ኢዜማ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን ሠየመ

0
289

ሐሙስ፣ ግንቦት 15/2011 በግዮን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) 21 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ሠይሟል። የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የፓርቲውን መሪ፣ ምክትል መሪ፣ ሊቀ መንበር፣ እና ምክትል ሊቀመንበር ጨምሮ 21 አባላት ያሉት የሰባት ዘርፎች መሪዎችን ይዟል።

ኢዜማ ሁለት መዋቅር ያለው ሲሆን፥ በፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና በፓርቲው ሊቀ መንበር የሺዋስ አሠፋ እንደሚመሩ ግንቦት 2 በተካሔደው የመሥራች ጠቅላላ ጉባዔው ተገልጾ ነበር። በፓርቲው መሪ ሥር ያለው መዋቅር ከመንግሥት ትይዩ ካቢኔ የመሠረተ ሲሆን፥ እያንዳንዱን የመንግሥት ሚኒስቴር የሚተካ የፓርቲ ዕጩ አባል የሚኖርበት መዋቅር ነው ተብሏል። በሌላ በኩል በፓርቲው ሊቀመንበር የሚመራው መዋቅር ለምርጫ የማይወዳደር ነገር ግን የፓርቲውን ሥራዎች የሚያከናውን መዋቅር መሆኑ ተገልጿል።

በሐሙሱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሹመት ከመሪው መዋቅር ውስጥ 7 አባላት የተሠየሙ ሲሆን፥ ከትይዩ ካቢኔው ሦስት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እጩ ተወካይ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወካዮች እንዲሁም ከመሪው ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና ምክትል መሪው አንዱዓለም አራጌ ጋር መካተታቸውን በዕለቱ የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በምርጫ ወረዳዎች ውስጥ የተለያዩ ኀላፊነት የነበራቸው እና ለሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ አባልነት የተመረጡት አባላት፥ ድርብ ኀላፊነትን እንደማይወስዱ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው፣ በምርጫ ወረዳዎች ውስጥ ያላቸውን ኀላፊነት እንደሚለቁ ገልጸዋል።

በዚህ መሠረት ዋሲሁን ተስፋዬ የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ኀላፊ፣ አምሃ ዳኘው የጥናትና ምርምር ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ ፅዮን እንግዳ እና ቴዎድሮስ አሰፋ የወጣቶች ጉዳይ ተጠሪዎች፣ እሌኒ በጋሻው እና ሒሩት ክፍሌ የሙያ ማኅበራት ተጠሪ፣ ካውሰር እድሪስ እና ናንሲ ውድነህ የሴቶች ጉዳይ ተጠሪ፣ ግርማ ሰይፉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዕጩ ተወካይ እንዲሁም ዳንኤል ሺበሺ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕጩ ተወካይ ሆነው ተሠይመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here