በመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች የተፈጠረው ግጭት አሁንም እልባት አላገኘም

0
1055

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን መስቃንና ማረቆ በተባሉ ኹለት ወረዳዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት አሁንም ድረስ እልባት እንዳልተሰጠው ተገለፀ። ከመስከረም 3/2011 ጀምሮ ግጭቱ የተፈጠረ ቢሆንም እስካሁን ባለመብረዱ ዘጠነኛ ወሩን መያዙ ታውቋል። የሰላም ሚኒስቴር ዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ባለፈው ሚያዚያ 29/2011 ወቅት ችግሩን በሚመለከት ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን ጥናት እያካሔድኩ ነው ሲል አስታውቋል። በጥናቱም የሚገኘውን ግኝት መሰረት አድርጎ ሰላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድም ዝግጁ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ይሁን እንጂ ከአካባቢዎች የሚነሳውን ቅሬታ የምክር ቤት አባል ሟጅብ አብዱ ማረቆና መስቃን ወረዳ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ወደ ሰላም ሚኒስቴር ቀርበው አቤት እንዳሉ እና ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው በመግለፅ ምሬታቸውን ገልፀዋል። በተለይም የመስቃን ወረዳ አርሶ አደሮች በአሁኑ ሰዓት እየተፈናቀሉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ግጭቱን ለማረጋጋት በወረዳዎች በሰፈረው የመከላከያ ሰራዊት እንግልት እየደረሰባቸው እንደሆነም ሟጅብ ለምክር ቤቱ እና ለሚንስትሯ አስታውቀዋል።

ከዚህ ቀደምም በመስቃን ወረዳ ኢንሴኖ ከተማ አርሶ የአደሮች ማሳን በማቃጠል ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንዲከሰት የተደረገበት ሁኔታን አውስተው አሁንም የታየ ለውጥ አለመኖሩን አክለዋል።

የቀረበውን አቤቱታ በሚመለከት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪሃት ምላሽ ሲሰጡ የቀረበውን ቅሬታ እና በመከላከያ በኩል በመስቃን አርሶ አደሮች ላይ የሚደርሰውን መፈናቀል በሚመለከት የሰላም ሚኒስቴር የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ገልፀዋል። አያይዘውም የሰላም ሚኒስቴር በኹቱም ወረዳዎች ተከሰተውን ግጭት በድርድርና በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመስቃን ወረዳ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት የአካባቢው የሰላም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ገልፀው ፤ በቅርቡ በሰላም ሚኒስቴር የተጀመረው የሰላም ድርድሩም ከታሰበለት ጊዜ መንጓተት ማሳየቱን ገልፀዋል።

በወረዳዎቹ የተከሰተውን ግጭት በሚመለከት አዲስ ማለዳ በመስቃን ወረዳ የታየውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚመለከት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ምንም ምላሽ እየሰጠን አይደለም በማለት ነዋሪዎች ያቀረቡትን አቤቱታ መዘገቧ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋርም በተያያዘ በአንድ ታዳጊ ልጅ ላይ አሰቃቂ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ሲሆን በጥር 18/2011 ከሐዋሳ ወደ ቡታጅራ በሚያመራ የሕዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪ ላይም ማረቆ ወረዳ ልዩ ስሙ ወርካ በሚባል ስፍራ ጥቃት ደርሶበታል። በዚህም ወቅት በሰውና በንብረት ላይ ከባድና ቀላል ጉዳቶች ተከስቶ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here