁ ደያስ ከመንግሥት ድርሻውን ጠቅልለው ገዝተዋለ።

በአጠቃላይ ሪዞርቱ ይዞት ከሚገኘው ቦታ ላይ 127 ሄክታሩን ያለማው ሲሆን በ600 ሚሊዮን ብር በተደረገ ማስፋፊያ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ከሚሰጡት 371 መኝታ ክፍሎች በተጨማሪ፤ አዳዲስ አንድ መቶ ክፍሎችን ለመኖሪያነት እየገነባ እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here