የመንግሥት እና ሃይማኖት ግንኙነት መሠረቱን እንዳይስት!

0
690

ያለፉት መንግሥታዊ ስርዓቶች የመንግሥት እና ሃይማኖት መቀላቀል ሳያሳስባቸው ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅ ወይም ተቀባይነት ለማግኘት አንዱን ሃይማኖት፣ ወይም አንዱን የአንድ ሃይማኖት ክንፍ በመደገፍ ወይም ሌላውን በመቃወም እና በማዳከም በርካታ ስህተቶችን ሠርተዋል። ይህም ታሪካዊ ቁርሾዎች፣ ጠባሳዎች እና ቅሬታዎችን ትቶ አልፏል። እንደዚህ ዓይነቱ በመንግሥት እና ሃይማኖት መካከል ያለ መርሕ አልባ ግንኙነት እስከወዲያኛው መቋረጥ ይኖርበታል።

በዘውዳዊው አገዛዝ ወቅት መንግሥታዊ ሃይማኖት በመኖሩ ምክንያት አንዱ የበላይ እምነት ሌላኛው የበታች ተደርገው መታየታቸው ያደባባይ ምስጢር ነበር። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የፀደቀው የመጀመሪያው ሕገ መንግሥትም ይሁን ኹለተኛው (የተከለሰ) ሕገ መንግሥት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና የንጉሠ ነገሥቱ ሃይማኖት እንደሆነ ይደነግጋል። ንጉሠ ነገሥቱ ሥልጣናቸውን ሊቀሙ የሚችሉበት ብቸኛው ምክንያት ሃይማኖታቸውን ከቀየሩ ወይም የተለየ እምነት ተከታይ የሆነች ሚስት ካገቡ እንደሆነ በግልጽ ይደነግግ ነበር።

የሃይማኖት ነጻነትን የሚጠይቁ ሰዎች በ1966ቱ አብዮት ወቅት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደነበራቸውም አይዘነጋም። አብዮቱ ዘውዳዊውን ስርዓት አፍርሶ በዚያው እግር የተተካው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር – ደርግ – በተሳሳተ የርዕዮተ ዓለም አረዳድ ሳቢያ – እምነትን ከቤተ መንግሥት ለመነጠል ከመሞከርም ባለፈ የዜጎችን የማመን መብት እና ነጸነት እስከሚዘልቅ ድረስ ተፅዕኖ ያደርግ ነበር። ምንም እንኳን በደርግ ስርዓት ውስጥ እምነት በመንግሥት ውስጥ ጣልቃ መግባት እንዳይችል ቢደረግም፣ መንግሥት ግን በእምነት ጉዳይ ጣልቃ ይገባ ነበር ማለት ይቻላል።

በ1987 የፀደቀው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ይህንን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት በማሰብ የሃይማኖት እና መንግሥት መቀላቀልን በይፋ ከመርሖዎቹ አንዱ አድርጎ ደንግጓል። ይኸውም በአንቀፅ 11 እንደተመለከተው አንደኛ “መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው”፣ ኹለተኛ “መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም” እና ሦስተኛ “መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም። ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም” በሚል ግልጽ ተደርጓል።

ይሁንና መንግሥት ይህንን መርሕ በመጣስ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ለመከፋፍሎች መንስኤ ሲሆን እንደነበር በርካታ ጊዜ ተስተውሏል። እንደ አብነትም የቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ለስደት ተዳርገው፥ ሲኖዶሱም ለኹለት ተከፍሎ መሰንበቱ ይታወሳል። በተመሳሳይ መንግሥት አንድ የእስልምና አስተምኅሮ ያለ ሕዝበ ሙስሊሙ ፈቃድ ሊጫንብን ነው በሚል በርካታ ሙስሊሞች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ከመክረማቸውም ባሻገር ለመፍትሔ ፍለጋ የመረጧቸው የሃይማኖት አባቶች ለእስር እና ከፍተኛ እንግልት ተዳርገው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የተከሰተው ለውጥ እነዚህን በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ሳቢያ የተከሰቱ ክፍፍሎች ለማረም ረዥም ርቀት መሔዱ፥ መንግሥትን የሚያስመሰግነው መሆኑ ቢታመንም፣ በሃይማኖት እና በአማኞቹ መካከል ያሉት ጉዳዮች በራሳቸው በአማኞቹ እንዲፈቱ በመተው የመንግሥት እና የሃይማኖት መለያየት መሠረታዊ መርሕ ተከብሮ መቆየት አለበት ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

መንግሥት ቅሬታዎችን ለመፍታት ባደረገው ሙከራ የቤተ እምነቶቹ ክፍፍሎች በሠላም መፈታታቸው የሚደነቅ ቢሆንም፥ መንግሥት የግጭት እና ክፍፍል መንስኤ መሆን የማይገባውን ያክል ራሱን እንደ አስታራቂ አድርጎ ማቅረቡም ቢሆን ከጣልቃ ገብነት ተለይቶ አይታይም። የመንግሥት የአሁን እርምጃዎች ከውጤታቸው አንፃር ተገምግመው ከላይ ሲታዩ አዎንታዊ ቢሆኑም እንኳን በቤተ እምነት ውስጥ ጣልቃ መግባቱ የሕገ መንግሥት ጥሰት ስለሚሆን የሚጠበቅበት እርምጃ እጁን ከሲኖዶሱም ይሁን መጅሊሱ ማውጣት እንጂ ቀጣዩን ሒደት በሙሉ አማኞቹ በራሳቸው መንገድ እንዲያከናውኑ መተው ይኖርበታል።

የመንግሥት እንደ አስታራቂ ሆኖ መቅረብ ቅሬታ ያስከተለባቸው የእስልምና እና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች አሉ። የሸራቱኑ ጉባዔ በመባል የሚጠቀሰው እና ባለፈው ወር የተደረገው ሥምምነት እየተካሔደ በነበረበት ሰዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሲያደርጉ ድምፃቸውን በተቃውሞ ያሰሙ ሰዎች መኖራቸው ለዚህ አንዱ ምሳሌ ነው። በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም ከፖለቲካ ለውጡ ጋር ለማመቻመች ያለሙ መሸጋሸጎች መኖራቸው በብዙኀን መገናኛዎች ተደምጠዋል። እንዲህ ዓይነቶቹን አካሔዶች እና በአማኞች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚደረጉ ተፅዕኖ አሳዳሪ የመንግሥት እና የሃይማኖት መሪዎች ግንኙነት በጥንቃቄ መታየት አለበት ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

መንግሥት የፀጥታ እና ደኅንነት ጉዳይ ካልተከሰተ በቀር፣ በአማኞች መሐል የሚገባበት አንዳችም ምክንያት መኖር የለበትም። የእምነት ነጻነትን ሙሉ ለሙሉ ማክበር፣ በእምነት ተቋማት ውስጥም ይሁን በሃይማኖት መሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ራሳቸው በራሳቸው እንዲወስኑ ማድረግ የመንግሥት ኀላፊነት ነው። ይህ ግን የመንግሥት ኀላፊነት ብቻ አይደለም፤ የሃይማኖት አባቶችም በውስጣቸው ያሉ ችግሮችን (ካሉ) ራሳቸው በራሳቸው መፍታት መማር አለባቸው እንጂ የመንግሥትን ቡራኬ ወይም ሽምግልና መጠበቅ የለባቸውም። ስለዚህ ከወዲሁ ይታሰብበት!

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here