የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ውሃ መቀነስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሥጋትን ፈጥሯል

0
575
  • የዝዋይ ሐይቅ ጥልቀት ከ12 ሜትር ወደ 4 ሜትር ቀንሷል
  • በአራት ዓመታት ውስጥ የዓሣ ምርቱም ከ6000 ቶን ወደ 1000 ቶን ወርዷል

በአገራችን የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ከፍተኛ የእሳተ ገሞራ ክምችት መኖሩን በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች መረጋገጡን ዋቢ የሚያደርገው የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እሳተ ገሞራውን አቀዝቅዘው የያዙት በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ የዝዋይ፣ የአቢጃታና ሻላ የመሳሰሉት የውሃ አካላት ላይ የተጋረጠው የመድረቅ አደጋ ክፍተኛ ሥጋት እንደፈጠረበት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በሐይቆቹ ላይ እየደረሰ ያለው ሰው ሰራሽ ጉዳት ከወዲሁ መፍትሔ ካልተፈለገለት አደጋው የከፋ በመሆኑ ገና የተቀናጀና የተጠናከረ ባይሆንም የመከላከል እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል። የሐይቆቹ ጉዳት ለወደፊቱ ሊከሰት ከሚችለው የእሳተ ገሞራ ሥጋት ባሻገር በአሁኑ ወቅት በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀጥተኛ ተጠቂዎች አድርጓል።
ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በዝዋይ ሐይቅ መታየት የጀመረው የእምቦጭ አረም፣ በሐይቁ ዙሪያ በብዛት የሚገኙ በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ አልሚዎች፣ ትላልቅ የአበባ ልማት ድርጅቶች፣ ሕገ ወጥ ዓሣ አጥማጆችና የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ከአቅሙ በላይ ጫና በማሳደር አደጋ ላይ ጥለውታል ሲሉ ለማ አበራ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባቱ ዓሣና ሌሎች የውሃ ውስጥ ሕይወት ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅና ከፍተኛ ተመራማሪ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመታት በፊት በዓመት በአማካይ ከ4 ሺሕ 500 እስከ 6 ሺሕ ቶን የሚደርስ ዓሣ ይመረትበት የነበረው ሐይቁ፣ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺሕ ቶን ያነሰ ምርት እየሰጠ ሲገኝ ጥልቀቱም ከ12 ሜትር ወደ 4 ሜትር ወርዷል። በተለይ የሞጆ-ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ቀኑን ሙሉ አቧራ ለመከላከል ሲባል በውሃ ማመላለሻ መኪኖች ከሐይቁ ውሃ እየቀዳ በመንገዱ ላይ በማፍሰስ ተጨማሪ ጫና እያሳደረ ነው ሲሉ ለማ ይናገራሉ።

ከአርሲ ከታርና ከጉራጌ መቂ ወንዞች ወደ ዝዋይ ሐይቅ ይገባ የነበረው ንፁሕ ውሃ በየአካባቢው በሚካሔዱ የመስኖ ልማቶች ተቆራርጠው እየቀሩ መሆናቸው ደግሞ ለሐይቁ ብክለትም ሆነ ለውሃ መጠኑ መቀነስ አሉታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱን አዲስ ማለዳ ከኢንስቲትዩቱ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የዝዋይ ሐይቅ የመድረቅ አደጋ አሳሳቢነትን በመረዳት ከአርሲ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የሐይቁን ጫና ለመቀነስና መልሶ እንዲያገግም የሚያደርጉ ጥናቶችና ምክረ ሐሳቦች እየቀረቡ ናቸው።

700 ወጣቶች በማደራጀትም ፓርኩን እየጠበቁና የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በማከናወን ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አሠማርተናቸዋል ብሏል ኢንስቲትዩቱ።

የኢፌድሪ የአካባቢ ደንና የአየር ለውጥ ሚኒስትር በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ከሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎቹ ጋር በተደጋጋሚ በስልክ ለመገናኘት ብንችልም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው በነሱ በኩል ያለውን ምላሽ ማካተት አልቻልንም።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here