‘ሲትኮም’ ከማሳቅ ባሻገር

0
760

አጭርና ራሰ በራ የሆነው ቶኪቻው ከጭቃ በተሠራች ደሳሳ ጎጆ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሏል። ጠላ እየጠጣ የሚገኘው ቶኪቻው ክፍለ ሀገር አብሯቸው የሔደው ጓደኞቹ ሲመለሱ ጥለውት ስለመጡ ይቅርታ ቢጠይቁትም, ይቅርታ ሊያደርግላቸው አልፈለገም። ጓደኞቹም ተስፋ ባለመቁረጥ የይቅርታ ጥያቄያቸውን ደጋግመው በማቅረባቸው የተናደደው ቶኪቻው, የለበሰው ቲሸርት በንዴት እላዩ ላይ እንዳለ መቀዳደድ ጀመረ።

ቶኪቻው በድኅነት ውስጥ የሚኖር የዐሥራ አንድ ልጆች አባት ሲሆን ከየቤቱ ቆሻሻ በመሰብሰብ በሚያገኛት ገቢ ነው ኑሮውን የሚመራው። ጠላ ጠምቆ በመሸጥ የሚተዳደሩት እማማ ደንበኛ የሆኑት ጓደኞቹም ይህንን ስለሚያውቁ ለምን የራሱ ንብረት የሆነውን ቲሸርቱን እንደሚቀድ በመገረም ይጠይቁታል። ይህ ትዕይንት የአገራችንን ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊውን እንከኖች ከሚተቹት ተከታታይ ‘ሲትኮም’ የቴሌቪዥን ድራማዎች አንዱ ከሆነው ‘የእማማ ቤት’ ኻያ ስምንተኛው ክፍል ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው።

‘ሲቺዌሽናል ኮሜዲ’ ወይንም ሲትኮም በመባል የሚታወቀው የኮሜዲ ዓይነት ዋነኛው ዓላማው በተመልካቾች ዘንድ ሳቅን ማጫር ሲሆን መቼቱ የተወሰነ ቦታ ላይ ማለትም ልክ እንደ ‘እማማ ቤት’ በጠላ መሸጫ ቤት፣ በመኖሪያ ቤት ውስጥ፣ በኢንተርኔት ካፌ ወይንም በእንግዳ ማረፊያ ቤት ውስጥ ያተኮረ ነው። አብዛኛውን ጊዜም ታሪኩ ከዕለት ተዕለት ሕይወት ተነስቶ ልክ የሚመስል የኑሮ ዘዬ በገጸ ባሕሪው ሞኝ፣ ቂላቂል የሚመስሉ ድርጊቶች፣ ምጸቶችና መሰል ድርጊቶች በመተቸት ወይንም አፈንጋጭ ባሕሪይ በማሳየት ይቀጥላል። ይህም ገጸ ባሕሪው ከወዳጅ ዘመዶቹ፣ ከጓደኞቹ እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲጋጭ ያደርገዋል። በመጨረሻ ግን የተፈጠሩት ችግሮች መፍትሔ አግኝተው ትዕይንቱ ያበቃል።

‘የእማማ ቤት’ አዘጋጅና ዳይሬክተር የሆነው ሱራፌል ዳንኤል የእማማ ቤት ኻያ ስምንተኛው ክፍል ከመተላለፉ በፊት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖሩ ወጣቶች በሥልጣን ላይ የነበረውን መንግሥት በመቃወም መኪኖችንና አውቶብሶችን በድንጋይ የሚሰብሩበት እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶችን በእሳት የሚያጋዩበት ወቅት ነበር። በመሆኑም ይህ ክፍል ድርጊቱን በሳቅና በጨዋታ እያዋዛ ለመተቸት የተሞከረበት ነው። በፖለቲካ ባሕላችን ላይ የሚታዩ ሕጸጾችን ከመተቸት በተጨማሪም ‘የእማማ ቤት’ ማኅበራዊ ችግሮቻችንንም ነቅሶ በማውጣት ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ ይቅርታና የውይይት አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ያደረጉ አጀንዳዎችንም ያነሳል።

እኔ ባደኩበት አካባቢ ለመሸጥ ባይሆንም እንደእማማ ጠላ የሚጠምቁ እናት ነበሩ የሚለው ሱራፌል, ችግር ሲፈጠር የአካባቢው ነዋሪ መፍትሔ ፍለጋ እርሳቸው ጋር ሔዶ እንደሚወያይ ያስታውሳል። “አንድ ሰው የሆነ ሥራ ለመሥራት ሲያስብ ከሚያውቀው ነገር ቢጀምር ጠቃሚ ነው፤ ይህንን ሥራ ለመሥራት ያሰብኩት ከዚህ ልምድ ተነስቼ ነው።”

በጠላ መጠጫ ቤት በራፍ ላይ መቼቱን ያደረገው ‘የእማማ ቤት’ ከአንዷ መሪ ገጸ ባሕሪይ ውጪ ቀሪዎቹ አምስት ተዋንያን በድኅነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። “በኢትዮጵያ የሚሠሩት ፊልሞች ላይ በአብዛኛው የሚታዩት የተደላደለ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎችን ናቸው። ነባራዊው እውነት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በድኅነት የሚኖረው ሕዝብ ሀብታም ከሆነው በእጅጉ ይልቃል። ጠላ ቤትን መቼት ያደረግነው ይህንን ለማሳየት ነው” ትላለች የድራማው አዘጋጅ የሆነችው ናኦሚ መሐመድ።

በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሁን በመታየት ላይ ከሚገኙት ሲትኮሞች መካከል ‘ትንሽዋ ፓርላማ’ እና ‘ዓለሜ’ ይገኙበታል። የ‘ትንሽዋ ፓርላማ’ አብዛኞቹ ትዕይንቶች የሚታዩት በኢንተርኔት ካፌ ውስጥ ሲሆን ዋና ዓላማውም ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚታዩ እጸጾችን ነቅሶ በማውጣትና በመተቸት ኅብረተሰቡን ማስተማር ነው። አዘጋጁ ጥላሁን ሺነበርክ “የኛ ዋና ትኩረት የማኅበራዊ ሚዲያ ትችት ሲሆን ተጠቃሚው የተጻፈን ሁሉ እንዳያምን፣ እውነትን ከውሸት እንዲለይና የሚያገኛቸውን መረጃዎች እንዲያረጋግጥ የምንመክርበት መንገድ ነው” ይላል።

‘ዓለሜ’ ደግሞ ሰባቱን ዋና ገጸ ባሕሪያቱን በመጠቀም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንከኖችን እየተቸ፣ በገጸ ባሕሪያቱ በኩል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በትዕይንቱ መጨረሻ ላይ በመፍታት ይቋጫል።

እየተሠሩ ያሉት ሲትኮሞች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢመስልም ሒደቱ ግን ከተግዳሮት የጸዳ አይደለም። ሱራፌል “እኛ ‘የእማማ ቤት’ን ለመሥራት ስንነሳ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ነበረች” በማለት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል። ምንም እንኳን ሲትኮም በምጸት፣ በጨዋታና በሳቅ አጅቦ መልዕክቶችን አለዝቦ የማስተላለፍ አቅም ቢኖረውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆን በራሱ ነጻነትን የመገደብ አቅም ስለነበረው ፖለቲካውን በመተቸት ፈንታ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ለመሥራት ተገድደው ነበር።

የተለያዩ ሚዲያዎችንና ሰዎችን አሳምኖ ሥራን ወደ ሚዲያ ማውጣትም ሌላው ፈተና ነው። “አንዳንዴ “ምን ተሠራ?” ሳይሆን “ማን ሠራው?” የሚለው ላይ ትኩረት የሚሰጡ ሰዎች አሉ። እናም ጥሩ ሥራ እንደሠራን መጀመሪያ በብዙ ትግል ማሳየት ነበረብን” በማለት ናኦሚ የገጠማቸውን ፈተና ትገልጻለች።

ጥላሁንም በበኩሉ የሚዲያ ባለቤቶች አዘጋጆችን ማስታወቂያ ፈልጋችሁ አምጡ እንደሚሉና ሥራቸውን ለአየር ካበቁ በኋላ ሚዲያው ራሱ ገበያ መፈለግ ሲገባው አዘጋጁ ማስታወቂያ ፈልግ መባሉ ሌላው ፈተና እንደሆነ ያስረዳል። “በተጨማሪም ማስታወቂያ የሚያሠሩ ድርጅቶች የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያመጣ በመረዳት ፈንታ, እየረዱን እንዳሉ ስለሚሰማቸው አንዳንዴ ማስታወቂያ ልሥራላቸው ብሎ መጠየቅ እንደልመና ይቆጠራል” ይላል።

አዘጋጆች ገቢ ከሚያገኙበት መንገድ መካከል አንዱ በተመልካች ቁጥር ከዩቲዩብ የሚያገኙት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከቴሌቪዥን ባሌቤቶች ጋር በገቡት ውል መሰረት ከማስታወቂያ የሚያገኙት ነው። ሱራፌል ለአንድ ክፍል እስከ 20 ሺሕ ብር ከማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚገኝ ይናገራል። ይሁንና ሥራውን ለመሥራት ከሚወጣው ወጪ አንጻር ሲታይ ክፍያው አጥጋቢ እንዳልሆነ ናኦሚ ትገልጻለች። አዘጋጆች ከሚያገኙት ገቢ ላይ አብዛኛው ለተዋናዮች የሚከፈል ሲሆን የእማማ ቤት ተዋናዮች ከ700 እስከ 1000 ብር ይከፈላቸዋል። ነገር ግን ሱራፌል ተዋናዮቹ ለገንዘብ ብለው ሳይሆን ለሞያው ፍቅርና ያለንን በጀት ከግምት አስገብተው ስለሚሠሩ እንጂ ከዚህም በላይ ይገባቸዋል ባይ ነው። የብዙ ዓመታት ልምድ ያላቸው በዓለሜ ላይ የሚሠሩት ተዋናዮች ደግሞ እስከ 10 ሺሕ ብር ድረስ ይከፈላቸዋል።

ሌላው ወጪ ፊልሙን ለመቅረጽ ከሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ጋር የሚያያዝ ሲሆን 5 Dmax 3 ካሜራ እስከ 90 ሺሕ ብር የሚሸጥ ሲሆን በኪራይ ደግሞ በቀን ከ800 እስከ 1 ሺሕ ይገኛል። ሌላው ደግሞ በአማካኝ ለመብራት 800 ብር፣ ለፊልም ስኮሪንግ 18,000 ብር፣ ለአኒሜሽን 15,000 ብር እና ለድምጽ ቀረጻ ከ28,000 እስከ 30,000 ብር ወጪ ሊኖር ይችላል። ይህንንና ሌሎች ወጪዎችን ከግምት በማስገባት የዓለሜ ዳይሬክተር የሆነው ብንኤል ተሾመ አንድ ክፍል ሲትኮም ለመሥራት እስከ 100 ሺሕ ብር ወጪ ሊጠይቅ ይችላል ያለ ሲሆን ሱራፌል በበኩሉ መሰረታዊ ነገሮች አንዴ ከተሟሉ እስከ 15 ሺሕ ብር ድረስ በሚገመት ወጪ መሥራት ይቻላል ባይ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here