የማዕድናት ግብይት ማዕከላት በክልሎች ሊከፈቱ ነው

0
526

ሕገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር እንዲሁም ገዢ እና ሻጭን በቀጥታ ለማገናኘት በማሰብ የማዕድናት ግብይት ማዕከላት በክልሎች መክፈት መጀመሩን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። ዘላቂ ግብይትን ለመፍጠርና አምራቾችን በቀጥታ ከላኪዎች ጋር በማገናኘት ንግድ ስርዓቱን ጤናማ ማድረግ ነው ሲል አስታውቋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 3/2011 በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የኦፓል ማዕድን ግብይት የሚካሔድበት ማዕከል ተመርቆ ስራ መጀመሩንም የሚኒስቴሩ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሚካኤል መንገሻ ተናግረዋል። ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ጨምረው እንዳብራሩት በቀጣይ ደግሞ በሦስት ክልሎች ማለትም በደቡብ፣ በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ክልሎች የወርቅ ማዕድን ግብይት ሚካሔድባቸው ማዕከላት እንደሚከፈቱ አስታውቀዋል። በዚሁ አመት መገባደጃ ድረስም ተመርቀው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሏል።

ራሱን የቻለ መመሪያ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ስራ እንደሚገቡ የሚጠበቁት እነዚህ ማዕከላት፥ አሁን ላይ መመሪያው ተዘጋጅቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ማዕከላቱ በሚገኙበት የወረዳዎች የውሃ ፅሕፈት ቤት ስር እንደሚተዳደር ታውቋል። ነገር ግን መመሪያው ተዘጋጅቶ ሲጠናቀቅ እስከ ወረዳ በሚደርስ መዋቅር ስለሚዘረጋ የወረዳዎች የማእድን ፅሕፈት ቤቶች እንደሚያስተዳድሯቸው ይጠበቃል። በክልሎች ፍላጎት መሰረት ማዕከላቱ እንዲቋቋሙ እንደተደረጉ እና ባለቤቶችም የክልልና የወረዳ አካላት ናቸው የሚሉት ሚካኤል ፥ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የአደረጃጀት ሒደቱን እንደሚያስተባብር አክለዋል።

የሕገ ወጥ ንግዱን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል የተባሉት እነዚህ አዲስ የግብይት ማዕከላት በክልሎች መተግበሩ በተለይም ደግሞ በጋምቤላ ክልል እና በቤንሻንጉል ክልል የሚታየውን ውስብስብ እና ሕገ ወጥ የወርቅ ግብይትን ይፈታል ተብሎ ታምኖበታል ። በዚህ ጉዳይ ሚካኤል ሲናገሩ በኹለቱም ክልሎች ከክልሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ስራ እየተሰራ ቢሆንም አመርቂ የሚባል ለውጥ ሊመጣ አለመቻሉን አስታውቀዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ ንግዱን በተለይም ወርቅን የሚቆጣጠር አንድ የእዝ ጣቢያ መቋቋሙን አልሸሸጉም። ይህ ሁሉ ተደርጎ የሚፈለገው ለውጥ አልመጣም የሚሉት ኃላፊው የማዕከላት መገንባት አምራቾች በቀጥታ ወደ ላኪዎች ስለሚደርሱ የንግዱ መረብ ከማጠሩም በተጨማሪ ሕገ ወጥ ደላሎችን ከጭዋታ ውጭ ስለሚያደርግ ሕግ ወጥ ንግዱንም ይቀንሰዋል ብለዋል።

በኹለቱም ክልሎች ሕገ ወጥ የወርቅ ንግድን ከመከላከል ጎን ለጎን ምርቱንም ለማሳደግ በኅብረተሰቡ ደረጃ ሊቀርቡ የሚችሉ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዙ የወርቅ ማውጫዎችን ለማቅረብ ታቅዷል። ይህም ዘርፉን የምርት መጠን በማሳደግ ለብሔራዊ ባንክ የሚቀርበውን የወርቅ መጠን መጨመር እንደ አንድ እቅድ ተይዟል። በዚህም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከወርቅ ማዕድን ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች፣ ከወርቅ ግብይት ማኅበራት ኢነተርፕራይዞችና ማኅበራት አመራሮች ጋር በስፋት እየመከረበት እንደሆነ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here