ፓርላማው ዳኛ አየለ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ወሰነ

0
597

ከጥቅምት 2011 ጀምሮ የፌደራል ዳኞች አስተዳድር ጉባኤ በጣለባቸው ውሳኔ መሰረት ከደመወዝ እና ከሥራ ታግደው የቆዩት የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አየለ ዲቦ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወሰነ። ሰኞ፣ ግንቦት 12 በተደረገው መደበኛ ጉባኤ ላይ በሕግና ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረቡትን የውሳኔ ሐሳቦች በአብላጫ ድምጽ በማፅደቅ አስታውቋል።

የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ስንቅ የሌለው ቼክ በመፃፍ ወንጀል የተከሰሱትን አማኑኤል አዲሱ የተባሉ ግለሰብን ጨምሮ ሦስት ሰዎች ያጠቃለለውን መዝገብ በመመርመር፣ በአራዳ 3ኛ ምድብ ችሎት መዝገቡን በትዕዛዝ በማስመጣት እና በአቻ ፍርድ ቤት የተሰጠን ያለመጣመር ውሳኔ ሽረው አቤቱታውን በቀጥታ ተቀብለው ተጣምሮ እንዲታይ ውሳኔ መስጠታቸውን የሕግ ስህተት ፈፅመዋል በሚል ጥፋተኛ አድርጓቸውም ነበር።

መዝገቦቹን አጣምረው ክሱን መመርመር ሲጀምሩ ቀድሞ ክስ የተመሰረተበትን ከባድ የወንጀል ድርጊት ክስ ወደ ቸልተኝነት ድንጋጌ በመቀየር ዋስትና ወደሚፈቅድ አንቀጽ በማውረዳቸው እና ተጠርጣሪዎችም በተፈቀደው ዋስትና ተጠቅመው እንዲያመልጡ አስችለዋል በሚል ጉባኤው ጥፋተኛ ማድረጉ ታውቋል። መዝገቡን ሲያጣምሩ ክሱን አቅርቦ የሚከታተለውን ዐቃቤ ሕግ አልጠሩም፤ በዚሁ ምክንያት ክሱ እንዲመክን በመደረጉ መዝገቦቹ እልባት ሳይሠጣቸው እንዲቀሩ በማድረግ ከባድ የሥነ ምግባር ጥሰት ፈፅመዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ዳኛው ቋሚ ኮሚቴው ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡም አንደኛ ተከሳሽ በቃሊቲ ምድብ ችሎት ቀድመው በተከሰሱበት ጉዳይ ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በአራዳ ምድብ ችሎት በመከሰሳቸው ከጠበቃቸው ጥያቄ በቀረበ ጊዜ የአራዳውን ጉዳይ የያዘው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን በደብዳቤ አስተያየት ጠይቀው ተቃውሞ እንደሌለው በመግለፁ የተሰጠ ውሳኔ ነው ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም የአቻ ፍርድ ቤት ውሳኔን ሽረዋል መባላቸውንም የዳኛውን ውሳኔ በወቅቱ እንደማያውቁት አስረድተዋል።

በተጨማሪም ዋስትና በመፍቀድ ተከሳሾች እንዲጠፉ አድርገዋል ለሚለው ክስም ሕጉን እና መረጃዎችን መሰረት ተደርጎ የተሰጠ ውሳኔ ነው በሚል ዳኛ አየለ አስተባብለዋል።

“አንደኛ ተከሳሽ አራት ዓመት እስር እና 10 ሺሕ ብር ቅጣት ተፈርዶባቸው በቃሊቲ ማረሚያ እያሉ እና ምናልባት የዳኝነት ስህተት ተፈፅሟል ቢባል እንኳን በይግባኝ የሚታረምበት ሕግ ባለበት እና ለዋስትና የተያዘው አንድ ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን በወሰንኩበት ሁኔታ ግለሰቡን ሆን ብሎ ለመጥቀም የመንግሥትን ጥቅም አሳጥቷል የሚለው ውንጀላ ትክክል ካለመሆኑም ባሻገር ጉዳዩን ቀርቤ እንዳስረዳ እንኳን ዕድል አልተጠኝም›› ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።

“የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠኝን የመደመጥ መብት በመጣስ መልስ እንዲሰጥበት ባልተጠየኩበት ጉዳይ ጭምር ሳይቀር በምንአልባት ሊሆን ይችላል በሚል ከባድ ዲሲፒሊን ጥፋት ፈጽሟል፣ ከሥራ ይሰናበት ብሎ መወሰኑን ትክከል አይደለም›› በማለት ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የሰነድ ምርመራና ውይይት ዳኛ አየለ ዲቦ ክሱ እንዲቀጥልና በተለይም የአንደኛ ተከሳሽ መዝገብ እልባት እንዲያገኝ ያሳለፉትን ሒደትና የተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውን፣ የዋስትና ማስያዣው በአሰራሩ መሰረት ተሸጦ አንድ ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ ይደረግ ብለው ውሳኔ ማስተላለፋቸው መረዳት መቻሉን ገልጿል።

በተጠቀሰው የወንጀል ድንጋጌ መሰረት ተከሳሽ ጥፋተኛ መባላቸውን፣ ዳኛው የክስ ይጣመርልን አቤቱታ በጠበቆቹ ሲቀርብላቸው ከማስተናገዳቸው በፊት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስተያየት እንዲሰጥበት ያደረጉ መሆኑን፣ እንዲሁም የዳኛው ሕገ መንግሥታዊ የመደመጥ መብት ተከብሮላቸው ቢሆን ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችሉ አያይዘው ባቀረቡት ሰነድ ቋሚ ኮሚቴው ለመረዳት መቻሉንም በምክር ቤቱ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል።

ቋሚ ኮሚቴ ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ ዳኛው ከዚህ በፊት በሙያቸው የተመሠገኑ፣ የሥነ ምግባር ችግር የሌለባቸው እና የመጀመሪያ ስህተታቸው ነው የሚለውን የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ አባላት የልዩነት ድምጽ ግምት ውስጥ በማስገባት, ከማባረር በመለስ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ለተገለፀው ስህተት የሚመጥን የዲሲፒሊን ቅጣት በዳኞች አስተዳደራዊ ጉባኤ ደንብ መሰረት ተቀጥተው ወደ ሥራ ገበታው እንዲመለሱ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here