ሰሞነኛው የኀይል ፈረቃ ከድጡ ወደ ማጡ

0
719

ባለትዳርና የቤተሰብ አስተዳዳሪ ለሆነችው ለፍቅር ያረጋል የሰሞኑ የመብራት መቆራረጥ የእሷና እና የቤተሰቧን ኅልውና እየተፈታተነ እንደሚገኝ ትናገራለች። ከዚህ ቀደም በቀን እስከ 50 ኪሎ ዳቦ እና ኬክ አዘጋጅታ ትሸጥ የነበረ ሲሆን ላለፉት ሦስት ሳምንታት የገበያው ፍላጎት ቢጨምርም ፍቅር ማቅረብ የቻለችው ግን ግማሹን ብቻ ነው።

በተለምዶ ሾላ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት ለወትሮው ዳቦ ቤቶች ገበያቸው በሚደራበት በማለዳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በራቸው ዝግ ነበር። ፍቅር እንደምትለው ከሆነ በአካባቢው በብዛት ያሉት ዳቦ ቤቶች የራሳቸው የንግድ ቦታ ካለመሆኑ አንጻር ይህን ሁኔታ ተቋቁመው መሥራት አይችሉም።

“እኔ ዛሬ እዚህ የተገኘሁት ቤት ኪራይ ስለሌለብኝ, ይህን ችግር ተቋቁሜ ማለፍ እችላለው በሚል እምነት ነው። ነገር ግን ዳቦ ቤቱ ክፍት ሆኖ በትንሹም ቢሆን አገልግሎት ይስጥ እንጂ ኪሳራው እጅጉን የከፋ ነው” ትላለች።
ዳቦ ጋግሮ በማከፋፈል ንግድ ላይ የተሰማራው አሕመድ ቡሼራ በኀይል አቅርቦቱ ምክንያት ሠራተኞቹን እስከመቀነስ እንደደረሰ ይናገራል። አሕመድ እንደሚለው ከዚህ ቀደም ከስንዴ ዱቄት እጥረት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ እንግልት እንደደረሰበት እና ይህን ሁኔታ በማስተካከል ደንበኞቹን ሳይመልስ በድጋሜ ይሔ መፈጠሩ የማይወጣው ችግር ውስጥ እንደከተተው ይናገራል።

“ሠራተኞቼን ቀነስኩ፤ ነገር ግን የቤት ኪራይን መቀነስ አልችልም። ይህ ማለት ችግሩ በመጠኑም ቢሆን ካልቀነሰ ሥራዬን ማቆሜ አይቀርም” ሲል በከፍተኛ ትካዜ ውስጥ ሆኖ ይናገራል።

በባለፉት ሳምንታት እየተካሔደ ባለው የኤሌክትሪክ አቅቦት መቀነስ ምክንያት ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ መጉላላት እየደረሰበት እንደሆነ በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች ሲገልፅ ሰንብቷል። የተለያዩ ዳቦ ቤቶች አገልግሎት ያለመስጠት፣ የእንጀራ ዋጋ መጨመር እንዲሁም የተለያዩ ሥራዎች መስተጓጎል ኅብረተሰቡን ላልታሰበ የኑሮ ጫና እየዳረገው እንደሆነ አዲስ ማለዳ የታዘበች ሲሆን የማኅበራዊ ሚዲያውም በጉዳዩ ላይ በስፋት ሲነጋገርበት ሰንብቷል።

ባለፈው ዓመት ክረምት እና በልግ ወቅት ወደ ግድቦች የገባው የዝናብ ውሃ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ግድቦች ማመንጨት የነበረባቸውን ያህል ኀይል ማመንጨት አለመቻላቸው በምክንያትነት የጠቀሰው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ሲሆን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የኀይል አቅርቦቱን ከግንቦት 1/2011 ጀምሮ በኹለት ፈረቃ ከፋፍሎ መዳረስ መጀመሩ ይፋ ያድርገው እንጂ የኀይል መቆራረጡ የተለመደ ነው። ይሁንና በተለያዩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ከ24 ሰዓት በላይ ያለ መብራት በመቆየት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደገቡ ይናገራሉ።

የውበት ሳሎን ባለሙያ የሆኑት ፍሬሕይወት ነብዩ ከሥራዋ ጋር በተያያዘ በኀይል አቅርቦቱ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ ውጥረት ውስጥ እንደገባች ትናገራለች። ፍሬሕይወት እንደምትለው የፀጉር ቤት ሥራ ያለመብራት ባዶ ነው። “ሁሉም ነገር ከዚህ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ለ24 ሰዓት ያለ አገልግሎት መቆየት ማለት ከቤት ወጪ ባለፈ ለቤት ክራይ የምንከፍለው እሰከ ማጣት ደርሰናል። ይህ የመብራት ፈረቃ ከመጀመሩ በፊት ባላወቅነው ምክንያት እስከ ሦስት ቀን በተከታታይ እየጠፋ ለሦስት ሳምንታት ያለሥራ ተቀምጠናል አሁንም በተባለው ሰዓት ማግኘት አልቻልንም” ትላለች።

የተፈጠረውን የኀይል አቅርቦት ክፍተት ለማስተዳደር በግድቦቹ ውስጥ ያለውን ውሃ እስከ ሰኔ 30/2011 ወይም ውሃ ወደ ግድቦቹ መግባት እሰከሚጀምር ድረስ የወጪ ንግድ ዘርፍ፣ የምግብ ማቀነባበሪያዎች፣ የመድኀኒት ፋብሪካዎች፣ ዩንቨርሲቲዎች እና ከማኅበራዊ አገልግሎት ማለትም ከመጠጥ ውሃና ከመሳሰሉ ምርቶች በስተቀር ማንኛውም ተጠቃሚ በሦሰት ፈረቃ እንዲጠቀም ቢወሰንም በአሁኑ ሰዓት ፈረቃው በኹለት ተከፋፍሎ ለዝቅተኛ ኀይል ተጠቃሚዎች እንዲደርስ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር መላኩ ታዬ ተናግረዋል። ይህ የሆነበት ምክንያትም በፊቱ በነበረው ፈረቃ የኔትወርክ መቆራረጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያስቸግር ነበር። ይህም ማለት ኅብረተሰቡ አገልግሎቱን በሚያገኝበት ጊዜ በቂ ሰዓት ሳያገኙ ከአገልግሎቱ ውጪ ሲሆኑ ይስተዋላል። ለዚህም ነው ኅብረተሰቡ ፍትሓዊ በሆነ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ እንዲሁም ኢኮኖሚውን እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴውን ከጉዳት ለመቀነስ ፈረቃውን በኹለት መንገድ የተደረገው ይላሉ።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሚኒስቴር ስለሺ በቀለ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አማካይ የማመንጨት አቅማቸው 2 ሺሕ 500 ሜጋ ዋት ቢሆንም ማመንጨት የተቻለው 1 ሺሕ 400 ሜጋ ዋት ብቻ ነው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ባለፈው ዓመት ክረምት ከፍተኛ ኀይል ከሚያመነጩ ጊቤ ሦስት፣ ቆቃና መልካ ዋከና ግድቦች በቂ ወሃ መያዝ አልቻሉም። በአንፃሩ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ፊንጫ፣ ጊቤ አንድና አመርቲ ነሼ ግድቦች በተሻለ መልኩ ውሃ ይዘው እንደነበር ታውቋል። በመሆኑም በአገሪቱ በተፈጠረው የኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት የኀይል ስርጭቱ በመላ አገሪቱ በፈረቃ እንደሚሆን እና ከፍተኛ ኀይል የሚጠቀሙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች፣ የብረታ ብረትና ሌሎች መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችም የፈረቃው አካል እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል።

በተያያዘም የድንጋይ ወፍጮዎች በግንቦት እና በሰኔ የኤሌክትሪክ ኀይል እንዳይጠቀሙ የተደረገ ሲሆን ለሱዳን የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኀይል ሽያጭም ሙሉ በሙሉ እንዲቆም እንዲሁም ለጅቡቲ የሚደረገው የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት 50 በመቶ የሚሆነው እንዲቀነስ መፈደረጉም ታውቋል።

የመጀመርያው የከፍተኛና መካከለኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ካላቸው የሥራ ባሕሪይ የተነሳ ለተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቋረጥባቸው መሥራት ስላለባቸው 50 በመቶ የሚሆኑት ከግንቦት 7 ቀን ጀምሮ በዐሥራ አምስት ቀን ልዩነት በፈረቃ እንዲጠቀሙ የተደረገ ሲሆን ከሰብስቴሽን በቀጥታ የኤሌክትሪክ ኀይል የሚያገኙ የብረታ ብረትና ሌሎች መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች 50 በመቶ የሚሆኑት በ24 ሰዓት ፈረቃ መርሃ ግብር እንዲሠሩ መደረጉን ጠቁመዋል።

በዚህ መሠረት ከፍተኛ የኀይል ጭነት ባለባቸው ከንጋቱ 11 ሰዓት እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት 514 ሜጋ ዋት፣ ከቀኑ አምስት ሰዓት እስከ ዐሥር ሰዓት 530 ሜጋ ዋት፣ ከቀኑ ዐሥር ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት 700 ሜጋ ዋት በማድረግ በሶስት ፈረቃ ተከፋፍሎ የነበረው አቅርቦት ተቀይሮ ማንኛውም ተጠቃሚ በቀን ለስምንት ሰዓታት ብቻ ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል ተብሏል፡፡

ሱዳን ዐሥር በመቶ የሚሆነውን የኀይል ፍላጎቷን ከኢትዮጵያ በምታገኘው ኀይል የሚሸፈን እንደነበር ተገልጿል። ከዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭም ኢትዮጵያ በዓመት 182 ሚሊዮን ዶላር ታገኝ ነበር፤ ሆኖም የኀይል ሽያጩ መቋረጡን ተከትሎ ኢትዮጵያ የምታገኘውን የውጪ ምንዛሬ ታጣለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here