አስደንጋጩ የዕፅ ተጠቃሚነት እና ዝውውር በአዲስ አበባ

0
1407

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በስፋት እየተስተዋለ ያለውን የአደንዛዥ (አነቃቂ) ዕፅ ዝውውርና ተጠቃሚነት በመታዘብ በወጣቱ ትውልድ ላይ እያደረሰ ያለውን ሞራላዊ ጉዳት በተመለከተ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ በዕፅ ዝውውር ጉዳይ ላይ ምርመራ በማድረግ፣ በዕፅ ተጠቃሚነት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችን በማናገር እና በጉዳዩ ዙሪያ የተሠሩ ምርምሮች እና ጽሑፎችን በማመሳከር የአደንዛዥ ወይም አነቃቂ ዕፅ ዝውውርና ተጠቃሚነትን የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

ቢኒያም ዮሴፍ (ሥሙ የተቀየረ) በኻያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ክልል የሚገኝ ወጣት ሲሆን፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የኮምፒውተር ሳይንስ የኹለተኛ ዓመት ተማሪ ነው። በከተማችን በግንባር ቀደምትነት በሚጠቀሱ የዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ቢኒያም፥ ትምህርት ቤቱ ካስገበየው ዕውቀት ጎን ለጎን በጓደኞቹ ግፊት እስከዛሬም ድረስ የተጣባውን አንድ ትልቅ ባላጋራ ይዞ ነበር የከፍተኛ የትምህርት ተቋምን የተቀላቀለው።

ቢኒያም እና ጓደኞቹ ዐሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ሳሉ ከመሞከር ወደ ኋላ የሚሉት ነገር አልነበራቸውም፤ በተለይ ደግሞ ከሱስ ጋር በተያያዘ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ቅዳሜና እሁድን ተንተርሰው በሚዘጋጁ የቀን ድግሶች (day party) ላይ በመገኘት መጠጡንም፣ ሲጋራውንም መሞከር ጀመሩ። በዚህ ሊወሰኑ ግን አልቻሉም፤ ወደ አደንዛዥ (አነቃቂ) ዕፆች በመሸጋገር በድብቅም ቢሆን በቀላሉ ሊገኝ የሚችለውን ካናቢስ ወይም ማሪዋና በመግዛት መጠቀም ጀመሩ። እንዲህ እንዲህ እያለ እንደቀልድ የተጀመረው የእነዚህን ታዳጊዎች የሱስ ጉዞ በተለይም ደግሞ የቢኒያምን ሕይወት ቁልቁል እንዲምዘገዘግ አደርጎታል።

ካናቢስ በማጨስ የተጀመረው የእነቢኒያም የዕፅ ተጠቃሚነት በሚማሩበት ትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ ውስጥ በማን አማካኝነት እንደሚገባ በማይታወቀው እና በስፋት ወደሚቸበቸበው የኮኬይን ሱስ ከፍ አለ። እስከዚህ ጊዜ ድረስ ቢኒያም እና ጓደኞቹ የሚያደርጉትን የትኛውንም የሱስ ተግባር ቤተሰብ አለማወቁ ትልቁ ችግር ነበር። ይሁን እንጂ ታዳጊዎቹ ኮኬይን መጠቀም ከጀመሩበት ቅፅበት ጀምሮ ነገሮች መልካቸውን ቀየሩ፤ ቢኒያምን ቀድሞ ከቤተሰቦቹ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት በአንድ ጊዜ ተቀየረ። መነጫነጭ የዘወትር ተግባሩ ሆነ፤ የፊት የቆዳ ቀለሙ እየተቀየረ መጣ፣ እንዲሁም ግዴለሽነቱ ከልክ ያለፈ ሆነ።
የቢኒያምን ታሪክ ከቤተሰቡ አንፃር ለመረዳት ወላጅ እናቱን ሕይወት ይልማን (ሥማቸው የተቀየረ) ቢሯቸው ድረስ በመሔድ አዲስ ማለዳ አነጋግራቸዋለች። ሕይወት “ከረፈደ ነበር የገባኝ” ሲሉ ይጀምራሉ ስለ ቢኒያም የሱስ ታሪክ ሲናገሩ። በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ገንዘብ ሲጠይቃቸው ከእኩዮቹ ጋር መዝናኛ ሥፍራ ሔዶ ለመዝናናት የሚል ሰበብ ይሰጣቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። “ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ግን ቢኒያም ላይ ለውጦችን ማየት ስጀምር ከፍተኛ ጥርጣሬ ገባኝ” የሚሉት የቢኒያም ወላጅ እናት፥ የጥርጣሬያቸውን እውነትነት ያረጋገጡት ደግሞ ቢኒያም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የጓደኛው እናት ለቢኒያም እናት ልጃቸው በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ መጠቃቱንና ቢኒያምም የዛው ተጠቂ እንደሆነ ሲነግሯቸው ነበር። ሕይወት ያኔ ከባድ ድንጋጤ ውስጥ መግባታቸውን ያስታውሳሉ። ከድንጋጤያቸው መለስ ሲሉ ከፍተኛ ብስጭት ውስጥ ይገባሉ። ይህንንም ተከትሎ መጀመሪያ ያደረጉት ቢኒያም የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲጨርስ አሜሪካን አገር ልከው እንደሚያስተምሩት የገቡትን ቃል መሰረዝ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ለቢኒያም ውሳኔያቸውን ከነምክንያቱ ቁጣ ባዘለ መንፈስ ሲነግሩት በብስጭት ቤቱን ለቆ በመውጣት ውጭ ማደሩን ያስታውሳሉ።

የልጃቸውን የሱስ መንገድ ሳግ በቀላቀለ አንደበታቸውና ፀፀት በሚበላው የእናት አንጀት የሚተርኩት ሕይወት, ገደቡን አልፎ የሚፈሰውን እምባቸውን ሐሳባቸውን እንዳይገልጹ በተደጋጋሚ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። “ቢኒያምን አሜሪካ ሔዶ እንዳይማር ያደረግኩት በግብታዊነት አይደለም” የሚሉት ሕይወት፥ ልጃቸው ከነሱሱ ወደ አገረ አሜሪካ ቢጓዝ እንደርሳቸው አስተሳሰብ በዓይነ ሥጋ በድጋሚ እንደማያገኙት እርግጠኛ ስለሆኑ ነበር። የሆነው ሆኖ ቢኒያም የኹለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን በአመርቂ ውጤት አልፎ አዲስ አበባ ዩኑቨርስቲን ተቀላቀለ። ዩኒቨርሲቲ መግባቱን ተገን አድርጎ ለጥናት በሚል ሰበብ ውጭ ማደር እና መሰንበት ያዘወተረው ቢኒያም, አብሮት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የገባው ደባል ሱሰ ጋር ቁርኝቱን ከመቼውም በላይ አጠነከረ። ጓደኛ የለውም፣ ሰው ሲያናግረው ወላጅ እናቱን ጨምሮ ትክክለኛ መልስ አይሰጥም፤ ቢሰጥም ፈጣን አይደለም። ቀናት ቀናትን ተክተው አንደኛው የትምህርት ዓመት አልፎ ኹለተኛው ተጀምሯል ቢኒያምም የኹለተኛ ዓመት ተማሪ ሆኗል።
በዚህ ጊዜ ግን ቢኒያም ከዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ተከታትሎ ለምሳ ወደ ቤቱ ገብቷል። በመኖሪያ ቤቱ ሳሎን ብቻውን የቴሌቪዥን ሲመለከት የነበረው ቢኒያም በድንገት ከፍተኛ ጩኸት ያሰማል። በቤቱ ከቤት ሠራተኛ በስተቀር ማንም ስላልነበር ቢኒያምን ይዞ ማረጋጋት የሚችል አልነበረም፤ ቢኒያምም ጩኸቱን እንደቀጠለ ከጊቢ በመውጣት ሰፈር ውስጥም ማዳረስ ጀመረ። ይህን ጊዜ ታዲያ የሰፈር ሰዎች ተረባርበው በመያዝ ወደ ሐያት ሆስፒታል ወስደው የመጀመሪያ የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኝ በማድረግ ለወላጅ እናቱ ይደውላሉ።

እንዲህ እንደቀልድ የተጀመረው የሱስ ታሪክ, በቢኒያም ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥሎበታል። ወላጅ እናቱ እንደሚሉት፥ ሦስት ጊዜ ወደ ሱስ ማገገሚያ ማዕከላት ገብቶ ተሽሎታል ተብሎ ከወጣ በኋላ እዛው ሱስ ውስጥ በመገኘቱ ድጋሚ በሽታው እንደሚያገረሽበት ይናገራሉ። ቢኒያም ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ አንድ ቦታ ተረጋግቶ ያለመቀመጥ ችግር ይስተዋልበት ነበር። በሽታው ሲነሳበት ምን እንደሚሰማው የሐበሻ የምላስ እጥፋት በማይታይበት እንግሊዘኛ ቋንቋ፥ “በጣም የሚያስጠላ ድምፅ እሰማለሁ፤ በተለይ ደግሞ የምሰማው ድምፅ እንዴት ረባሽ እንደሆነ ለሰዎች መግለጽ አለመቻሌ ያበሳጨኛል” ሲል ተናግሯል።

አሁን ላይ ቢኒያም ከትምህርት ገበታው ከተስተጓጎለ ድፍን ኹለት ዓመት ሆኖታል። ሳይንሳዊው መንገድ ምንም ለውጥ ማምጣት ስላልተቻለ ወደ መንፈሳዊው ሕክምና በማምራትም ለአራት ወራት ፀበል ሳይወጣ ሲጠመቅ እንደነበር ወላጅ እናቱ ሕይወት ይናገራሉ። አሁን ላይ የታየበትን ለውጥ ከግምት ውስጥ በማስገባት ታዲያ በተመላላሽ እንዲጠመቅ መደረጉን አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

የቢኒያም ከሱስ ጋር ተያይዞ ጤናው መታወኩ መላ ቤተሰቡን ከመደበኛ የኑሮ ዑደቱ እንዲስተጓጎል እንዳደረገው እናቱ በተሰበረ ልብ ይናገራሉ። “በልጅ የሚመጣን ጉዳት ወላጅ የሆነ ሰው ብቻ ነው የሚገባው” ሲሉ ስሜታቸውን በቃል ለመግለጽ አለመቻላቸውን ያሳብቅባቸዋል። ከሱስ ማገገሚያ ባለፈ ለምን ወደ አዕምሮ ሐኪም ዘንድ እንዳልወሰዱት አዲስ ማለዳ ላነሳችው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ያልደረስኩበት የአዕምሮ ሐኪም የለም። የሚሰጡት መድኀኒት ከመጠን በላይ እንዲተኛ ከማድረግ ባለፈ, በጤናው ላይ ምንም ለውጥ አላመጣም” በማለት የመጨረሻ አማራጫቸው ፀበል እንዲሆን መወሰናቸውን አስረድተዋል።
ቢኒያምን እንደማሳያ አነሳን እንጂ፥ ከአደንዛዥ (አነቃቂ) ዕፅ ጋር በተያያዘ በርካታ ወጣቶች የአዕምሮ ጤንነታቸው ይታወካል። ታዲያ ለእነዚህ አገር ተረካቢ ወጣቶች ጤና መታወክና ከምርታማነት መጉደል ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ሀይ ባይ ያጣው የአደንዛዥ እፅ ዝውውር መሆኑን አዲስ ማለዳ ባደረገችው ቅኝት ተረድታለች።

አዲስ አበባና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርና አጠቃቀም
አዲስ አበባ በርካታ ዓይነት ዕፆች እንደሚዘዋወሩ በየጊዜው የሚወጡት የፖሊስ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናዋ አሉ በሚባሉ የምሽት ጭፈራ ቤቶች ላይ ኮኬይን እና ካናቢስ ወይም ማሪዋና እና አልፎ አልፎም ቢሆን ሔሮይን የተባሉ አደንዛዥ (አነቃቂ) ዕፆችን መጠቀምና መሻሻጥ የተለመደ እየሆነ መጥቷል። አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችበት በተለምዶ ቦሌ መድኀኔዓለም በሚባለው አካባቢ ቁልቁል ደረጃዎች ተወርዶ የሚገባበት ቤት ነው። ቤቱ በቂ ብርሃን የለውም፤ ይህ በሁሉም ጭፈራ ቤቶች የተለመደ ነው ተብሎ ሊታሰብ ይችላል። ነገሩ ግልጽ የሚሆነው ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል ሲዘልቁ ነው። ጨለማው አይለመድም፤ ከአንዲት ሰማያዊ ቀለም ካላት የሸምበቆ መብራት በስተቀር የሚበራ ነገር የለም። ወደዚህ ክፍል ለመግባት ታዲያ መጀመሪያ በቤቱ የታወቁ ደንበኛ መሆን አሊያም ደግሞ የሚያውቁት ሰው ሊኖር ግድ ነው። ክፍሉ ውስጥ ኮኬይን የሚባል ነጭ ዱቄት መሳይ ነገር በግልጽ ይቸበቸባል። በአፍንጫ ይሳባል፤ መጠጥ ላይ እየተነሰነሰ ይጠጣል፤ ይላሳል። በዚህ ሁኔታ ላይ ለመታዘብ እንደተሞከረው ዕድሜያቸው ኻያዎቹ አጋማሽ እና ከዛ በታች የሆኑ ሴቶች እንዲሁም የሴቶችን ዕድሜ በዐሥር ዓመታት የሚያስከነዱ ጎልማሳ ወንዶች ተሳታፊ ነበሩ።

ሌላው ኤድና ሞል የተሰኘውን ሕንፃ በግራ በኩል በመተው ልቁልቁለቱን በጥቂቱ ወረድ ሲሉ አንድ የምሽት ቤት ይገኛል። በአደባባይ ሲወገዝና ሕገ ወጥነቱ ሲለፈፍ የሚውለው ሺሻ ገና ወደ ውስጥ ሳንገባ ሽታው ከደጅ ተቀብሎናል። እንደመጀመሪያው ምሽት ቤት ይሔ እምብዛም ጨለማ የሚባል አይደለም። ወደ ውስጥ ዘልቀን መቀመጫ እንደያዝን በቅርብ ርቀት ሺሻ እያጨሱ መጠጥ የሚጎነጩ ሦስት ወጣቶች በሺሻ ዕቃ ውስጥ ካናቢስ (ማሪዋና) በመጨመር ሲያጨሱ አስተውለናል። ትንሽ ግር የሚለው ነገር ደግሞ ሐሺሹን ከሸከፉበት ላስቲክ ነገር አውጥተው በሺሻ ዕቃው ላይ ለማድረግ ምንም ዓይነት መሸማቀቅ እና መደባበቅ አለማድረጋቸው በቤቱ የተለመደ ድርጊት እንደሆነ ያስገምታል።

በዚህ የምሽት ክበብ ውስጥ ከሺሻውና በሺሻ ዕቃ ከሚጨሰው ካናቢስ በተጨማሪ በሥፍራው በርከት ያሉ ወጣቶች ካናቢሱን በወረቀት ጠቅልለው በግላጭ ሲያጨሱ መመልከት ግርምትን ያጭራል።

ሦስተኛው የምሽት ቤት ከኹለተኛው ቤት አንድ ሆቴል ብቻ የሚለየውን ጎራ ልንልበት ወደድን። ይህ ቤት እስካሁን ከገባንባቸው የተለየ ይመሥላል። ወደ ውስጥ ለመዝለቅ በር ላይ ያለውን ጥብቅ ፍተሻ ማለፍ ግዴታ ነው። ፍተሻውን አልፈን ወደ ውስጠኛው ክፍል ስንዘልቅ ከሰዎች ላይ ከሚነሳው የሽቶ ጠረን ውጭ የሲጋራም ሆነ የሌሎች ነገሮች ሽታ አልገጠመንም። “ጉድና ጅራት ወደኋላ ነው” እንዲሉ በምሽት ቤቱ ውስጥ ልዩ የመስተናገጃ ክፍሎች ወይም በእነሱ አጠራር ‘ቪአይፒ ክፍሎች’ አሉ። እንደ መጀመሪያው ቤት ሁሉ እዚህም ለመግባት ታዋቂ ደንበኛ መሆን የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ቢሆንም ረብጣ ገንዘብዎን ይጭነቀው እንጂ በሮች ወለል ብለው ለሚከፍሉ ይከፈትላቸዋል። አዲስ ማለዳም አጋጣሚዎችን በመፍጠር ወደ ልዩ መስተናገጃ ክፍሎች ዘልቃለች። መጀመሪያው ቤት ላይ የታዘብነው ዱቄት መሳዩ ነጭ ነገር (ኮኬይን) እዚህ በስፋት አለ። ሽያጭ የለም፤ በቃ ዝም ተብሎ በአፍንጫ መሳብ ነው፣ ይጠጣል፣ በአፍንጫ ይማጋል፣ ይሳቃል፣ የምሽቱ ሕይወት ይኼንን ይመስላል።

አዲስ ማለዳ የአደንዛዥና አነቃቂ ዕፅ ዝውውሩን እና ወጣቶችን በተመለከተ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ያደረገቻቸው እንቅስቃሴዎች እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ነበር፤ ምክንያቱ ደግሞ ጥቃቅን ስህተቶች ከፍተኛ ዋጋ ስለሚያስከፍሉ ነው። በዚሁ በጠቀስነው ቦሌ መድኀኔዓለም አካባቢ ሸገር ሕንፃ ጀርባ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር የሚገኘው ቤት ደግሞ በቀዳሚዎቹ ቀናት ጉብኝት እንዳደረግንባቸው ቤቶች ዓይነት አይደለም። ከውጭ ሲታይ ዝም ያለ እና መደበኛ መኖሪያ ቤት ይመስላል። መኪናችንን አቁመን በጥሩምባ በሩን እንዲከፈት ምልክት ሰጥተን መጠበቅ ጀመርን በዚህ ጊዜ ታዲያ ከጊቢው ውስጥ አንድ ወጣት ልጅ ወደ እኛ በመቅረብ ማንነታችንን ከጠየቀንና አብሮን ከነበረው ሰው በተሰጠው ምላሽ በሩ እንዲከፈትልን ሆነ ወደ ውስጥም ገባን። አሁንም ጊቢው በአርምሞ እንደተሞላ ነው፤ ነገር ግን በጊቢውና በቤት ውስጥ በርከት ያሉ ሰዎች ተቀምጠው በለሆሳስ ይጨዋወታሉ።

ከአፍታ ቆይታ በኋላ አንድ እጅግ ግዙፍ ሰው በሰነድ መያዣ ቦርሳ የተለመደውን ኮኬይን በማውጣት ጮክ ብሎ ማጫረት ጀመረ። መጠኑ በግምት ከግማሽ ኪሎ የማይዘለውን ኮኬይን የጨረታ መነሻው 55 ሺሕ መሆኑን ግዙፉ ሰው አወጀ። ጨረታው ግን ብዙም ሳይዘልቅ ኮኬይኑ በ108 ሺሕ ብር ተሸጠ ግብይቱ ተጠናቀቀ። እኛም በሔድንበት ሁሉ ከለላ ሆኖን ሲያስጎበኘን ከነበረው ወጣት ባለሀብት ጋር ቤቱን ለቀን ወጣን። ይህን ጊዜ ግን እንዳመጣጣችን ብቻችንን አልነበርንም፤ መጀመሪያ በር ላይ ያነጋገረን ወጣት መኪና ተጋርቶናል።

የጨዋታችን ፍሰት ሔዶ ሔዶ ኮኬይኑን ከገዙት ግለሰብ ተቀብሎ የሚያከፋፍለው እሱ መሆኑን ተረዳን። አዲስ ማለዳ ለአከፋፋዩ የኮኬይን የመጀመሪያ መገኛው ከወዴት እንደሆነ ላቀረበችለት ጥያቄ “ኢትዮጵያ እኮ ቅዱስ አገር ስለሆነች ማሪዋና ብቻ ነው የምታበቅለው” ሲል ጀመረ። እንደ ወጣቱ ማብራሪያ ኮኬይኑ የሚገኘው በዓለም ዐቀፍ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የሚያዙት ዕፆች ከግማሽ በላይ አንዳንዴም ሙሉ በሙሉ በእጅ አዙር ከተማ ውስጥ እንደሚሸጡ ገለጸልን። በዚህ መሸጥና ገዝቶ የማከፋፈል ንግድ ውስጥም ከፌደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ባለሀብቶች፣ የባለሥልጣን ልጆች፣ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ባልደረቦች በተወጣጣ መረቡ እንደተዘረጋ ይናገራል።

በዚህ ሥራ ላይ ወደ አምስት ዓመት ገደማ እንደቆየ የሚናገረው ይኸው ባለታሪክ፥ አንድ ጊዜ ብቻ በፖሊስ ተይዞ ለቀናት ታስሮ እንደነበርና ማን እንዳስፈታው ባያውቅም እንደተፈታ አጫውቶኛል።

ከኮኬይን ጋር በተገናኘ ቦታዎችን እና ግለሰቦችን እንደማሳያ አነሳን እንጂ በርካታ ጉዶች ከዕፅ ዝውውር ጋር ይሰማሉ። በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፉ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ቀለበት ውስጥ ማስተላለፊያ መሆኗን ተከትሎ በርካታ ነገሮች ይሰማሉ፤ ይታያሉ።

ከኮኬይን በተጨማሪ መዲናዋ አዲስ አበባን እያመሳት ያለው ደግሞ የካናቢስ ወይም የማሪዋና ዝውውር እና ጥቅም ላይ መዋል ነው። ይህ ዓይነቱ ዕፅ በስፋት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ ይነገራል፤ ለዛም ይመስላል በርካታ ሥሞች ተሰጥተውታል። ማሪዋና፣ ጋንጃ፣ ኩሽ፣ ስፕሊፍ፣ ፖት፣ ኸርብ የመሳሰሉት የዳቦ ሥሞች ያሉት። ካናቢስን የመጀመሪያ ደረጃ እና ኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በስፋት እንደሚጠቀሙት መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ ደግሞ ከዋጋ አንፃር ቅናሽ ከመሆኑም በላይ በቅርበት መገኘቱ ነው።

ዕፁን በማከፋፈል ሒደት በርካታ ወጣቶች ተሳታፊ ሲሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለምዶ “ጀብሎ” ወይም ሱቅ በደረቴ የሚሠሩ ወጣቶች በስፋት እየሠሩት ይገኛሉ። አዲስ ማለዳ ለመታዘብ እንደሞከረችው በቦሌ አካባቢ ሰዓቱ ለዓይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር በየመንገዱ ዳር ቆመው ለእግረኛው በምስጢር ሥም በመጥራት ይፈልግ እንደሆነ ይጠይቃሉ፤ በመኪና ለሚንቀሳቀሱ ደግሞ ባትሪ መብራቶችን ብልጭ በማድረግ ምልክት በመስጠት ካናቢስ መያዛቸውን ያሳውቃሉ። በአንድ የሲጋራ ዘለላ ለሚሸጡት ካናቢስም እስከ ኻያ ብር ይጠይቃሉ።

በዋናነት ከሻሸመኔ በማስመጣት የሚያከፋፍለው በሠላሳዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኘው ጎልማሳ ፋሲል ሽፋ ረጅም ዓመታትን የቆየበት ሥራው ነው። በዚህ ሥራም ልጁን ደኅና ትምህርት ቤት ማስተማር ችሏል። ለባለቤቱም የልብስ መሸጫ ሱቅ እንደከፈተላት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ፋሲል እንደሚለው ለበርካታ ጊዜያት ተይዞ መታሰሩን ለማመልከት “የእኛ ኑሮ እኮ ግማሽ ውስጥ, ግማሽ ውጪ ነው” ብሏል። በእንደዚህ ዓይነት ሥራ ላይ አንዲት የፖሊስ አባል ሚስት ተቀናቃኝ መኖሯን የሚገልጸው ፋሲል, ባለቤቷን ተጠቅማ እንደምታሳስረው እና በዚህም ምክንያት ሦስት ወር በላይ በአንድ ቤት የቆየበት ጊዜ እንደሌለ ይናገራል።

ዕፆች ከጤና አንፃር
በአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶክተር ዮናስ ላቀው አደንዛዥ ዕፆች የሚያሳድሩት የአዕምሮ ጤና እክል በተለይም ደግሞ በወጣቱ ላይ በጉልህ እንደሚታይ በመጥቀስ ያብራራሉ። “በሥራ ዘመኔ ከዕፅ ጋር በተገናኘ ኹለት ብቻ ዕሜያቸው የገፋ ሰዎችን ነው ያከምኩት” ይላሉ። የአዕምሮ ሕመም መንሥኤው በውል የሚታወቅ እንዳልሆነ የሚገልጹት ዶክተሩ, በእርግጠኝነት ግን ዕፅ ተጠቃሚነት አንደኛው፣ ምናልባትም ዋነኛው መንሥኤ ነው ብሎ መናገር እንደሚቻል ግን አልሸሸጉም። በአሁኑ ሰዓት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የአዕምሮ ሕመም “ስኪዞፍሬኒያ” የሚባለው እንደሆነና መንሥኤው ደግሞ በዋናነት ዕፅ ተጠቃሚነት እናና የአልኮል ሱሰኝነት እንደሆነ አስረድተዋል።

እንደ ዶክተር ዮናስ ገለጻ፥ በተጠቀሰው በሽታ ከተጠቁት ሰዎች ውስጥም 10 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የሕክምና ዕርዳታ የሚያገኙት። በስፋት ከሚስተዋሉት የአዕምሮ ሕመሞች ድባቴ፣ ጭንቀት በላቀ ሁኔታ ትኩረት የሚያሻው “ስኪዞፍሬኒያ” በታማሚው ላይ ከባድ የሆነ የአዕምሮ ኹከት እንደሚያመጣ እና አላስፈላጊ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት በየዓመቱ 7 ሺሕ ሰባት መቶ ሰዎች ከዚሁ በሽታ ጋር በተያያዘ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን፥ ከዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚከሰተው በአዲስ አበባ መሆኑን ይናገራሉ። የተጠቀሰው የሞት መጠንም በአንድ ዓመት በትራፊክ አደጋ ከሚሞተው ቁጥር በ2 ሺሕ ብልጫ እንዳለው ያሳያል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የዶክተር ዮናስን ሐሳብ የሚጋሩት ደግሞ በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የምርምርና ሥልጠና ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ኃይሌ ናቸው። ዶክተር ክብሮም በአዲስ አበባ ከተማ ሔሮይን የሚባል እና በመርፌ የሚወሰደውን አደገኛ ዕፅ ወደ 4 ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች እንደሚጠቀሙ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይህ ደግሞ በሔሮይን ብቻ ሳይሆን በኮኬይን እና በካናቢስ በኩልም ቁጥሩ እጅግ እያሻቀበ መምጣቱን ነው የሚናገሩት። ዶክተር ክብሮም አያይዘውም በተለይ አሁን አሁን በትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ በዐሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች የአደንዛዥ (አነቃቂ) ዕፅ ተጠቃሚ መሆናቸው አሳሳቢ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

በመንግሥት የሚተዳደሩ የሱስ ማገገሚያ ማዕከላትንም በሚመለከት አማኑኤልን፣ ዘውዲቱ እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ጨምሮ በድምሩ 20 የሱስ ሕክምና የሚሰጥባቸው አልጋዎች እንዳሉ ዶክተር ብሩክ ተናግረዋል። ይህም በቂ እንዳልሆነና አንድ በሱስ የተጠቃ ታካሚ ቢያንስ ስልሳ ቀናትን ተኝቶ መታከም ስለሚኖርበት የረጅም ጊዜ ወረፋ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ። ዶክተሩ አሁን ባላቸው መረጃ መሠረት አንድ ታካሚ ከሱስ ጋር በተገናኘ ተኝቶ ለመታከም ከአንድ ወር ያላነሰ ጊዜ ወረፋ መጠበቅ እንደሚኖርበት አስረድተዋል።

በሱስ የተጠቁ ታካሚዎች በአብዛኛው የሚመጡት ከአዲስ አበባ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ክብሮም, ካለው ቅርበት አንፃርም ቶሎ ታክመው እንዲወጡ በማድረግ ተመላላሽ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉ እንዲሁም ለክልል ታካሚዎች ቦታ ለመልቀቅ ሲባል መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ስለ ሱስ ማገገሚያ ቦታ ጥበት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሔኖክ ይትባረክ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፥ ሆስፒታሉ በ1930 በጣሊያን ወረራ ዘመን እንደተገነባ ምንም መሻሻል ሳያሳይ፣ ከሕዝቡ ቁጥር ዕድገት ጋር አብሮ ባለማደጉ ችግሩ ከአቅም በላይ መሆኑን ነው የሚናገሩት። በሌሎች ሆስፒታሎች ያለው የአልጋ እጥረት ለአዕምሮ ሕመም በተለይም ደግሞ ለሱስ ሕክምና በቂ ዕውቀት አለመኖሩ መሆኑን ሙያዊ አስተያየት ሰጥተዋል።

የተፈጠረውን ችግር በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለመቅረፍ በሱስ የመጠቃት ችግር በስፋት በሚታይበት አዲስ አበባ ኻያ የጤና ጣቢያዎች ጋር በጋር እየተሠራ ስለሆነ እገዛ እንደሚያደርግ ያምናሉ። ከ2008 ጀምሮ በሥራ ላይ የተገባው ሆስፒታሉ ከጤና ጣቢያዎች ጋር በቅንጅት የሚሠራው ሥራ፥ ውጤታማነቱ ታይቶ በዐሥር ጤና ጣቢያዎች የተጀመረው አሁን ኻያ ደርሰዋል።
ሜዲካል ዳይሬክተሩ ጨምረው ሲገልጹ ከወንጀል ጋር በተገናኘ “ፎረንሲክ ሳይካትሪ” ሆስፒታሉ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ከዕፅ ተጠቃሚነት ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙት ወንጀሎች ሰማንያ አምስት በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ መሆኑንም አስረግጠዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here