ምርጫ ቦርድ ኢዴፓ አልከሰመም አለ

0
614
  • የኢዴፓ መክሰም ሕጋዊ አይደለም ያሉ የምክር ቤት አባላት ክስ መሰረቱ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ምክር ቤት አባላት ፓርቲው የከሰመበት መንገድ ሕግና ስርዓቱን የተከተለ አይደለም ሲሉ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክስ መስርተዋል። የኢዴፓ ሊቀ መንበር የነበሩት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሕጋዊ መስመሩን ተከትለን ነው የከሰምነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘችው ምላሽ እንደሚያመለክተው ቦርዱ የኢዴፓ’ን መክሰም አያውቅም፤ ኢዴፓም መክሰሙን የሚገልጽ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ እንዳላቀረበም ታውቋል።

ኢዴፓ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ውሕደት ለመፍጠር ጠቅላላ ጉባኤ መጋቢት 1/2011 መጥራቱን ለምርጫ ቦርድ አሳውቆ እንደነበር የገለጹት የቦርዱ ኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ, ጠቅላላ ጉባኤው ሕጉን ተከትሎ መካሔድ አለመካሔዱን ምርጫ ቦርድ በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል አዳነ ታደሰ በፓርቲያቸውን ጉዳይ ዙሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳነጋገሯቸው እንዲሁም የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳም እልባት እንዲሰጡ ማሳሰባቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ይህ ጉዳይ በሒደት ላይ እያለና የኢዴፓ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በፓርቲው ሕገ-ደንብ መሰረት ምንም ዓይነት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የመዋሐድ ውሳኔ ባላስተላለፈበት ሁኔታ የምክር ቤቱ አራት አባላት ጠቅላላ ጉባኤ መጠራቱ ሌላው ስህተት መሆኑን አዳነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እነ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የመሰረቱት አዲስ ፓርቲ እንጂ, የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት ነባር ፓርቲዎችን የማዋሐድ እንቅስቃሴ አለመሆኑ እየታወቀ ኢዴፓ ከስሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር እንደተዋሐደ ተደርጎ መነገሩ ፍጹም ሕገ-ወጥ በመሆኑ, ቦርዱ እርምጃ ይወስዱልን ስንል አመልክተን የምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ ሊወስን በቀጠሮ ላይ ነን ሲሉም አዳነ አክለውዋል።

መጋቢት 1/2011 ተካሔደ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ ያልተገኘበትና የፓርቲው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ተስፉ መስፍን በፓርቲው ሕገ ደንብ መሰረት የተካሔደ አጠቃላይ ጉባኤ አለመሆኑን አጣርተናል፤ በጉባኤው ላይ ተገኙ የተባሉት አብዛኞቹ ሰዎች የኢዴፓ አባላት አለመሆናቸውንና ማንነታቸው የማይታወቁ ግለሰቦች መሆናቸውንም አረጋግጠናል ብለዋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን አጣርቶ ፓርቲው ሕጋዊ ሕልውናውን አግኝቶ የሚቀጥልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች መጠየቁን ተስፉ ለአዲስ ማለዳ አክለዋል።

ጫኔ በተነሱት ክሶች ላይ ለአዲስ ማለዳ ዝርዝር ምላሽ ሊሰጡ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በእነሱ በኩል ያለውን ምላሽ ማካተት አልተቻለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here