የተፈናቃዮችን የሰብኣዊ መብቶች አያያዝ የሚያጠና ቡድን ተሠማራ

0
767

የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የተፈናቃዮችን የሰብኣዊ መብቶች አያያዝ እና የመልሶ ማቋቋም ሒደትን የሚያጣራ፣ በምክትል ዋና ኮሚሽነር የሚመራ ቡድን በመላው አገሪቱ ማሠማራቱን አስታወቀ። ‘ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል’ የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ባሳለፍነው ሰኞ ግንቦት 11፣ 2011 ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም ዐቀፍ ስደተኞችን በተመለከተ እየወሰደ ባለው እርምጃ ከዓለም ዙሪያ እየተመሰገነ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የራሱን ተፈናቃይ ዜጎችን የያዘበት መንገድ ከሰብኣዊነት የራቀ ነው ማለቱ ለማጣራት እርምጃው ምክንያት መሆኑ ታወቋል።

ኢሰመኮ በመጠለያ ውስጠ ባሉ ዜጎች ላይ የተለያዩ ችግሮች እንደሚደርሱ ጥቆማዎች እንደሚቀርቡለት አስታውቋል። ዜጎችን በማፈናቀል ብዙ ችግር ያደረሱ አካላትን ለፍርድ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ከፍተኛ የተፈናቀይ ቁጥር በሚገኝባቸው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖችና ጉጂ ዞን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል በጌዲዮ፣ መልካዛ ወረዳና ሳይለም ወረዳ፣ መስቃንና ማረቆ ወረዳዎች እና በቤንቺ ማጂ ዞን እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ጐንደር ዞን ምልከታውን ያካሔዳል ተብሏል። በተጨማሪም በትግራይ ክልል ደቡብና ምሥራቅ ዞኖች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በካማሼ ዞን ተመሳሳይ ዳሰሳዎችን ያካሒዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ዓለም ዐቀፍ የስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚሠራው ‘ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል’ ግብረሰናይ ድርጅት በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በጫና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን አመልክቷል። በተለይም በደቡብ ክልል የተፈናቀሉ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን በግዳጅ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት መኖሩን አስታወቆ፥ “ይህ የመንግሥት እርምጃ፣ ያለውን የሰብኣዊ ቀውስ ሁኔታ የበለጠ የከፋ ያደርገዋል” ማለታቸውን ወደ አካባቢው ተጉዘው የነበሩት የግብረሰናይ ድርጅቱ ባለሙያ ማርክ ያርኔልን ጠቅሶ ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮቹ ተጠልለውባቸው የነበሩ ቦታዎችን በማፍረስ ጭምር ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል። አሁን እየተካሔደ ያለው የመመለስ ጥረት በፈቃደኝነት፣ በዘላቂነትና ከተፈናቃዮቹ ጋር በመተባበር የሚደረግ እስከሚሆን ድረስ የማስገደዱ ድርጊት እንዲቆም ጥሪውን አቅርቧል።

ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው በሚመለሱበት ጊዜ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው አያያዝ ተግባራዊ እንደሚደረግና ደኅንነታቸው ተጠብቆ የሚያስፈልጋቸው መሠረተ ልማት ተሟልቶ እንዲሆን መንግሥት ጥረት እንደሚያደርግ ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here